​ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ 0-0 ደደቢት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር የሊግ አራተኛ ሳምንት ድሬዳዋ ላይ ደደቢትን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታውን ያለግብ አጠናቋል።

ወደ ወልድያ አቅንቶ ያለግብ አቻ ተለያይቶ በተመለሰው ድሬዳዋ ከተማ እና በሜዳው በሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስቶ አሸንፎ መውጣት በቻለው ደደቢት መካከል የተደረገው የዛሬው ጨዋታ እምብዛም የጎል ሙከራ ያልተደረገበት እና ጥንቃቄን መሰረት ባደረገ እንቅስቃሴ ደጋፊው ተሰላችቶ የወጣበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል።

በጌታነህ ከበደ አማካኝነት በተጀመረው የመጀመርያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 15ቱን ደቂቃ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጭነው የተጫወቱት ባለ ሜዳዎቹ ድሬዎች የጎል ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ ነበሩ። በዘንድሮ አመት የድሬዳዋ የማጥቃት ምንጭ የሆነው የመስመር ተከላካዩ ዘነበ ከበደ በቀኝ መስመር  ሰብሮ በመግባት ያሻገረውን ኳስ 1ኛው ደቂቃ ላይ አትራም ኩዋሜ መትቶ ለጥቂት በጎሉ ጠርዝ የወጣበት ኳስ  የመጀመርያው የጨዋታው ሙከራ ነበር። በዚህ የጎል ሙከራ የተነቃቁት ድሬዎች በደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ ታጅበው በተደጋጋሚ የደደቢትን የግብ ክልል የፈተሹ ሲሆን በ5ኘመው ደቂቃ ወጣቱ ያሬድ ታደሰ የአስራት መገርሳን ስህተት ተጠቅሞ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ሌላው ጠንካራ የጎል ሙከራ ነበር። 

ከ10 ኛው ደቂቃ በኋላ ጨዋታው ሰቢ ከሆነ ፈጣን እንቅስቃሴ ወጥቶ በመሀል ሜዳ እና በራስ የግብ ክልል የሚንሸራሸሩ ኳሶች ወደበዙበት እንቅስቃሴ ተቀይሯል። 15ኛው ደቂቃ ላይ ደደቢቶች በአምበላቸው ብርሀኑ ቦጋለ አማካኝነት ለዕለቱ ዳኛ ወልዴ ንዳ የክስ ሪዘርቭ ያስያዙ ሲሆን ምክንያታቸው በአንድ ጨዋታ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከሦስት በላይ የውጭ ተጨዋቾችን ተጠቅሟል ፤ ይህ ደግሞ የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተጨዋቾች ተገቢነት ደንብን ይጣረሳል የሚል ነበር። 

ጨዋታው ከክሱ ቀጥሎ ሲካሄድ የተቀሩት 30 ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው እንደሚጫወት ቡድን የማጥቃት እንቅስቃሴ ከማሳየት ይልቅ በአንድ አጥቂ እየተጫወተ ጥንቃቄን መምረጡ ለደደቢት ተከላካዮች ምቾት ሲሰጥ ደደቢት በአንፃሩ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ጌታነህ ከበደ ፣ አቤል ያለው ፣ ሽመክት ጉግሳ እና ኤፍሬም አሻሞ ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉትን ጥረት በተደራጀው የድሬዳዋ የተከላካይ መስመር ክፍተት በማጣት ሲቸገሩ ተስተውሏል። 

የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ ሲቀረው 41ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳንኤል በግራ መስመር ከመሀል ሜዳ ጀምሮ ቆርጦ በመግባት መሬት ለመሬት ወደ ጎል ያሻገረውን ኳስ የደደቢቱ ተከላካይ ከድር ኩሊባሊ ተንሸራቶ ወደ ውጭ ለማውጣት ብሎ የመታው ኳስ ወደ ራሱ ግብ አምርቶ ግብ ጠባቂው አማራህ ክሌመንት እንደምንም ተወርውሮ ያወጣው አጋጣሚ ፣ 45ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳንኤል የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ አቤል ያለው ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አገባው ሲባል ሳምሶን ያዳነበት እና የተተመለሰውን እንደገና መትቶ የተመለሰበት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሁለተም በኩል የተገኙ ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎች ነበሩ። 

ከእረፍት መልስ በተመሳሳይ መልኩ ትርጉም የሌለው የጨዋታ እንቅስቃሴ አሰልቺ በሆነ መንገድ የተመለከትንበት ነበር። እስከ 65ኛው ደቂቃ ድረስ የጨዋታው አካል የነበረው የተጨዋቾች ቅያሪ የተመለከትንበት ከመሆኑ በላይ የሚጠቀስ ነገር አልነበረም። ተመልካቹም በድሬዳዋ እንቅስቃሴም ሆነ በጨዋታው ደስተኛ ባለመሆኑ አቋርጦ ከሜዳ መውጣት የጀመረ ሲሆን በሁለት የተከላካይ አማካይ የገቡት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አጥቂው ዘካርያስ ፍቅሬን ቀይረው ካስገቡበት ደቂቃ ጀምሮ የተሻለ በሚባል መልኩ ወደ ጎል በተደጋጋሚ መቅረብ ሲችሉ ተስተውሏል። ሆኖም አናጋው ባደግ 83ኛው ደቂቃ ላይ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ከውሳኔ ችግር የተነሳ ተከላካዮች በፍጥነት ደርሰው ያዳኑት የሁለተኛው አጋማሽ ብቸኛ ተጠቃሽ የጎል አጋጣሚ ነበር። 

ከ75ኛው ደቂቃ በኋላ የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የታክቲክ ለውጥ አድርገው በሁለት አጥቂ መጫወት ከጀመሩበት አንስቶ ባለሜዳዎቹ ድሬዎች ያደረጉት የማጥቃት ጫና ለምን ከመጀመርያው ጀምሮ አልሆነም በማለት በስታድየሙ የነበሩ የክለቡ ደጋፊዎች ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ሰምተናል።

ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ደደቢት በ6 ነጥቦች በሊጉ መሪነት ሲቀጥል ሁለት ተከታታይ አቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ድሬዳዋ ከተማ በ5 ነጥብ ተከታዩን ደረጃ ይዟል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ዘላለም ሽፈራው – ድሬዳዋ ከተማ

” የዛሬው ጨዋታ ይዘነው ወደ ሜዳ የገባነው አቀራረብ ተጭኖ በመጫወት ጎል ለማስቆጠር ነበር። ያንንም ሜዳ ላይ ተግብረናል። ያገኘነውን አጋጣሚ አለመጠቀማችን ድክመት ነበር። በተለይ የመስመር ተጨዋቾቼ የሚያገኙትን ኳስ በሚገባ አለመጠቀማቸው እንደ ድክመት እወስደዋለው። ተጫዋቾቼ ግን ሜዳ ውስጥ የሚችሉትን አድርገዋል። በእነሱ የማቀርበው ቅሬታ የለም።

” ድሬዳዋ በሜዳውም ከሜዳው ውጭ ባመዛኙ መከላከልን እና ጥንቃቄን መሰረት ያደረገ አጨዋወት ይከተላል ይባላል። እኔ በዚህ አባባል አልስማማም። ዛሬ ያያችሁት ጨዋታ ይሄን አያሳይም። እንዲህ ሲባል ማሳያዎች ሊኖሩ ይገባል። ታክቲካል የሆኑ ነገሮች ያስፈልጋሉ። እንዲሁ ቡድንህን ክፍት አድርገህ አታጋልጥም። ዛሬ ከወትሮ በተሻለ በከፍተኛ ሁኔታ አጥቅተናል። አጋጣሚን ያመጠቀም ድክመት ነው። ስለዚህ የድሬደዋ ከተማ ቡድን አጨዋወት በመከላከል ላይ ያተኮረነው ሊባል አይችልም። ”

ንጉሴ ደስታ – ደደቢት

“ወደ ድሬዳዋ የመጣነው ሦስት ነጥብ ለመውሰድ ነበር። ለዚህም እንዲረዳን ወደ ሜዳ ይዘነው የገባነው አጨዋወት ይህን ያሳያል። ሆኖም ተጋጣሚያችን ይዞት የገባው ጠጣር የሆነው የመከላከል ባህሪ ያለው አጨዋወት እንደፈለግነው ይዘነው የመጣነውን አጨዋወት እንዳንተገብር አድርጎናል።

” የፌዴሬሽኑ ህግ በአንድ ጨዋታ ሦስት የውጭ ተጨዋቾችን ነው እንድንጫወት ያዘዘው። ለዛ ነው ሦስት ተጨዋቾችን በዘጠና ደቂቃ ላይ የምንጠቀመው። ዛሬ ግን እንደምታየነውዩት አራት የውጭ ተጨዋቾችን ተጠቅመዋል። እኛ ደግሞ ህጉ ይከበር የተቀየረ ነገር ካለ በደብዳቤ ያሳውቁን ነው ጥያቄያችን። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *