​የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ዛሬ የምድብ ጨዋታዎች ተጠናቀዋል

[ ሪፖርት – በለጠ ኤርበሎ ከሆሳዕና ]

የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዋንጫ የመጨረሻ ጨዋታዎች ተደርገው ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያለፉ ቡድኖች ተለይተዋል፡፡

ቀትር 6:00 ላይ የተገናኙት የምድብ ለ መሪው ደቡብ ፖሊስ እና ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደገው በቀድሞ ስሙ ሚዛን አማን እንዲሁም በአዲሱ ስያሜው ቤንች ማጂ ቡና ጨዋታቸውን አንድ አቻ በሆነ ውጤት አጠናቀዋል፡፡ ደቡብ ፖሊስ ከእረፍት በፊት አገኘው ልኬሳ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ሲሆን ከእረፍት መልስ መሰለ ወልደሰንበት በቅጣት ምት ጎል ቤንች ማጂ ቡናን አቻ አድርጓል፡፡ ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቀን ተከትሎ ደቡብ ፖሊስ በቀዳሚነት፣ ቤንች ማጂ ቡና በተከታይነት ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፈዋል፡፡

8:00 ላይ በምድብ ሀ ተጠባቂው የሀላባ ከተማ እና የሀዲያ ሆሳዕና ያለግብ ተጠናቋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በጨዋታው ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እና የጎል ሙከራዎችን አድርገው በጨዋታው ምንም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል፡፡ በዚህ ውጤት መሠረትም ሁለቱም ቡድኖች በእኩል 5 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው ሀዲያ ሆሳዕና አንደኛ ሆኖ ሲያልፍ ሀላባ ከተማ በሁለተኝነት ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀል ችለዋል፡፡

10:00 ላይ በተደረገው ሌላኛው የምድብ ሀ ጨዋታ መውደቃቸውን ያረጋገጡትን ስልጤ ወራቤ እና ዲላ ከተማ ተገናኝተው ዲላ ከተማ ከእረፍት መልስ ቢኒያም በቀለ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ከዚህ ምድብ አስቀድመው ሀዲያ ሆሳዕና እና ሀላባ ከተማ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፋቸውን ተከትሎ ዲላ ከተማና ስልጤ ወራቤ ከምድብ ሳያልፉ ሲቀሩ ከምድብ ለ ሀምበሪቾ ዱራሜ ሌላኛው ተሰናባች ሆኗል፡፡

የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች የፊታችን አርብ ጥቅምት 24 የሚደረጉ ሲሆን ሀላባ ከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና ከ ቤንች ማጂ ቡና የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *