​ሪፓርት | አዳማ ከተማ እና ደደቢት ያለግብ አቻ ተለያይተዋል

በሁለተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ደደቢትን ያስተናገደው አዳማ ከተማ ጨዋታውን 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት አጠናቋል፡፡

እምብዛም የጠሩ የግብ እድሎች ባልተፈጠሩበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባለሜዳዎቹ አዳማዎች የበላይነት የታየበት ሲሆን በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የሜዳ ክፍል በመግባት በቁጥራቸው በርከት ያሉ ኳሶች ከግብ ክልል ውጪ በቀጥታ ኢላማቸውን ባይጠብቁም ሲሞከሩ ተስተውለዋል፡፡

በአዳማ በኩል በተለይም በ13ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ተስፋዬ በሰራው ስህተት የተገኘውን ኳስ በረከት ደስታ ከግራ መስመር አክርሮ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም በ16ኛው ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም ሲሳይ ቶሊ ሁለት ተጫዋቾችን ቀንሶ ያሻማውን ኳስ በመቀስ ምት ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ ተጠቃሽ ነበሩ፡፡ በተጨማሪም በ19ኛው ደቂቃ ከነአን ማርክነህ ከደደቢት የግብ ክልል ጠርዝ ላይ ሞክሯት ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት ኳስ በአዳማ ከተማ በኩል ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ወደ ጨዋታው ቀስ በቀስ መግባት የቻሉት ደደቢቶች ለወትሮው በመከላከል ጥንካሬው ይታወቅ የነበረው የአዳማ ከተማ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች የሚሰሩትን በርካታ የቦታ አጠባበቅና ከልክ ያለፈ የራስ መተማመን ስህተቶች መጠቀም አልቻሉም እንጂ በርካታ እድሎችን ማግኘት ችለው ነበር፡፡

ከወትሮው በተለየ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾቻቸውን ቁጥር አብዝተው የገቡት ደደቢቶች ከዚህ ቀደሙ በተሻለ ወደ ማጥቃት አንድ ሶስተኛው መድረስ ቢችሉም ኳሶቹን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በተለይም ሽመክት ጉግሳ፣ አቤል ያለው እና ፋሲካ አስፋው ያመከኗቸው አስቆጪ አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው እጅጉን በተቀዛቀዘ መልኩ ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ ታይቶበታል፡፡ በመሀል ሜዳ ላይ ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጡ ኳሶች ታጅቦ የተካሄደው ይህ የጨዋታ አጋማሽ ከመጀመሪያው በተቃራኒ በርካታ ጉሽሚያዎችና ካርዶች የበዙበት ነበር፡፡ በዚህም በ70ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማው የቀኝ መስመር ተከላካይ የሆነው ተስፋዬ ነጋሽ ሽመክት ጉግሳ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተቃረበበት የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም ቡድኖች በቀጥተኛ አጨዋወት በፍጥነት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ ግቦችን ለማግኘት ጥረት አድርገዋል፡፡ በተለይም አዳማ ከተማዎች በሱሊይማን መሀመድ እንዲሁም በሙጂብ ቃሲም ያደረጉት ጥረት ሳይሰምር ቀርቷል፡፡

ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አዳማ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ነጥብ ሲያሳካ በአንፃሩ ደደቢቶች በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ያለ ግብ በአቻ ውጤት መለያየት ችለዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ

“ማንኛውም ቡድን ወደ ሜዳ የሚገባው ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ነው፡፡ የኛም ተጫዋቾች የዛሬውን ጨዋታ በዚያው አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው ነበር ወደ ጨዋታ የገቡት፡፡ አንድ ተጫዋች እንኳን ጎድሎብን ጫና ፈጥረን ለመጫወት ሞክረናል፡፡ ነገርግን እንዳለመታደል ሆነ አቻ ለመለያየት ተገደናል፡፡”

ንጉሴ ደስታ – ደደቢት 

“ቡድናችን በብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ምርጫ ምክንያት በመዳከሙ በዛሬው ጨዋታ እምብዛም ልምድ የሌላቸው ወጣት ተጫዋቾች ለመጠቀም ተገደናል፤ ነገርግን ብዙ እድሎችን ብናገኝም መጠቀም ሳንችል ቀርተናል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *