​የሐረሪ፣ አፋር እና ጋምቤላ እግርኳስ ፌዴሬሽኖች በምርጫው ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል

የሐረሪ፣ አፋር እና ጋምቤላ እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ዛሬ 4፡00 በኢትዮጵያ ሆቴል በተለይ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ጋር የተያያዘ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫው ላይ የአፋር እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት መሃመድ ያየ፣ የሐረሪ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት አብዱልሃኪም አብዱልራህማን እና የጋምቤላ እግርኳስ ፌድሬሽን ተወካይ ቻን ጋትኮት ተገኝተዋል፡፡

ጉባኤው ከሰመራ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ መደረጉን እንደማይደግፉት ያስታወቁ ሲሆን ፊፋ የፕሬዝደንታዊ ምርጫው የዓለም አቀፉን እግርኳስ አስተዳዳሪ አካል መርህ እና ህግ ያከበረ እንዲሆን ፌድሬሽኑን ያሳሰበበተን ደብዳቤ እንደሚቀበሉት በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል፡፡

አቶ መሃመድ በመግለጫቸው ጠቅላላ ጉባኤው ከሰመራ የተዛወረበት ሁኔታ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡ ለፌድሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሱት አቶ መሃመድ ዳግም ወደ አዲስ አበባ ጠቅላላ ጉባኤው መዛወሩን ከሚዳያ መስማታቸውን ገልፀዋል፡፡ “በአሁኑ ሰዓት በአፋር ውስጥ ክለቦች እያደራጀን እና አደረጃጀቶችን እየፈጠርን ከነበርንበት ሁኔታ የተሻለ ነገር እየፈጠርን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው በሰመራ ቢካሄድ ስፖርቱን ከማነቃቃት አንፃር በእኛ ክልል እንዲካሄድ ግልፅ የሆነ ደብዳቤ ፅፈናል፡፡ ፌድሬሽኑም ጥያቄያችንን ተቀብሎ ጉባኤው በሰመራ እንደሚካሄድ እና ለመስተንግዶ አስፈላጊውን ዝግጅት እንድናደርግ በደብዳቤ አሳውቆናል፡፡ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራዎን እና ዝግጅቶችን ማድረግ ከጀመረ በኃላ ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ ሳይገለፅልን የጉባኤው ቦታ ዝውውር በሚዲያ ሰምተናል፡፡ ባለድርሻ አካላትን እና የውጭ እንግዶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ቦታ መለወጣችንን እንገልፃለን የሚል ምላሽ ያለው ደብዳቤ ከቆይታ በኃላ አግኝተናል፡፡ በአፋር ክልል ጉባኤው ማካሄዱ የሚያመጣው ጉዳት ምንድነው? ”

ፌድሬሽኖቹ በተለይ የፕሬዝደንታዊ ምርጫው መራዘም እንዳለበት ያሳሰቡ ሲሆን የፊፋ አሰራርን የተከተለ መሆን እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡ የጉባኤው ስፍራ ወደ አዲስ አበባ መዛወሩን ተከትሎ ጥቅምት 30 በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤም ላይ በጉዳዩ ላይ ተቋውማቸውን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ለዝግጅት ከፍተኛ ግንዘብ የአፋር ክልል ከማውጣቱ ባሻገር የሞራል ጉዳትም በህዝቡ ላይ እንደደረሰ የፌድሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ መሃመድ ገልፀዋል፡፡ የእጩዎች ማሳወቂያ ቀን ማጣር፣ ክልሎች አንድ ለፕሬዝደንታዊ ምርጫ እና አንድ ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት አቅርቡ የሚለው የፌድሬሽኑ ደብዳቤም ከህጉ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ እንደማይቀበሉት ገልፀዋል፡፡ ፌድሬሽኑ የግለሰብ ነው አንዳባልም ጉዳዩ ተመርምሮ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው ቀናት ሲቀሩት ይህንን መግለጫ ለማድረግ ለምን ታሰበ ተብለው አቶ መሃመድ ከጋዜጠኞች ለተጠየቁት ጥያቄ “ቀን እና ሰዓቱ ለውጥ የለውም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን 10 መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በመጪው ሐሙስ አዲስ አበባ ላይ የሚያካሄድ ሲሆን የፕሬዝደንታዊ ምርጫው ፊፋ የአሰራር ክፍተት አለበት ብሎ ባቀረበው ሃሳብ መሰረት መራዘሙ ይታወቃል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ገና ከጅምሩ በእጩዎች አመራረጥ፣ ህግ እና ደንብ ያለከበሩ ጉዳዮች ፌድሬሽኑ ላይ መታየታቸውን ተከትሎ አነጋጋሪ ሆነው ሰምብተዋል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንትም የፊፋ ዋና ፀሃፊ ፋትማ ሳሞራ ፌድሬሽኑን በምርጫው ካሳሰቡ በኃላ በወቅቱ የስራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባላት በመካከል ፀብ መፈጠሩ ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *