” ግብ ማስቆጠሬ የተለየ ስሜት አልፈጠረብኝም”  ኤፍሬም ዘካርያስ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ትላንት አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ አዳማ ከተማ ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። በ19ኛው ደቂቃ ላይ ከሱለይማን መሀመድ የተላከችውን የማዕዘን ምት በግንባሩ ገጭቶ በቀድሞ ክለቡ ላይ በማስቆጠር አዳማ ወሳኝ ሶስት ነጥቦችን እንዲያገኝ ያስቻለው ደግሞ ኤፍሬም ዘካሪያስ ነው። 

በ2009 በበርካታ ውጣ ውረዶች ያሳለፈው ኤፍሬም ከሁለተኛው ዙር ጨምሮ በሀዋሳ ከተማ በተላለፈበት ቅጣት ጨዋታ ማድረግ ያልቻለ ሲሆን በመጨረሻው ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባደረጉት ጨዋታን ውጤት ያለ አግባብ እንዲለወጥ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ተደራድሯል በሚል ክለቡ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ለ4 ወራት የዘለቀ ምርመራ ተደርጎ ነፃ መውጣቱ እና ለአዳማ ከተማ መፈረሙም የሚታወስ ነው።
ኤፍሬም የማሸነፍያዋን ጎል ካስቆጠረበት የትላንቱ ጨዋታ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ጎል የፈጠረበት የተለየ ስሜት እንደሌለ ተናግሯል። ” ጎል ማስቆጠሬ አስደስቶኛል። ነገር ግን እንደ ማንኛውም ጨዋታ ነበር ተመልክቼው የገባሁት። ባለፈው አመት የነበሩ እና እኔን ያልገቡኝ ድርጊቶች ቢኖሩም የተለየ አመለካከት ኖሮኝ ወደ ሜዳ አልገባሁም። በውስጤ ምንም ጥላቻን የሚያሳይ ስሜትም የለኝም። ብቻ እንደ ፈጣሪ ፍቃድ ሆኖ ጎል አግብቻለሁ። በኔ ግብም ቡድኔ አሸናፊ በመሆኑ ደስ ብሎኛል። ግን ማስቆጠሬ እንደተለየ ነገር አልተመለከትኩም። ለኔ እንደ ሌሎች ጊዜያት ላይ እንደማስቆጥረው ጎል ነበር። ” 

የአጥቂ አማካዩ ኤፍሬም በቀዳሚነት ስሙ ሲነሳበት ከነበረው ጉዳይ ነፃ ቢወጣም ከዛ በፊት የነበሩ ጊዜያት ከባድ እና ተስፋ አስቆራጭ እንደነበሩ ገልፆ እግርኳስ ለማቆም እስከማሰብ ደረጃ አድርሶት እንደነበር ይናገራል። ሆኖም ከዚህ በኋላ ስላለፈው ጊዜ ማሰብ እንደማይፈልግም ገልጿል። 

” ሲጀመር እኔ በኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ጨዋታ ያደረኩት ምንም ነገር የለም። ያንንም አሁን ላይ ማሰብ አልፈልግም። ብቻ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደዚህ አይነት ስሜት መመለሴ አስደስቶኛል። ከክለቤ ጋር እንኳን ልምምድ ማድረግ የጀመርኩት ዘግይቼ በመስከረም ወር ነበር። አሁን ከዚ የተሻለ ነገር ማድረግ እፈልጋለሁ። ከአዲሱ ክለቤ ጋር የተሻለ ነገር ለማሳካትም እጥራለሁ።” ብሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *