የኢትዮጵያ ​ፕሪምየር ሊግ 20 አመታት – ክፍል 2

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወጥ በሆነ የውድድር ፎርማት መካሄድ ከጀመረ 20ኛ አመቱን መድፈኑን በማስመልከት የተለያዩ ፅሁፎች እያደረስናችሁ እንገኛለን፡፡ ዛሬ በሁለተኛው ክፍል በፕሪምየር ሊጉ 20 አመታት የተከሰቱ ዋና ዋና ክስተቶችን እንዲህ አቅርበንላችኋል፡፡  


የክፍል አንድ ፅሁፍን እዚህ ያገኛሉ | LINK


1991

በዚህ የውድድር ዘመን ከሊጉ በታች ከሚገኘው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሙገር ሲሚንቶ እና ምድር ባቡር አድገው የተሳፊዎች ቁጥር ወደ 10 ከፍ አለ፡፡ ድሬዳዋ ላይ በተደረገው የማጠቃለያ ውድድር በቀዳሚነት ያጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስም በመጣበት አመት አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ዋንጫውን ከፍ አደረገ፡፡  ይህም ብቻ ሳይሆን 9 ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ሪኮርድ ማስመዝገብ ቻለ፡፡ በወቅቱ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያለፈው ሙገር ሲሚንቶ ብቸኛው የኦሮሚያ ቡድን በመሆኑ በሶስት የኦሮሚያ ከተሞች (አሰላ፣ ጅማ እና ወንጂ) እየተዘዋወረ የሜዳውን ጨዋታ ማድረጉ የጊዜው አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡ 

እንዳለፈው አመት (1990) ሁሉ በዚህም አመት አንድ ክለብ (ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ) ወርዶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ እና አዳማ ከተማ ሲያድጉ የተሳታፊዎች ቁጥርም ለቀጣዩ አመት ወደ 12 ከፍ ተደረገ፡፡ 


1992 

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዲስ የሊግ እርከን አስተዋወቀ፡፡ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ወደ 3ኛ እርከን ወርዶ 2ኛ እርከን ላይ አዲስ ሊግ ተቋቋመ፡፡ ቀድሞ ብሔራዊ ሊግ ይባል የነበረው ዋናው ሊግ ስሙን ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲቀይር ሁለተኛው እርከን ደግሞ ብሔራዊ ሊግ ተባለ፡፡ በብሔራዊ ሊጉ የመጀመርያ 5 አመታት ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያልፉ ክለቦች ላይ በአስገራሚ ሁኔታ ገደብ ይደረግ ነበር፡፡ ከአንድ ክልል/ከተማ አስተዳድርም ከአንድ ክለብ በላይ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዳያልፍ የሚል የኮታ ህግ የእርከኑ አካል ነበር፡፡ የኮታ ህጉ በ1997 ሲሻር የእርከን ተዋረዱ ግን እስከ 2007 የውድድር ዘመን ድረስ ዘለቀ፡፡ በዚህ አመት (1992) እንደቀደመው አመት ሁሉ የአስራት ኃይሌው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳይቸገር ዋንጫውን አነሳ፡፡ 


1993

በዚህ የውድድር ዘመን የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 14 ከፍ ተደርጎ ተካሄደ፡፡ በሀገራችን አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ኢትዮጵያ ወደ ግማሽ ፍፃሜው በመሸጋገር ለመጀመርያ ጊዜ በአለም ወጣቶች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ መሆኗን ተከትሎ ይህ የውድድር አመት የኢትዮጵያ እግርኳስ የተነቃቃበት ወቅት ነበር፡፡ ለወጣት ብሔራዊ ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾች ያስመረጠው መብራት ኃይል (ኤሌክትሪክ) እና አጥቂው ዮርዳኖስ አባይ ድንቅ አመት አሳልፈው በሁለትዮሽ ድል የውድድር ዘመኑን ዘጉ፡፡ ዮርዳኖስ አባይም 24 ግቦች በማስቆጠር ለቀጣዮቹ 16 አመታት የዘለቀ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል የማስቆጠር ሪኮርድ ጨበጠ፡፡     


1994

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1993 በኤሌክትሪክ የተነጠቀውን ቻምፒዮንነት ሲያስመልስ የመዝጊያው ጨዋታ ጥያቄዎችን ያጫረ ክስተት አስተናገደ፡፡ የምድር ባቡሩ አህመድ ጁንዲ በ18 ጎሎች የሊጉን ግብ አስቆጣሪነት ሲመራ ዮርዳኖስ አባይ በ16 ግቦች እየተከተለው ነበር፡፡ በመጨረሻው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤሌክትሪክ አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት እና በቅዱስ ጊዮርጊስ 8-5 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ዮርዳኖስ አባይ 4 ጎሎችን አስቆጥሮ የግብ መጠኑን 20 ሲያደርስ አህመድ ጁንዲ ደግሞ ምድር ባቡርን ከትራንስ ኢትዮጵያ ባደረጉት ጨዋታ አንድ ግብ ቢያስቆጥርም በዮርዳኖስ የተበለጠበት ክስተት አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ ዮርዳኖስ ሆን ተብሎ ተለቆለት ነው በሚሉ እና በወቅቱ የተዋጣለት ግብ አስቆጣሪ እንደመሆኑ 4 ጎሎች ማስቆጠር አይሳነውም በሚሉ ሁለት ጎራዎች መካከል ክርክር አስነስቶ ነበር፡፡    


1995

አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ በአስደናቂ ግስጋሴ ሳይታሰብ ወደ ቻምፒዮንነቱ ተጠጋ፡፡ የአሰልጣኝ መለሰ ሸመና ቡድን ቻምፒዮን በመሆን የመጀመርያው የክልል ክለብ ለመሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻው የኢትዮጵያ ቡና የደርቢ ጨዋታ ነጥብ መጣል ይጠበቅበት በመሆኑ ውጥረት ነገሰ፡፡ ሐምሌ 10 ቀን 1995 የተደረገው የመጨረሻ ጨዋታ እስከ ጭማሪው ደቂቃ ድረስ 1-1 የነበረ ሲሆን አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎችም የመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አካል ነበሩ፡፡ በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሽርፍራፊ ሰኮንዶች በቀሩበት ሰአት ኬንያዊው ኤሪክ ሙራንዳ ባስቆጠረው ጎል 2-1 አሸንፎ ሊያጣው የተቃረበውን ዋንጫ ከአርባምንጭ አፍ ነጠቀ፡፡  

በዚሁ አመት በኢትዮጵያ ቡናው ካሳዬ አራጌ ምክንያት የኢትዮጵያ እግርኳስ መነጋገርያ የሆነበት አመት ነበር፡፡ በወቅቱ የ”ጂኬ ፍልስፍና” ን በኢትዮጵያ ቡና ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ ሊጉ ‹‹ኢትዮጵያ ቡና እና ሌሎች 13 ክለቦች›› የሚል መጠርያ እስከማግኘት ደረሰ፡፡ ክለቡ በወቅቱ ለነበረው የደጋፊ ቁጥር መብዛት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የካሳዬ ፍልስፍና ሲሆን ክለቡ ያስመዘገበው ከፍተኛ የሜዳ ገቢም ይህንን የሚያረጋግጥ ነበር፡፡ ሆኖም ቡና በ1996 መጀመርያ በተደረገው የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በቅዱስ ጊዮርጊስ በደርሶ መልስ 6-0 መሸነፉ አሰልጣኝ ካሳዬን ጫና ውስጥ ከቶት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ተሰናበተ፡፡ 


1996

‹‹የእግርኳሱን ፉክክር ለማመጣጠን›› ተብሎ የተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አላማውን ያሳካው ዘግይቶ በ1996 ነበር፡፡ ሀዋሳ ከተማም ሊጉን ለመጀመርያ ጊዜ በማሸነፍ ታሪክ አስመዘገበ፡፡ በውድድር አመቱ ኢትዮጵያ ቡና ረጅም ጉዞ ማድረግ ቢችልም በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በውስጥ ውዝግቦች ታምሶ ዋንጫውን ለሀዋሳ ከተማ አሳልፎ ሰጠ፡፡ ቡና በወቅቱ በሰንጠረዡ አናት ላይ ተቀምጦ አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻን ማሰናበቱ መነጋገርያ ሆኖ ነበር፡፡ የቻምፒዮንነት ፉክክሩ እስከ መጨረሻው ሳምንት በመዝለቁ ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ላይ ሁለት ዋንጫዎች ተዘጋጁ፡፡ የከማል አህመዱ ሀዋሳ ከተማ የራሱን እድል በራሱ ተጠቅሞ ኒያላን 3-1 በመርታት ዋንጫውን ከፍ ሲያደርግ ቻምፒዮንነታቸው በሀዋሳ መሸነፍ ላይ ተንጠልጥሎ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና እና ትራንስ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ ተጋጣሚዎቻቸውን ቢያሸንፉም በሀዋሳ ማሸነፍ ምክንያት ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡


1997    

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ1996ቱ ደካማ የውድድር አመት በኋላ በአሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ‹‹ሚቾ›› መሪነት ጠንካራ ቡድን በመገንባት 2ኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀው ትራንስ ኢትዮጵያ በ18 ነጥቦች ርቆ ቻምፒዮን በመሆን አጠናቀቀ፡፡ በዚህ የውድድር ዘመን የመዝጊያው ስነስርአት እንደቀደሙት አመታት ክቡር ትሪቡን ላይ ከተቀመጡ የክብር እንግዶች ዋንጫ በመቀበል አልነበረም የተደረገው፡፡ ይልቁኑም ክለቡ ባዘጋጀው መድረክ እና ባለቀለም ወረቀቶችን በሚበትኑ ማሽኖች አማካኝነት ሜዳው ላይ በተደረገ ስነስርአት ነበር ፍፃሜው የተከናወነው፡፡      


1998 – 2000 የእብደት አመታት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንደ 1998ቱ የውድድር አመት እጅግ አስቀያሚውን አመት አሳልፎ አያውቅም፡፡ በሰኔ ወር 1995 በፊፋ እውቅና ባልተሰጠው ጠቅላላ ጉባኤ ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ በፊፋ ጣልቃ ገብነት በድጋሚ በተደረገ ምርጫ በ1997 መጨረሻ ወደ ፕሬዝዳንትነት በተመለሱት ዶ/ር አሸብር የሚመራው አዲሱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሊጉን ተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 16 ከፍ ለማድረግ ወሰነ፡፡ በወቅቱ ፕሬዝዳንቱ የተሳታፊዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ እንዲል እና በሁለት ዞኖች ተከፍሎ የማድረግ እቅድ ፌዴሬሽኑ እንዳለው ገልፀው ነበር፡፡ ሆኖም በ1997 ውድድር 14ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ በመፍረሱ ውድድሩ በ15 ክለቦች መካከል ተካሄደ፡፡  

በየሳምንቱ አንድ ቡድን አራፊ በሚሆንበት በዚህ የውድድር ዘመን ካለፉት አመታት በባሰ መልኩ ስርአት አልበኝነት የሰፈነበት፣ ውድድሮች የሚቆራረጡበት እና አሳማኝ ያልሆኑ ውሳኔዎች የበዙበት አመት ሆኖ ተጠናቀቀ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ቡና እና ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ የገቡበት አመት ሆኖ አልፏል፡፡ በየካቲት ወር በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ዳንኤል ተክሉ በፍቅሩ ተፈራ ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ መሰናበቱን ተከትሎ በካታንጋ በተከሰተ ብጥብጥ ጨዋታው ተቋረጠ፡፡ ኢትዮጵያ ቡናም ጥፋተኛ ተደርጎ ቅጣት ሲጣልበት ክለቡ ቅጣቱ አግባብ እንዳልሆነ በመግለፅ ይግባኝ ጠየቀ፡፡ ሆኖም ይግባኙ ታይቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የሚደረገው ጨዋታን ‹‹እንዳታደርጉ›› ብሎ ለክለቦቹ በደብዳቤ በመግለፁ ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታውን ሳያደርግ ቢቀርም ፎርፌ ተሰጠበት፡፡ ፌዴሬሽኑ በወቅቱ ለፎርፌ ውሳኔው የሰጠው ምክንያትም ጨዋታውን ‹‹እንድታደርጉ›› ነው ያልኩት የሚል ነበር፡፡ ይህ አስገራሚ የፊደል ግድፈት በቡና እና ፌዴሬሽኑ መካከል የነበረውን ልዩነት ይበልጥ አሰፋው፡፡ ቀጥሎ ግንቦት ወር ላይ ከመከላከያ ጋር በተደረገው ጨዋታ ደብሮም ሀጎስ ያስቆጠረው ጎል ሳይፀድቅ ሲቀር ከሚስማር ተራ ደጋፊዎች አጥር ዘለው መግባታቸውና የቡና ተጫዋቾችም ጨዋታውን አቋርጠው መውጣታቸውን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ቡናን ከውድድር አግዶ ብዙም ሳይቆይ ጥፋተኛ ያላቸውን በመቅጣት ወደ ውድድር እንዲመለስ አደረገ፡፡ በውድድር አመቱ መጨረሻ ደግሞ አጥቂው ታፈሰ ተስፋዬ 21 ጎል አስቆጥሮ በአመዘጋገብ ስህተት የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብሩ ለበረከት አዲሱ በመሰጠቱ ደጋፊዎች ቁጣቸውን ገለፁ፡፡ ለተጫዋቹ በግላቸው ያዘጋጁትን ሽልማትም አበረከቱ፡፡ 

ከኢትዮጵያ ቡና በተጨማሪ ወንጂ ስኳር በሁለተኛው ዙር በሜዳው በተፈጠረ ስርአት አልበኝነት ከሊጉ እንዲሰናበት ተደርጎ በቀጣይ ሳምንታት ከወንጂ ጋር ጨዋታ የሚያደርጉ ክለቦች በሙሉ ፎርፌ እዲሰጣቸው ተወሰነ፡፡ 

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሰኔ 15 የተጠናቀቀው ሊግን ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሸናፊነት ቢፈፅምም የክለቡ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል ጭምር ያልተገኙበት ቀዝቃዛ የመዝጊያ ስነስርአት ተካሄደ፡፡ ከመዝጊያው እለት ቀደም ብሎም ኢትዮጵያ ቡና በይፋዊ መግለጫ የቅዱስ ጊዮርጊስን የፕሪምየር ሊግ አሸናፊነት እውቅና እንደማይሰጠው አስታወቀ፡፡

በ1999 የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 16 አደገ፡፡ እስከ ሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታዎች ድረስም በመርሀ ግብሩ መሰረት ተካሄደ፡፡ ሆኖም ክለቦች ከፌዴሬሽኑ ጋር የፈጠሩት ውዝግብ ቀስ በቀስ ወደ መካረር አምርቶ 10 ክለቦች ሊጉን 21ኛው ሳምንት ላይ አቋርጠው ወጡ፡፡ ኢትዮጵያ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ለምታደርገው የ2008 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ዝግጅት የፕሪምየር ሊጉ ለአንድ ወር መቋረጥ ነበር የውዝግቡ መነሻ፡፡ 10 ክለቦች (በተለይ የአዲስ አበባ ክለቦች) በጀታችው እስከ 30 ድረስ ብቻ የሚቆይ በመሆኑ እንዳይቋረጥ ቢጠይቁም ፌዴሬሽኑ አሻፈረኝ በማለቱ ውዝግቡ እያየለ መጥቶ በ6 ክለቦች ብቻ ተካሂዶ በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ በወቅቱ ባላንጣዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በአንድ ጉዳይ ላይ ተስማምተው አቋም መያዛቸው እና በአንድ ጠረጴዛ ቁጭ ብለው መምከራቸው አጀብ አሰኘ። 

የ1999 ውዝግብ ሊጉን ቅጥ ቢያሳጣውም በእግርኳሱ ተስፋ የፈነጠቀ ነበር። ክለቦች ሊጉን ራሳቸው ለማስተዳደር መጠየቃቸው በራሱ ለለውጡ ትልቅ እርምጃ ነበር። አሁን ድረስ መቋቋም ያልቻለው የክለቦች የሊግ አስተዳደር በወቅቱ ሊፈጠር እንደሚችል ፍንጭ የሰጠበት ሆኖም ነበር፡፡ በመስከረም ወር 2000 ላይ ከሊጉ አቋርጠው የወጡ ክለቦች ከብሔራዊ ሊጉ ተጨማሪ ክለቦችን አካተው በአበበ ቢቂላ ስታድየም የክለቦች ህብረት ዋንጫ በሚል ውድድር አዘጋጁ፡፡ ይህም ክለቦች ራሳቸው የሚያስተዳድሩትን ሊግ ለማቋቋም እንደቆረጡ የሚያሳይ ነበር፡፡ በውድድሩ መክፈቻ ስነስርአት ላይ የአስከሬን ሳጥን በሜዳው ዙርያ ይዞ የመዞር ትርኢትም ‹‹የእግርኳሳችንን መሞት›› መርዶ የተነገረበት የወቅቱ መነጋገርያ ክስተት ሆነ፡፡   

ሆኖም ውዝግቦች እልባት እያገኙ ሲመጡ የኢትዮጵያ እግርኳስም ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ። ክለቦች ያኔ ውድድር እስከማቋረጥ ያደረሰ ውዝግብ ውስጥ ገብተው የነበረው ለምን እንደሆነ አሁን ላይ ሆነን ስንመለከተው ግራ አጋቢ ነው።

በ2000 የውድድር አመት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በ1999 ሊግ ላይ የነበሩት እና ውድድሩን ሳያቋርጡ የቀጠሉት 6 ክለቦችን እንዲሁም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደጉትን ክለቦችን ጨምሮ ጥለው በወጡት ክለቦች ምትክ ከብሔራዊ ሊጉ 8 አዳዲስ ክለቦችን በመጨመር የአዲሱን ሚሌንየም ውድድር ጀመረ፡፡ ውድድሩ በዚህ መልኩ ቀጥሎ በጥር ወር በፊፋ እውቅና ያልተሰጠው ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ከስልጣን በማንሳት አቶ አህመድ ያሲንን በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት ሾመ፡፡ የሹም ሽሩን ተከትሎ ከፌዴሬሽኑ ጋር በፈጠሩት የከረረ ውዝግብ ከሊጉ ተነጥለው የክለቦች ህብረት በማቋቋም የራሳቸው ውድድር ያካሄዱት 11 ክለቦች በአዲሱ የአቶ አህመድ ያሲን አመራር አማካኝነት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመለሱ፡፡ ሆኖም በየካቲት ወር 2000 ኢትዮጵያ በፊፋ ከማንኛውም የኢንተርናሽናል እግርኳስ እንቅስቃሴ  ታገደች፡፡ 

በ1999 አቋርጠው የወጡት ክለቦች በመመለሳቸው የተሳታፊዎች ቁጥር ቀድመው ውድድር ከጀመሩት ጋር ተደምሮ 25 ደረሰ፡፡ የውድድሩ አካሄድ በአዲስ መልክ ተከልሶ በአንድ ዙር ውድድር ብቻ እንዲደረግ ተወስኖ 14 ክለቦች ሲቀሩ ሌሎቹ ወደ ብሔራዊ ሊግ ወረዱ፡፡ በአዲሱ ሚሌንየም የተካሄደው ይህ ውድድር የለውጥ ጭላንጭል በታየበት ወቅት እንደመካሄዱ ከ1990ዎቹ አጋማሽ በኋላ እየጠፋ የነበረው ተመልካችን ወደ ሜዳ የመለሰ ከመሆኑ ባሻገር በሚድሮክ ግሩፕ በ1.5 ሚልዮን ብር ስፖንሰር ተደርጎ ለመጀመርያ ጊዜ የስያሜ መብቱን ሸጠ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ የሊጉን ዋንጫ ከፍ ሲያደርግ ሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ወደ ሊጉ ለ2001 አደጉ፡፡


2001

የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ትኩሳት እስከ 2001 መጨረሻ ድረስ ሳይበርድ ዘልቆ ፊፋ ባስቀመጠው ፍኖተ ካርታ መሰረት በሐምሌ ወር 2001 በተደረገ ጠቅላላ ጉባዔ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ከስልጣናቸው ራሳቸውን ማንሳታቸውን በመግለጽ አዲስ ምርጫ ተካሂዶ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ አዲሱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆኑ፡፡ የፊፋ እገዳ ሲነሳ አንፃራዊ ሰላምም በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ሰፈነ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከፌዴሬሽኑ ጥላ የማላቀቅ ‹‹ትግል›› ኢላማውን ሳይመታ ጉዞውን ቀጠለ፡፡


2002 

የደደቢት መምጣት የሊጉን መልክ ቀየረው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሁነኛ ተፎካካሪ ሆኖም ብቅ አለ፡፡ በሀገሪቱ ሚሌንየሙን ተከትሎ የመጣው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በደደቢት አጋፋሪነት በእግርኳሱም ዘልቆ ገባ፡፡ ደደቢት በወቅቱ ቡድኑን በሀገሪቱ ምርጥ ተጫዋቾች ሲሞላ የፊርማ ክፍያ ሪኮርዶችን በመሰባበር ነበር፡፡ ሆኖም ደደቢት በወቅቱ የመጣበት መንገድ ጥያቄዎች ያስነሳ ሆነ፡፡ ከብሔራዊ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚድጉት ክለቦች 2 እንደሆኑ ቀደም ብሎ ተነግሮ ሲዳማ ቡና እና ሜታ አቦ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ቢያድጉም ደደቢት የውድድር አመቱ መጀመርያ ላይ የተነገረን ምድባቸውን በመሪነት ያጠናቀቁ ክለቦች ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያድጋሉ ተብሎ ነው በሚል ባነሳው ጥያቄ ከወረዱት ክለቦች ጋር የመለያ ጨዋታ በማድረግ ትራንስ ኢትዮጵያ በሊጉ ሲቆይ ደደቢት 3ኛ ቡድን ሆኖ ወደ ሊጉ አደገ፡፡ ሊጉም በ18 ክለቦች መካሄዱን ተከትሎ በታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጨዋታ (306) ተካሂዶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታዩ ደደቢትን በ24 ነጥቦች በመብለጥ በ84 ነጥቦች ቻምፒዮን ሲሆን 4 ክለቦች ወረዱ፡፡ በወቅቱ ላለመውረድ የነበረው ትንቅንቅ ልብ አንጠልጣይ የነበረ ሲሆን በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላለመውረድ የአቻ ውጤት ይበቃው የነበረው ኢትዮጵያ መድን በሀዋሳ 2-1 ሲሸነፍ መከላከያን 4-0 የረታው ኤሌክትሪክ በግብ ልዩነቶች በመብለጥ ለጥቂት ከመውረድ ተረፈ፡፡


2003

በ16 ክለቦች መካከል በተደረገው የዚህ የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ቡና ከ13 አመታት ጥበቃ በኋላ የመጀመርያ የሊግ ቻምፒዮን መሆን ፕሪምየር ሊጉን የትኩረት ማዕከል አደረገው፡፡ በወቅቱ ሊጉ የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ያገኘበትም ነበር፡፡ ከ1996 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ እስከ መጨረሻው ሳምንት የዘለቀው የቻምፒዮንነት ፉክክር ኢትዮጵያ ቡና ሙገር ሲሚንቶን 2-0 በማሸነፍ በአሸናፊነት ደመደመ፡፡ 


2004

እንደሌሎች አመታት ሁሉ የሊግ ክብሩን ባጣ በቀጣዩ አመት ተጠናክሮ ብቅ የሚለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቻምፒዮንነቱን የግሉ አደረገ፡፡ ይህ ዋንጫ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከ1990 በኋላ የተመዘገበ 10ኛ ድል ሆኗል፡፡


2005

በ2005 ኢትዮጵያ 31 አመት ወደራቀችበት የአፍሪካ ዋንጫ ተመለሰች፡፡ በሀገሪቱ የነገሰው ቅጥ ያጣ የደስታ ስሜትም የፕሪምየር ሊጉን ውድድር አደበዘዘው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – መለስ ዋንጫ›› በሚል ስያሜ የተደረገው ውድድር በአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት ምክንያት በተደጋጋሚ እየተቋረጠ ቆይቶ ከአፍሪካ ዋንጫው በኋላ ቀጥሎ ደደቢት አዲሱ የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ሆነ፡፡ ደደቢት በሊጉ የቆየባቸው አመታት ጥቂት ቢሆኑም በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ተፅእኖ ፈጣሪ መሆን ሊጉን ያነቃቃው መሰለ፡፡ ሆኖም ክለቡ ከ2005 በኋላ ባሉት አመታት ዝውውር ላይ እየተቀዛቀዘ በመምጣት የሊግ ድሉን በድጋሚ ማጣጣም ሳይችል ቀርቷል፡፡ 


2006

በ2006 መስከረም ወር ላይ በተካሄደ ምርጫ አቶ ጁነይዲ ባሻ ወደ ፕሬዝዳንነት ስልጣን መጡ፡፡ የቀድሞው የሐረር ቢራ ክለብ ስራ አስኪያጅ በሊጉ ብሎም በእግርኳሱ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ባለፉት 4 አመታት የሊጉ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ያሽቆለቆለበትን ጊዜ አሳልፏል፡፡ በ2005 ክብሩን ያጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥቂት ጠንካራ ዝውውሮችን በመፈፀም በዚህ አመት ወደ ቻምፒዮንነቱ ተመልሷል፡፡


2007

ከ1991 ጀምሮ በሚያሳድጋቸው ወጣት ተጫዋቾች በመጠቀም ቢያንስ በሰንጠረዡ ወገብ ላይ ሲያጠናቅቅ የቆየው ሙገር ሲሚንቶ ወደ ከፍተኛ ሊግ ወረደ፡፡ ከሙገር ጋር ባለመውረድ ትንቅንቅ ውስጥ የነበረው ኤሌክትሪክ ሀዋሳ ከተማን 6-0 ያሸነፈበት ጨዋታ ከውድድር ዘመኑ የኤሌክትሪክ ደካማ አቋም እና ከጎሉ መብዛት ጋር ተደማምሮ በስፖርት ቤተሰቡ በጥርጣሬ የታየ ሆኖ አለፈ፡፡ ሙገር ከአንድ አመት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ እጣ ፈንታው መፍረስ ሆኗል ።2008
 

እግርኳሱ አንድ እርከን ተጨመረለት፡፡ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከፕሪምየር ሊጉ በታች የሚገኝ ሊግ እንዲሆን በመወሰኑ ከዚህ ቀደም እንደዋዛ ይገባበት የነበረውን ፕሪምየር ሊግ መቀላቀል ይበልጥ አከበደው፡፡ በከፍተኛ ሊጉ የሚደረጉ ጨዋታዎች ብዛት እና ለጉዞ የሚወጣው ወጪ ከፕሪምየር ሊጉ ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደጉ ክለቦች አቅማቸውን በከፍተኛ ሊጉ አሟጠው በመምጣት ለፕሪምየር ሊጉ ዝግጁ እንዳይሆኑ ማድረጉ ውድድሩን በሚያማርሩ ወገኖች በኩል ሲደመጥ ሊጉ ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት በመሆኑ ክለቦች ለፕሪምየር ሊግ ፉክክር ተዘጋጅተው እንዲመጡ ያደርጋቸዋል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ 

በዚህ አመት ዳሽን ቢራ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን ተከትሎ ፈረሰ፡፡ ክለቡ በወቅቱ ለመፍረሱ ምክንያት ያደረገው በሊጉ ሁለተኛ ዙር በኢትዮጵያ ቡና 2-0 በተሸነፉበት ጨዋታ ቡና ያልተገባ ተጫዋች ተጠቅሟል በሚል ያቀረቡት ጥያቄ በፌዴሬሽኑ ችላ ተብሏል የሚል ነበር፡፡ 


2009 

ከአራት የውድድር አመታት በኋላ ወደ 16 ተሳታፊዎች የተመለሰውን ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለ4ኛ ተከታታይ ጊዜ ነገሰበት፡፡ ክለቡ በታሪኩ አሳክቶት የማያውቀውን 4 ተከታታይ የሊግ ድል ማሳካት ሲችል ጦር ሰራዊት ከ1943-46 በተከታታይ 4 አመታት ካሸነፈ በኋላ የመጀመርያው ሆነ፡፡ ቡድኑ በተለይ በመጨረሻዎቹ ሶስት የውድድር ዘመናት እንደ ቻምፒዮን ቡድን ሲታይ ደካማ የውድድር ዘመን ያሳለፈበት መሆኑና ጥሩ ካልሆነ አጀማመር በኋላ በመጨረሻ ዋንጫውን የሚያነሳበት መንገድ ሌሎች ክለቦች አመቱን ሙሉ ምንድነው የሚሰሩት ያስባለ ነበር፡፡ 

በዚሁ አመት ጌታነህ ከበደ 25 ጎሎችን በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ክብር ለ3ኛ ጊዜ ሲያሸንፍ ዮርዳኖስ አባይ ለ16 የውድድር ዘመናት ይዞት የቆየውን በአንድ አመት በርካታ ጎል የማስቆጠር ሪኮርድ ማሻሻል ችሏል፡፡ ጌታነህ በመጨረሻ ጨዋታ ሁለት ግብ ወላይታ ድቻ ላይ ያስቆጠረበት መንገድ በ1994 ዮርዳኖስ ላይ እንደተከሰተው ሁሉ ጥርጣሬዎች ያጠሉበት ነበር፡፡

ሁልጊዜም ጥያቄ የሚነሳበት ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር በዚህ አመት ወደ ከፍተና ደረጃ ተሸጋገረ፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሀዋሳ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ የመላቀቅ ሙከራ ተደርጓል በሚል ሀዋሳ ከተማ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ጅማ አባ ቡና ክስ በማቅረብ ለ4 ወራት ጉዳዩ ታይቶ ፌዴሬሽኑም ሆነ የአቃቤ ህግ ክሱን ውድቅ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ 

ከ1992 ጀምሮ በሊጉ የቆየው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፈረሰውም በዚህ አመት ነበር። 


ይቀጥላል…

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን 20ኛ አመት በማስመልከት የምናቀርባቸው ፅሁፎች በቀጣይ ክፍሎችም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይቀጥላል፡፡ በፅሁፎቹ ላይ ያላችሁን አስተያየት እና ዕርምትም ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡


–  ተጨማሪ የመረጃ ምንጮች: ሊብሮ ፣ አቴና ፣ ኢትዮ ስፖርት ፣ ኢንተር ስፖርት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *