​የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቅጣት ውሳኔዎች

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በፕሪምየር ሊጉ 3ኛ እና 4ኛ ሳምንት እንዲሁም የአንደኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ላይ በተከሰቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰቶች ጥፋተኛ ያላቸው 4 ክለቦች ፣ አንድ አሰልጣኝ እና 3 ተጫዋቾች ላይ ቅጣት አስተላልፏል።


የተጫዋቾች ቅጣት

በአንደኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና አቻ ሲለያዩ በ89ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣው ትርታዬ ደመቀ 4 ጨዋታ እና 4ሺህ ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

በ4ኛው ሳምንት በተደረገው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ ጨዋታ በ54ኛው ደቂቃ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው አዲስ ነጋሽ ሌላው የ4 ጨዋታ እና 4 ሺህ ብር ቅጣት የተላለፈበት ተጫዋች ነው።

በ3ኛው ሳምንት አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባደረጉት ጨዋታ ላይ ከዳኛ እይታ ውጪ ተጫዋች በክርን መማታቱ በኮሚሽነር ሪፖርት የተደረገበት የአርባምንጩ አንድነት አዳነም ከላይ እንደተጠቀሱት ተጫዋቾች ሁሉ የ4 ጨዋታ እገዳ እና የ4 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎበታል።


የአሰልጣኝ ቅጣት

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወልዋሎን አስተናግዶ 3-1 በተሸነፈበት ጨዋታ 31ኛው ደቂቃ ላይ ከአሰልጣኝ መቀመጫ እንዲነሱ የተደረጉት የኤሌክትሪክ ረዳት አሰልጣኝ ኤርሚያስ ተፈራ 5 ጨዋታ ከቡድኑ ጋር በተጠባባቂ ወንበር ላይ እንዳይገኙ እና 4 ሺህ ብር እንዲቀጡ ተወስኗል።


የክለብ ቅጣቶች

በ4ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻ ከሀዋሳ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ መገባደጃ አካባቢ በተፈጠረው የደጋፊዎች ግጭት ለ17 ደቂቃዎች መቋረጡ ይታወሳል። ለመቋረጡ መንስኤ የነበሩት የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ወደ ሀዋሳ ደጋፊዎች ቁሶች በመወርወራቸው የ70 ሺህ ብር ቅጣት ፣ የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎችም አፀፋውን በተመሳሳይ ተግባር በመመለሳቸው የ50 ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
ሌላው በ4ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ላይ በተደረገውና ድሬዳዋ ከ ደደቢት ያለ ጎል አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከጥላ ፎቅ አካባቢ የድሬዳዋ ማልያን የለበሱ ደጋፊዎች የደደቢት እና ጌታነህ ከበደን ስሞ እየጠሩ በመሳደባቸው 80ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎበታል።

በአንደኛ ሰምንት ተስተካካይ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና አቻ ሲለያይ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ቡናን መለያ የለበሱ ደጋፊዎች በጨዋታ አመራሮች እና በፌዴሬሽኑ አመራሮች ላይ ስድብ በመሰንዘር እና የተለያዩ ቁሶችን በመወርወራቸው ክለቡ  80 ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎበታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *