​የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዋንጫ በደቡብ ፖሊስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ከጥቅምት 19 ጀምሮ በሆሳዕና ከተማ አስተናጋጅነት ላለፉት 7 ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የሰነበተውና የደቡብ የከፍተኛ ሊግ ክለቦችን ያሳተፈው ካስቴል ዋንጫ ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ ደቡብ ፓሊስ አስተናጋጁ ሀዲያ ሆሳዕናን በመለያ ምቶች በመርታት አሸናፊ ሆኗል፡፡

አስቀድሞ 6:00 ላይ ከፍፃሜው በተደረገ የደረጃ ጨዋታ ሀላባ ከተማ ቤንች ማጂ ቡናን በተመስገን ይልማ እና ቴዎድሮስ አሞ ጎሎች 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የሶስተኛ ደረጃንና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ዳንኤል ጌታቸው ለቤንች ማጂ ቡና ብቸኛዋን ጎል ያስቀጠረ ተጫዋች ነው፡፡

8:00 ሰዓት ላይ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መደበኛ ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡ በጨዋታው ሁለቱም አጋማሾች በኳስ ቁጥጥር እና በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመቅረብ ሀዲያ ሆሳዕና ብልጫ መውሰድ ቢችልም ጎል ማስቆጠር አልቻለም፡፡ አሸናፊውን ለመለየት ሁለቱ ቡድኖች ወደ መለያ ምት አምርተው ደቡብ ፖሊስ 6-5 በማሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀው የደቡብ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ካስቴል ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሸና የክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮሚሽነር ፍሰሃ ጋረደው ባስተላለፉት የመዝጊያ ንግግር የውድድሩ ዋነኛ ዓላማ የክለቦችን የእርስ በእርስ ትስስር ከማጠናከሩም በላይ ቡድኖች ያሉበትን ደረጃ የሚያዩበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽነር ፍሰሃ አክለውም የሁሉም ክለብ ደጋፊዎች ለስፖርታዊ ጨዋነት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ኮከቦች

ኮከብ ተጫዋች – አበባየሁ ዮሐንስ (ደቡብ ፖሊስ)

ኮከብ ግብ ጠባቂ – አልሜ ኤሬሮ (ቤንች ማጂ ቡና)

ከፍተኛ ግብ አግቢ – ተመስገን ይልማ (4 ጎሎች – ሀላባ ከተማ)

ኮከብ አሰልጣኝ – ግርማ ታደሰ (ደቡብ ፖሊስ)

ምስጉን ዋና ዳኛ – ፌ/ል ዳኛ ባህሩ ተካ

ምስጉን ረዳት ዳኛ – ፌ/ል ዳኛ ወጋየሁ አየለ

የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ደቡብ ፓሊስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *