​ሪፖርት | መከላከያ 0-0 አዳማ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በብቸኝነት የተደረገው የመከላከያ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል። 

በተለመደው የ4-4-2 አሰላለፍ ጨዋታውን የጀመረው መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን ከገጠመበት ቡድን ቴዎድሮስ በቀለን በሙሉቀን ደሳለኝ በመተካት ጀምሯል። ወላይታ ድቻን ማሸነፍ ከቻለው ቡድኑ በተለየ ሱሌማን ሀሚድ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና በረከት ደስታን በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ያስገባው አዳማ ከተማ በ 4-2-3-1 አሰላለፍ ሚካኤል ጆርጅን ብቸኛ አጥቂ አርጎ በመጠቀም ነበር ወደሜዳ የገባው።

ጨዋታው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር አመት ከጀመረ ጀምሮ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ከተስተናገዱት ጨዋታዎች ሁሉ እጅግ አሰልቺው ሆኖ አልፏል። የታዩት በጣት የሚቆጠሩ የግብ ሙከራዎችም በብዛት ከግብ ክልሉ እጅግ ርቀው የተደረጉ ነበሩ። በመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሙጂብ ቃሲም እና መስፍን ኪዳኔ ካደረጓቸው የሙከራ ጥረቶች ውጪ ቡድኖቹ ወደ ተቃራኒ ሳጥን ሲቃረቡ አልታዩም። በቀሪውም የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍል 23ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን ደሳለኝ በድንገት ተከላካዮችን አታሎ ወደ አዳማ የግብ ክልል ውስጥ በመግባት ከሞከረው እና ጃኮ ፔንዜ በቀላሉ ካዳነው ኳስ በቀር የታዩት ሙከራዎች ሁሉ ከሳጥን ውጪ የተደረጉ እና ኢላማቸውን ያልጠበቁ ነበሩ።

የተለመደው የመከላከያ የአማካይ ክፍል ችግር ዛሬም ጎልቶ የታየ ሲሆን በሙሉ ጨዋታው አጥቂዎቹ ከአዳማው ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዜ ጋር ፊት ለፊት ሊገናኙ ሚችሉበት ኳስ ከአማካይ ክፍሉ ሲገኝ አልተስተዋለም። አዳማዎችም ቢሆኑ መሀል ሜዳ ላይ የነበራቸውን የቁጥር ብልጫም ሆነ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ምንም ሲፈይዱበት አልታየም። የፊት መስመር ተሰላፊው ሚካኤል ጆርጅም እንደ ብቸኛ አጥቂ ያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ ከጀርባው ለነበሩት የአጥቂ አማካዮችም ሆነ ለራሱ የጠቀመ ሆኖ አልታየም።

በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው ሁሉ አዳማዎች የተሻለ ሲንቀሳቀሱ ቢታዩም አሁንም የመከላከያን የኃላ ክፍል ሰብረው የገቡበት አጋጣሚ አልነበረም። በዚህ ረገድ የተሻለ ሲንቀሳቀስ ያመሸው ሱራፌል ዳኛቸው ያደረጋቸው ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ። ሆኖም እስማኤል ሳንጋሪ በኤፍሬም ዘካሪያስ ተቀይሮ ከወጣ በኃላ ቡድኑ በሜዳ ላይ ያደረገው የተጨዋቾች ሽግሽግ ብልጫ እንዲወሰድበት ምክንያት ሆኖ ነበር። በዚህ ወቅትም መከላከያዎች በአማኑኤል ተሾመ፣ ምንተስኖት ከበደ እና መስፍን ኪዳኔ አማካይነት ከርቀት ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የሁለቱም ቡድን ግብ ጠባቂዎች የሰሯቸውን ስህተቶች እንኳን በአግባቡ የተጠቀመ አጥቂ ሳይኖር ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።

አምና በተመሳሳይ መርሀግብር አዲስ አበባ ላይ ያለግብ ተለያይተው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮም ግብ ባለማስቆጠር ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የጨዋታ ሂደት  አዝናኝ የሚባል ፉክክር ሳያሳዩ መቅረታቸው ለተመልካቹ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነበር። በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሲታዩ ግብ ለማስቆጠር እና ጨዋታውን ለማሸነፍ ፍላጎቱ ያላቸው ሁለት ቡድኖች ተገናኝተው በ90ደቂቃ ውስጥ አንድም ያለቀለት ዕድል ተፈጥሮ አለማየት ሊጉ ያለበትን ደረጃ እና የአሰልጣኞቻችንን የማጥቃት ስትራቴጂዎች ትዝብት ላይ የሚጥል ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *