ባህርዳር ከተማ እና አውስኮድ የዚህ ሳምንት ጨዋታቸውን ጎንደር ላይ ያደርጋሉ

በከፍተኛ ሊጉ የሚካፈሉት ሁለቱ የባህርዳር ክለቦች የሆኑት ባህርዳር ከተማ እና አማራ ውሃ ስራ (አውስኮድ) የምድቡ 3ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን በጎንደሩ ፋሲለደስ ስታድየም ያካሂዳሉ፡፡

የባህርዳር ከተማ የደጋፊዎች ማህበር እንደገለፀው ከሆነ የአፄ ቴዎድሮስ ስታድየም ሜዳው ለጨዋታ አመቺ ባለመሆኑ ምክንያት በእድሳት ላይ የሚገኝ ሲሆን በመጀመርያው ሳምንት አክሱም ከተማን በሳላምላክ ተገኝ ብቸኛ ጎል 1-0 ሲያሸንፍ የተጫወተበት ግዙፉ የባህርዳር አለማቀፍ ስታድየም ደግሞ የጣርያ ማልበስ ስራ እንደሚከናወን በመገለፁ ስራው እስከሚጠናቀቅ ጨዋታ አይደረግበትም፡፡ ማህበሩ በገጹ እንዳሰፈረው ክለቡ ስራ በማይከናወንበት የሜዳ ክፍል ብቻ ደጋፊዎችን ለማስገባት እና ለሚደርሰው ኪሳራ ሁለቱ ክለቦች ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ያቀረበው ጥያቄ በተቋራጩ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ እንደሶስተኛ አማራጭነት የተያዘው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ደግሞ በበጋ ወራት በትምህርት ተቋማት ጨዋታ ማድረግ የማይቻል በመሆኑ በአማራጭነት ለፌዴሬሽኑ ወዳስመዘገበው የፋሲለደስ ስታድየም ተዛውሮ ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ሰአት ክለቡ ለነገው ጨዋታ ወደ ጎንደር እያቀና መሆኑን የሰማን ሲሆን በተመሳሳይ አማራ ውሃ ስራ (አውስኮድ) ዛሬ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በአጼ ፋሲለደስ ስታድየም 09፡0 ላይ የሚያከናውን ይሆናል፡፡

ባህርዳር ከተማ በአጼ ፋሲል ስታድየም ጨዋታ ሲያደርግ ይህ የመጀመርያ አይደለም፡፡ ባለፈው አመት ከአአ ፖሊስ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በዚሁ ስታድየም ማከናወኑ ይታወሳል፡፡

ከስታድየም ጋር በአበበ ቢቂላ ስታድየም እድሳት ምክንያት በተያያዘ የአዲስ አበባ ክለቦችም ችግር ላይ ይገኛሉ፡፡ አአ ከተማ የመድን ሜዳን ምርጫው ሲያደርግ ፣ ፌዴራል ፖሊስ በኦሜድላ ሜዳ ፣ የካ ክፍለከተማ በየካ ሜዳ ፣ ኢኮስኮ ደግሞ የለገጣፎ ሜዳን የሜዳቸው ጨዋታዎችን ለማካሄድ ምርጫቸው ሆኗል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *