አርባምንጭ ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ድል ሲቀናው ድቻ እና ድሬዳዋ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታ አርባምንጭ የውድድር አመቱን የመጀመርያ ሶሰት ነጥብ ሲያስመዘግብ ወላይታ ድቻ ከ ድሬዳዋ ከተማ አቻ ተለያይቷል። የወልዲያ እና መቐለ ከተማ ጨዋታ ደግሞ ሳይደረግ ቀርቷል።

በተከታታይ ጨዋታዎች ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኝት ተስኖት የነበረው አርባምንጭ ከተማ መከላከያን አስተናግዶ 2-0 አሸንፏል። የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ግብ የተጠናቀቀ ሲሆን 62ኛው ደቂቃ ላይ ወንድሜነህ ዘሪሁን ከረጅም ርቀት የመታት ኳስ የግቡን ብረት ገጭታ ስትመለስ ከተስፋ ቡድን ያደገው አጥቂው ብርሀኑ አዳሙ አዞዎቹን ቀዳሚ አድርገዋል፡፡ የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ በግምት 35 ሜትር ርቀት ላይ ፀጋዬ አበራ አክርሮ የመታት ኳስ ከመረብ አርፋ ጨዋታው በአርባምንጭ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኃላ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት “ውጤቱ ይገባን ነበር። በሚያስፈልገን ሰአተ አግኝተናል።” ሲሉ የመከላከያው ምንያምር በበኩላቸው ” እድል ከኛ ጋር አልነበረችም ማሸነፍ ይገባን ነበር” ብለዋል፡፡

ሶዶ ላይ የተገናኙት ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳወች ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ሄይቲያዊው አማካይ ሳውሬል ኦልሪሽ የግብ ጠባቂውን አቋቀም ተመልክቶ ከመሀለኛው የሜዳ ክፍል የላካት ኳስ ከመረብ አርፋ ድሬዎች መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን 43ኛ ደቂቃ ላይ ቶጎዊው አጥቂ ጃኮ አራፋት የጦና ንቦችን አቻ አድርጎ ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር በዚሁ ውጤት ተጠናቋል።

ወልዲያ ላይ ዛሬ ሊደረግ የነበረው የወልዲያ እና መቐለ ከተማ ጨዋታ ከስታድም ውጪ በከተማው መንገዶች በተነሳ ግጭት ምክንያት ሳይደረግ ቀርቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *