​ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ዳሰሳ | ወልዲያ ከ አዳማ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሶስት የመክፈቻ ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ፡፡ በመሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታድየም ወልዲያ አዳማ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታም 09:00 ላይ ይጀመራል፡፡ በጨዋታው ዙርያ ጥቂት ነጥቦች እነሆ::
ወልዲያ አምና ካደረገው የዝውውር እንቅስቃሴ በተለየ በሊጉ ተፎካካሪ ሊያደርገው የሚችል የተጫዋቾች ዝውውር በመፈጸም ክረምቱን አሳልፏል፡፡ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስን አሰልጣኝ አድርጎ የሾመውና ከ10 በላይ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ወልዲያ የተከላካይ መስመሩን በማጠናከር ላይ ያጋደለ ቢሆንም በሊጉ ደረጃ ምርጥ የሚባሉ ተጫዋቾችን ሰብስቧል፡፡ ቡድኑ አምና የታየበትን የግብ ማስቆጠር ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ አጥቂዎችም አስፈርሟል፡፡

አዳማ ከተማ በሊጉ ጥቂት ተጫዋች ካስፈረሙ ክለቦች አንዱ ነው፡፡ 5 ተጫዋቾች ያስፈረመው የአሰልጣኝ ተገኔ አሰፋ ቡድን በተከታታይ ሶስት አመታት ሶስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ያሳየውን ወጥነት ዘንድሮ ለመድገም ሊቸገር ይችላል፡፡  በተለይ በአማካይ ክፍል የሚታይበት የፈጠራ ችግርን ሳይቀርፍ ተጨማሪ አጥቂዎችን አስፈርሞ የውድድር አመቱን መጀመሩ ግራ አጋቢ ሆኗል፡፡

ከሊጉ መጀመር በፊት በተደረጉ ውድድሮች ደቡብ ካስቴል ዋንጫ ላይ የተካፈለው ወልዲያ ከምድቡ ማለፍ ሳይችል የቀረ ሲሆን አዳማ ከተማም በተመሳሳይ በአአ ከተማ ዋንጫ ከምድቡ ማለፍ አልቻለም፡፡ 

በጨዋታው ባለሜዳው ወልዲያ የማጥቃት አጨዋወቱ የተሻሻለ ቡድን ይዞ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አምና በንጉሴ ደስታ እየተመራ እጀግ የበዛ መከላከልን ሲተገብር የነበረው ወልዲያ የአስለጣኝ ለውጡ የቡድኑንም አቀራረብ ሊለውጠው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ሆኖም የመከላከል ባህርይ ባላቸው ተጫዋቶች የተዋቀረው ስብስብ በፍጥነት አቀራረቡ ይለወጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከሜዳው ውጪ ተጠቅጥቆ መከላከልን ከሚመርጠው አዳማ ከተማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታም በቀላሉ የግብ እድሎች ይፈጥራል፣ ጎሎችንም በቀላሉ ያስቆጥራል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ 

በጨዋታው ላይ የቡድኖቹ የቅርብ ጊዜያት (ከአምና ጀምሮ) አቋም ሊንፀባረቅ ይችላል፡፡ ወልዲያ በሜዳው ካደረጋቸው ያለፉት 15 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ሽንፈት ሲያጋጥመው አዳማ ከተማ ደግሞ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ሁለት ድል ብቻ አስመዝግቧል፡፡ 

አዳማ ከተማ የአጥቂ መስመሩ በእጅጉ ሳስቶ ወልዲያን ይገጥማል፡፡ አሰልጣኝ ተገኔ ቡልቻ ሹራ፣ ሚካኤል ጆርጅ፣ ታፈሰ ተስፋዬ እና አላዛር ፋሲካ በጉዳት እንደማይሰለፉ የገለጹ ሲሆን ዳዋ ሁቴሳ የአጥቂ መስመሩን ለብቻው እንደሚመራ ይጠበቃል፡፡ በወልዲያ በኩል ደግሞ አዳሙ መሐመድ እና ተስፋሚካኤል በዛብህ ጨዋታው የሚያመልጣቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡

እርስ በእርስ ግንኙነት 

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 4 ጊዜያት በሊጉ የተገናኙ ሲሆን አዳማ ከተማ 2 ፣ ወልዲያ 1 ጊዜ አሸንፈዋል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በአምና ግንኙነታቸው አዳማ ላይ አዳማ 1-0 ሲያሸንፍ ወልዲያ ላይ ወልዲያ በተመሳሳይ 1-0 አሸንፏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *