​ኢትዮጵያ ሴካፋ ላይ በአዳዲስ ተጫዋቾች ልትቀርብ ትችላለች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከህዳር 24 ጀምሮ በኬንያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ሲንየር ቻሌንጅ ዋንጫ ላይ እንደሚካፈል ተረጋግጧል፡፡ 

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሪምየር ሊጉ መርሃ ግብር ላይ ተጽእኖ በማይፈጥር ሁኔታ በውድድሩ ለመካፈል እንዳቀደ የተሰማ ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም በብሔራዊ ቡድን እምብዛም የመጫወት እድል ያላገኙ እና በየክለቡ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ባሳዩ ወጣቶች ብሔራዊ ቡድኑን እንዲገነቡ መመርያ እንደተሰጣቸው ተሰምቷል፡፡ አሰልጣኝ አሸናፊ በቅርብ ቀናት ውስጥ የተጫዋቾች ምርጫ በማድረግ ለውድድሩ ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩም ታውቋል፡፡ 

ኢትዮጵያ በተካፈለችባቸው አመዛኞቹ የሴካፋ ውድድሮች ዋናውን ቡድን ስታቀርብ የቆየች ሲሆን በጥቂት አጋጣሚዎች በሊጉ መርሀ ግብር አስገዳጅነት (በከፊል) እና በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ (ሙሉ ለሙሉ) ምክንያት ሙሉ ቡድኗን ሳታቀርብ ቀርታለች።
የሴካፋ ዋንጫ ህዳር 16 እንዲጀመር ታስቦ የነበረ ቢሆንም ወደ ህዳር 24 መገፋቱ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *