​ቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ቅድመ ዳሰሳ፡ አል አህሊ ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ  

የ2017 ካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ቅዳሜ ምሽት አሌክሳንደሪያ ከተማ ላይ ይደረጋል፡፡ አል አሃሊ እና ዋይዳድ ካዛብላንካም በፍፃሜው የተገናኙ ሁለት የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ሁነዋል፡፡ ሁለቱም ክለቦች የየሃገራቸውን ሊጎች በተደጋጋሚ ቢያሸንፉም በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ ግን በጣም የተለያየ የውጤት ደረጃ አላቸው፡፡ አሃሊ የ8 ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮን ሲሆን ዋይዳድ አንድ ግዜ ውድድሩን ማሸነፍ ችሏል፡፡

አመቱ ለአል አሃሊ መልካም ነበር ማጋነን አይሆንም፡፡ ክለቡ የግብፅ ፕሪምየር ሊግን አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ሲያጠናቅቅ ተጋጣሚው ዋይዳድ የከተማ ተቀናቃኙን ራጃ ካዛብላንካ እና ፉስ ራባትን ሳይፈትኑት የቦቶላ ሊግን ማሸነፍ የቻለው፡፡ በቅዳሜ የፍፃሜው ጨዋታ ዙሪያ ስለሚነሱ ሃሳቦች እነሆ እንዲ አቅርበንሏችኋለን፡፡

እንዴት መጡ?

አል አህሊ

አል አሃሊ በቻምፒየንስ ሊጉ በመጀመሪያው የማጣሪያ ዙር ቤድቬስት ዊትስን በአጠቃላይ ውጤት 1-0 በማሸነፍ ነበር ወደ ምድብ ያለፈው፡፡ በምድብ መ ከፍፃሜ ተጋጣሚው ዋይዳድ ካዛብላንካ፣ ዛናኮ እና ኮተን ስፖርት ጋር ሲደለደል በ11 ነጥቦች ከምድቡ በሁለተኛ ሆኖ ነበር ወደ ሩብ ፍፃሜ ያመራው፡፡ በሩብ ፍፃሜው እና ግማሽ ፍፃሜው የቱኒዚያ ባላንጣዎቹን ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝን (4-3) እና ኤትዋል ደ ሳህል (7-4) አሸንፏል፡፡ ካደረገቻው 12 ጨዋታዎች 6 ሲያሸንፍ በ4 ጨዋታዎች ነጥብ አቻ ተለያይቶ በ2 ጨዋታዎች ሽንፈትን ቀምሷል፡፡

ዋይዳድ ካዛብላንካ

ዋይዳድ ከቻምፒየንስ ሊጉ ምድብ ለመግባት ተቸግሮ ነበር፡፡ ወደ ጋቦን አምርቶ ከሞናና ጋር ያደረገውን ተሸንፎ በመለያ ምት 5-4 አሸንፎ ወደ ምድብ የገባው፡፡ በምድብ መ የተደለደለው የካዛብላንካው ክለብ ምድቡን በበላይነት ነው ያጠናቀቀው፡፡ በሩብ ፍፃሜው የ2016ቱን የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን በመለያ ምት ሲረታ በግማሽ ፍፃሜው ዩኤስኤም አልጀርን 3-1 ለፍፃሜ ቀርቧል፡፡ አሸንፎ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች 7 አሸንፎ 4 ተሸንፎ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለይቷል፡፡

አል አሃሊ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ተጋጣሚዎችን በተደጋጋሚ ከመረበሽ አልፎ ግቦችን ለማስቆጠር አይቸገረም፡፡ ቢሆንም ለአሃሊ የ2017 የቻምፒየንስ ሊግ ጉዞ ማማር ትልቁን ሚናን የተወጡት አሰልጣኝ ሆሳም ኤል ባድሪ ናቸው፡፡ በ2012 ክለቡ ለስምንተኛ ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮን ያደረጉት ኤል ባድሪ በተጫዋቾች ላይ የፈጠሩት መነቃቃት አሃሊን ለፍፃሜ እንዲበቃ እንዳስቻለው ለግብፁ የእንግሊዘኛ የእግርኳስ ድረ-ገፅ ኪንግፉት እና በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ቁጥራዊ መረጃዎችን ለሚያቀርበው ለአርቃም የሚሰራው ሂሻም አብዞርኪ ለሶከር ኢትዮጵያ ሃሳቡን አካፍሏል፡፡ “ሆሳም ኤል ባድሪ ወደ አሰልጣኝነት መንበሩ ከተመለሱ በኃላ በአል አሃሊ ያለው የተጫዋቾች የግል ባህሪ መሻሻልን ከማሳየት አልፎ የአሁኑ የአሃሊ ትውልድ ያልነበረውን ግን በወርቃማው ዘመን እንደጎማ፣ አቡትሪካ እና ባራካት የመሳሰሉት የነበራቸውን የቡድን መንፈስ በትንሹም መመለስ የቻለ የጠበቀ ግንኙነት ፈጥረዋል፡፡ የፕሪምየር ሊጉን ለማሸነፍ አልከበደውም እንዲሁም ግብ ጠባቂው ሻሪፍ ኤክራሚ በሊጉ ታሪክ በበርከታ ጨዋታዎች ግብ ያልተቆጠረበት ተጫዋቾች ሆኗል፡፡ ለዚህ እና መሰል ተጨባጭ የአሃሊ ለውጦች ምክንያቱ ኤል ባድሪ ነው፡፡ በአንድ ወይም ሁለት አጋጣሚ ለቡድ ተጫዋቾች እድል ሰጥቷል ይህም ሁሉም ተጫዋች ያቻለውን እንዲያበረክት አድርጓል፡፡ እንደሳላህ ጎማ ያሉ በግል ባህሪያቸው ምክንያት ከተለያዩ አሰልጣኞች ጋር የሚጋጩ ተጫዋቾችን ጥሩ እንዲቀሳቀሱ ማስቻሉን ስትመለከት ኤል ባድሪ ለአሃሊ ውጤት ቁልፍ እንደነበረ ትረዳለህ፡፡”  ሲል ያስረዳል፡፡

የዋይዳድ አሰልጣኝ ሁሴን አሞታ ለኳታሩ ሃያል ክለብ አል-ሰዓድ ቆይታ በኃላ ወደ ሃገሩ ተመልሶ የቦቶላ ሊግን ከማሸነፍ በዘለለ ቡድኑን ከ2011 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ለቻምፒየንስ ሊጉ ፍፃሜ አደርሰዋል፡፡ አሞታ ምንም እንኳን በሚጠቀሙት ወደ መከላከል ያዘነበለ የአጨዋወት ስርዓት በደጋፊዎች ባይወደድላቸውም ውጤታማነታቸው ላይ ግን ጥያቄ ማንሳት የሚቻል አይመስልም፡፡ ክለቡ የፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ማድረጉ ለአሞታ የለመዱትን ታክቲክ እንዲከተሉ ያስገድዳቸዋል፡፡ በዚህ ሃሳብ ሞሮኳዊው ሙአድ ቤንዞክሪ ይስማማል፡፡ “የዋይዳድ ቁልፍ ጥንካሬ አሰልጣኝ ሁሴን አሞታ ናቸው፡፡ እውነት ለመናገር ለዋይዳድ ደጋፊዎች ታክቲክ አሰልቺ ቢሆንም ዋይዳድን ጠንካራ ያደረገውን ግን ይህ አሰልቺ ታክቲክ ነው፡፡ የአሁኑ የዋይዳድ ተጫዋቾች ሙሉ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጫወቱ ያስቻለ በመሆኑ ነው የክለቡ ጥንካሬ ከአሰልጣኝ አሞታ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለው፡፡ ተጫዋቾቹን ላቀደው ዓላማ ለማነሳሳት አይቸገርም እንዲሁም ተጫዋቾቹ ለእሱ ያላቸው ክብር ከፍተኛ ነው፡፡ አዎ በአብዛኛው ከሜዳ ውጪ ዋይዳድ የሚከላከል ቡድን ሆኗል፡፡ ይህ የሆነው ቡድኑ ሲጫወት አሞታ የአቻ ውጤትን ወይም በጣብብ የግብ ልዩነት መሸነፍን ቅድሚያ ስለሚሰጡ ነው፡፡ የተከላካይ መስመሩም አስተማማኝ አይደለም፡፡ ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና ዩኤስኤም አልጀር ጋር የተደረጉትን ከሜዳ ውጪ በተደረገው ጨዋታ የቡድኑ አጥቂዎች በመከላከል ተጠምደው ነበር ሙሉ ደቂቃውን የጨረሱት፡፡”

ሂሻምም ሆነ ሙአድ በአሃሊ እና በዋይዳድ ጠንካራነት ቢስማሙም የፍፃሜው ጨዋታ አሸናፊ ላይ የተለያየ ሃሳብ አላቸው፡፡ “ለእኔ ፍፃሜ በጣም አስቸጋሪ እና ፈተና የበዛበት እንደሚሆን አስባለው፡፡ ሁለቱም እኩል የማሸነፍ እድል ነው ያላቸው፡፡ አሃሊ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከአስቸጋሪ ጨዋታዎች ውጤቶችን ለማምጣት አለመቸገሩ ስታይ የማሸነፍ እድሉ ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡ በሜዳው ማሸነፍ ባይችል እንኳን ካዛብላንካ ድረስ ሄዶ የማሸነፍ የብቃት ደረጃ አሃሊ ይዟል፡፡ ተቃራኒውም ሊያጋጥም ይችላል ነገር ግን ደጋፊው፣ ተጫዋቾቹ እና አሰልጣኞቹ ዋንጫው ወደ ግብፅ እንዲመለስ ፅኑ ፍላጎት አላቸው፡፡ በዚህ ላይ በክለብ የዓለም ዋንጫ ላይ የግብፅ ተወካይ ማየት እንፈልጋለን፡፡”

ሙአድ በበኩሉ የሞሮኮ ንጉስ መሃመድ ስድስተኛ፣ የዋይዳድ ፕሬዝደንት እና የሞሮኮ እግርኳስ ፌድሬሽን ሊቀርበው የታቀደው ሽልማት ተጫዋቾች አሃሊን ለማሸነፍ ይበልጥ እንዲሚያጠናክራቸው ያምናል፡፡ “በወረቀት ደረጃ አሃሊ ከዋይዳድ ይሻላል፡፡ ነገር ግን በሜዳ ላይ ይህ አይሆንም፡፡ በምድብ የተገናኙ ግዜ ካዛብላንካ ላይ ዋይዳድ 2-0 አሸንፏል፡፡ ከሜዳው ውጪ ደግሞ በጥቃቅን ስህተቶች አሃሊ አሸንፏል፡፡ ሁሴን አሞታ ከፉስ ራባት ጋር ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ማሸነፍ ችሏል እንዲሁም አል ሰዓድ የእሲያ ቻምፒየንስ ሊግ ሲሸንፍ ምክትል አሰልጣኝ ነበር ስለዚህም ለትልቅ ፍፃሜ አዲስ አይደለም፡፡ አምና በዛማሌክ ከደረሰባቸው ሽንፈት መርሳት ይፈልጋሉ ለዚህም አሃሊን ማሸነፍ ያስፈልጋል፡፡ እንደሌካች እና ቤንዲር የመሳሰሉ ተጫዋቾች የመጫወት ዘመናቸው እየተጠናቀቀ በመሆኑ ቢያንስ ጫማ ከመስቀላቸው በፊት ትልቅ ውድድር ማሸነፍ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ላይ የክለቡ ፕሬዝደንት ቻምፒየንስ ሊጉ ካሸነፉ ትልቅ ሽልማት እንዳዘጋጀ እየተነገረ ነው፡፡ የሞሮኮ ንጉስም ውጤት ከመጣ ተጫዋቾቹን ቤተ-መንግስት ጋብዞ እንደሚሸልም ቃል ገብቷል፡፡ ይህ የማንኛውም የሞሮኮ ዜጋ ምኞት ነው፡፡”

አሃሊ በቡድን ጥልቀት ከተጋጣሚው ዋይዳድ የተሻለ ነው፡፡ ዋይዳድ እንደዊልያም ጄቦር እና ፋብሪስ ኦንዳማ ያሉ አጥቂዎቹን ለቆ ክፍተቱን መድፈን አልቻለም፡፡ ቢሆንም ከቆመ ኳስ እና ከመስመር ከሚሻገሩ ኳሶች ግብ ማስቆጠር የሚችሉ ተጫዋቾችን ይዟል፡፡

የሚጠበቁ ተጫዋቾች

ጁኒየር አጃዬ እና አሊ ማሎል (አል አሃሊ)

ናይጄሪያዊው አጥቂ ጁኒየር አጃዬ ለአሃሊ ከፈረመ ወዲህ ምርጥ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል፡፡ ከኳስ ውጪ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች፣ የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀሙ፣ የተጋጣሚ ተከላካይን መፈተን መቻሉ ጁኒየርን በዚህ ጨዋታ እንዲጠበቅ ያደርጉታል፡፡ አጥቂው በሩብ ፍፃሜ እና ግማሽ ፍፃሜ ላይ ያሳየው ጥሩ ብቃት ተከትሎ የዋይዳድ አስተማማኝ ያልሆነ የተከላካይ ክፍል አጥቂውን የማቆም ፈተና ውስጥ ይገባሉ፡፡

የግራ መስመር ተከላካዩ አሊ ማሎል ግብ የሆኑ ኳሶችን ከማቀበልም አልፎ በመስመር የሚደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መልካም ናቸው፡፡ በመከላከሉም በማጥቃቱም ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የሚሳየው ማሎል ከቆሙ ኳሶችም እጅግ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ቱኒዚያዊው ኢንተርናሽናል ለአህጉሪቱ የክለቦች ውድድር ላይ አዲስ አለመሆኑ ያለው ልምድ አሃሊን እንዲጠቀም ያደርገዋል፡፡

መሃመድ ኦንዠም እና የሱፍ ራባህ

የመስመር አጥቂ እና አማካይ ሆኖ መሰለፍ የሚችለው መሃመድ ኦንዠም በዘንድሮው የቻምፒየንስ ሊግ የውድድር ዘመን ጥሩ ብቃታቸውን ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል የሚመደብ ነው፡፡ ኦንዠም ለአጥቂዎች በሚያደርሳቸው የተመቻቹ ኳሶችን እና በመስመር ላይ የሚያሳየው ጥሩ ብቃት የዋይዳድ ዋነኛ የማጥቃት መሳሪ ነው፡፡ ዋይዳድ በዚህ ዓመት ባደረጋቸው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ላይ ግቦች እንዲቆጠሩ ምክንያት የሆነው ኦንዠም ነው፡፡ ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች የሁሴን አሞታ ታክቲክ ጥንቃቄን መምረጡም ቢሆን ኦንዠምን ኮከብ ከመሆን አላገዱትም፡፡ ኦንዠም ከሚያሳየው ብቅት አንፃር ለሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን መመረጥ አለበት የሚሉ የሰሜን አፍሪካ የእግርኳስ ተከታታዮች በርክተዋል፡፡

የመሃል ተከላካዩ የሱፍ ራባህ ቡድኑ የመካላከል ድክመት ቢታይበትም በግሉ ጥሩ ዓመት አሳልፏል፡፡ ራባህ ባልተረጋጋው የዋይዳድ ካዛብላንካ የተከላካይ መስመር በሁሴን አሞታ እምነት የሚጣልበት ተጫዋች ነው፡፡ የተከላካይ አጣማሪው አይመን አቱቺ በቅጣት ምክንያት በመጀመሪያው የፍፃሜ ጨዋታ ላይ አለመኖሩ ስጋት ቢሆንም በግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ጥሩ የተንቀሳቀሰው ራባህ በዚህ ጨዋታ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚሆኑ ተጫዋች አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በፍፃሜው ጨዋታ ዙሪያ ምን ተባለ?

“ከውድድሩ መጀመሪያ አንስቶ አላማችን ዋንጫ ማሸነፍ ብቻ ነበር፡፡ ከፊታችን ያሉብንን ጨዋታዎች ማሸነፍ ነው የእኛ ትኩረት፡፡ በፍፃሜው ይህንኑ እንተገብራለን፡፡ ዋንጫውን ማሸነፍ ይገባናል ብዬ አምናለው፡፡ ሁሉንም ነገር በትክክል ነው እስካሁን የሰራነው፡፡ ከዋይዳድ ጋር በምድብ ጨዋታ ስለተገናኘን ሁለታችንም በሚገባ እንተዋወቃለን፡፡ እናከብራቸዋለን ግን ማንም አንፈራም፡፡” ሆሳም ኤል-ባድሪ (አል-አሃሊ)

“የአል አሃሊው ጨዋታ ከባድ ነው በተለይም ኤትዋል ላይ ስድስት ካስቆጠሩ በኃላ ፈታኝ ነው የሚሆነው፡፡ ኤትዋል ላይ ካስመዘገቡት ትልቅ ውጤት ቢመጡም እኛ ግን ለመቋቋም አይቸግረንም፡፡ በአሰላለፋችን ላይ እምብዛም ለውጥ አላደርግም፡፡ በማጥቃት እና በመከላከል ላይ መመጣጠን እንዲኖር አደርጋለው፡፡ የመጀመሪያው ዙር የፍፃሜ ጨዋታ የአፍሪካ ቻምፒዮን ለመሆን ለምናደርገው ጉዞ ወሳኝ ነው ስለዚህ ከሜዳችን ውጪ ግብ ማስቆጠር አለብን፡፡”

ስለአይመን አቱቺ ቅጣት

“በአንድ ተጫዋች ላይ የምንጠለጠል አይደለንም፡፡ ለዚህም የተጫዋቾቹን ለማነሳሳት እንፈልጋለን፡፡ አቱቺ በምድብ ጨዋታ ላይ ከአሃሊ ጋር ከሜዳችን ውጪ ተጫውተን 2-0 ስንሸነፍ የቡድኑ አባል ነበር፡፡ በአንድ ተጫዋች ላይ ጥገኛ አይደለንም፡፡” ሁሴን አሞታ (ዋይዳድ ካዛብላንካ)

ኢትዮጵያዊው ባምላክ ተሰማ ጨዋታውን በመሃል ዳኛነት ጨዋታው ይመራል፡፡

የቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ 2017 ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር)

2፡00 – አል አሃሊ (ግብፅ) ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ) (ቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም)

ጨዋታውን ቤን ስፖርትስ ኤችዲ 1 በቀጥታ ያስተላልፋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *