የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – የህዳር ወር የሶከር ኢትዮጵያ ምርጦች

የኢትዮጵያያ ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር ዘመን ከተጀመረ አንድ ወር አስቆጥሯል። የ5 ዙር ጨዋታዎች በተደረጉበት ሊግ ምርጥ አቋም ያሳዩትን ተጫዋቾች እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል


ግብ ጠባቂ

በረከት አማረ (ወልዋሎ ዓ.ዩ)

በረከት ወልዋሎ ዓ.ዩ ወደ ሊጉ እንዲያድግ አስተዋፅዖ ካደረጉ ተጨዋቾች መሀል አንዱ ነው። ቡድኑ በህዳር ወር ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ላይ መሰለፍ ሲችል በሁለቱ ግብ አልተቆጠረበተም። ግብ ጠባቂው በተለይ ከመቐለ ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ባሸነፉባቸው ጨዋታዎች ላይ ያዳናቸው ሙከራዎች ወልዋሎ በሊጉ አናት ላይ እንዲቀመጥ ምክንያት ነበሩ።

የድሬደዋ ከተማው ሳምሶን አሰፋ ፣ የደደቢቱ ክሌመንት አዞንቶ ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሮበርት ኦዶንካራ እና የኢትዮጵያ ቡናው ሀሪሰን ሄሱ በወሩ ጥሩ አቋም ያሳዩ ሌሎች ግብ ጠባቂዎች ነበሩ።


ተከላካዮች

ከድር ኩሊባሊ (ደደቢት)

ተፈጥሯዊ ቦታው የተከላካይ አማካይ ቢሆንም ደደቢት በኃላ መስመሩ ላይ ባለበት የተጨዋች አማራጭ እጥረት ምክንያት የዘንድሮውን ውድድር ከኩዌኪ አንዶህ እንዲሁም ከደስታ ደሙ ጋር በመጣመር በሁሉም ጨዋታዎች ላይ በመሀል ተከላካይነት ጀምሯል። ደደቢት በአምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ሲያስተናግድ የተጨዋቹ አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነበር። በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ያለው ቅልጥፍና እና የተከላካይ መስመሩን የሚመራበት ትኩረት በቦታው ተመራጭ እንዲሆን ያደረጉ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። አይናለም ኃይለን እና አክሊሉ አያናውን በዝውውሩ ባጣው ደደቢትም የኩሊባሊ መኖር ለአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ትልቅ እፎይታ ሆኗል።


ዓይናለም ኃይለ (ፋሲል ከተማ)

ዓይናለም ባለው የቡድን አመራር ብቃት ምክንያት ዘንድሮ በዝውውር የተቀላቀለውን ፋሲል ከተማን በዐምበልነት መምራት ጀምሯል። ደደቢትን ሲለቅ ለብዙዎች ወደ እግር ኳስ ዘመኑ ማብቂያ ላይ እየደረሰ ያለ ቢመስለም ፋሲል ከተማን ከተቀላቀለ ጀምሮ ብስለቱን በማሳየት የቡድኑን የተከላካይ መስመር በመምራት ላይ ይገኛል። ፋሲል ከተማ የያሬድ ባዬን አለመኖር ተከትሎ የተፈጠረበትን ሰፊ ክፍተትም በአግባቡ በመሸፈን ላይ ይገኛል። ዓይናለም በወሩ ካሳየው ምርጥ የመከላከል ብቃት በተጨማሪም ወልዋሎ ዓ.ዩ ላይ ግብ በማስቆጠር ፋሲል ከተማ ከሜዳው ውጪ አንድ ነጥብ አሳክቶ እንዲመለስ ወሳኝ ሚናን ተወቷል።


አሌክስ ተሰማ (መቐለ ከተማ)

መቐለ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በተደረገው የአራተኛ ሳምንት ጨዋታ 90ኛ ደቂቃ ላይ ጎል እስኪቆጠርበት ድረስ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ጨዋታዎች መረቡ አልተደፈረም ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ዋና ተዋናይ የነበረው ታታሪው የመሀል ተከላካይ በቁመቱ አጠር ቢልም ከፍቃዱ ደነቀ ጋር በፈጠረው ጥምረት ለሊጉ አዲስ የሆነውን ቡድን ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል።
በወሩ በተከላካይ መስመር ጥሩ አቋም ያሳዩ ሌሎች ተጨዋቾችን ስንመለከት ሙጂብ ቃሲም (አዳማ ከተማ) ፣ ፍቃዱ ደነቀ (መቐለ ከተማ)፣ ደስታ ደሙ (ደደቢት)፣ ሰኢድ ሁሴን (ፋሲል ከተማ)በረከት ተሰማ (ወልዋሎ ዓ.ዩ)፣ ምንተስኖት አዳነ እና ሳላዲን ባርጌቾ (ቅዱስ ጊዮርስጊስ) ይጠቀሳሉ።


አማካዮች


ኢማኑኤል ላሪያ (ድሬደዋ ከተማ)

ላሪያ በሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ኮከቦች ምርጫ ላይ መካተት የቻለ የመጀመሪያው የድሬደዋ ከተማ ተጫዋች ሆኗል። የድሬደዋ ከተማ አጨዋወት እንደ ቡድን መከላከል ላይ ያመዘነ በመሆኑ በግለሰብ ደረጃ ነጥረው የሚወጡ ተጨዋቾችን እንዳንመለከት ያደረገ ሆኗል። ሆኖም ኢማኑኤል ላሪያ እስካሁን በተደረጉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ላስተናገደው የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድን የተከላካይ መስመር በቂ ሽፋን በመስጠት በቀላሉ ሙከራዎችን እንዳያስተናግድ ከፍተኛ አስተዋፅኦን አበርክቷል።


ሳምሶን ጥላሁን (ኢትዮጵያ ቡና) 

አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች ተግብረውት በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ለውጥ እያሳየ በነበረው የዳይመንድ የአማካይ ክፍል ውስጥ በቀኝ በኩል የመሰለፍ ሀላፊነት የነበረው ሳምሶን ጥሩ የሚባል ወርን አሳልፏል። ተጨዋቹ ባለው ታታሪነትም የቡድኑን ሚዛን ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ። አሰልጣኙ የተገበሩት አጨዋወትም ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሻሻለ ሲመጣ ስምሶንም በዛው መጠን እየተሻሻለ በመሄድ በቡድኑ እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ሚና ነበረው። ኢትዮጵያ ቡና በተሸነፈበት ብቸኛ ጨዋታ ላይ በቤሔራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት ያልተሰለፈው ሳምሶን የቡድኑ የአማካይ ክፍል በቀላሉ የማይተካው ተጨዋች መሆኑ ተስተውሏል።


ሱራፌል ዳኛቸው (አዳማ ከተማ)

በየጨዋታው ቅርፁን በሚቀያይረው የአዳማ ከትማ ቡድን ውስጥ ሲለወጥ የማይታየው የሱራፌል ዳኛቸው ብቃት ነው። አዳማ አብዛኞቹን አጥቂዎች በጉዳት ባጣበት በዚህ ወር በርካታ የግብ ሙከራዎቹ የሚመነጩት ከሱራፌል ዳኛቸው ነው። ሱራፌል ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚይስደፍር መልኩ የቡድኑ የፈጠራ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ሲገኝ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጀምራቸው እንቅስቃሴዎች አዳማን በተጋጣሚው የመከላከል ዞን ውስጥ ዕድሎችን እንዲፈጥር የሚያስችል ነው።


ታፈሰ ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ)

በሊጉ ከሚገኙ ክለቦች መሀከል በተጋጣሚዎቹ ላይ የመሀል ሜዳ የበላይነት ለመውሰድ ብዙ ሲቸገር የማይታይታየው ሀዋሳ ከተማ ነው። በዚህ በቡድኑ ጠንካራ ጎን ውስጥ ደግሞ ባሳለፍነው ወር ጎልቶ የታየው ታፈሰ ሰለሞን ነው። ሀዋሳ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ብቻ አሸናፊ ሆኖ ቢቀጥልም ከሜዳው ውጪ ደደቢት ላይ ያስቆጠራትን ጎል ያገኘው ከታፈሰ ሰለሞን ነበር። በወልድያው ጨዋታም ታፈሰ ሁለት ጎል የሆኑ ኳሶችን ማቀበሉ በወሩ ላሳየው ስኬት ማሳያ ነበር።

ሌሎች በአማካይ ክፍል ላይ ወሩን ጥሩ በመንቀሳቀስ ያሳለፉት ሚካኤል ደስታ (መቐለ ከተማ)፣ ኢስማኤል ሳንጋሪ (አዳማ ከተማ )፣ አፈወርቅ ኃይሉ (ወልዋሎ ዓ.ዩ) ፣ ፍፁም ተፈሪ (ሲዳማ ቡና) ፣ ኤልያስ ማሞ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ያሬድ ከበደ (መቐለ ከተማ) እና ከንአን ማርክነህ (አዳማ ከተማ) ተጠቃሽ ናቸው።


ካሉሻ አልሀሰን ( ኢትዮ ኤሌክትሪክ )

ክለቡ እንደተለመደው ከውጤት ርቆ ቢቆይም ምናልባትም በሊጉ ወሩን በከፍተኛ ስኬት ካጠናቀቁ ጥቂት ተጨዋቼች መሀል ካሉሻ አንዱ ነው። የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አዲስ ፈራሚ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ ዋነኛ የማጥቃት አማራጭ በመሆን ወሩን አገባዷል። በዚህም ቡድኑ ባስቆጠራቸው አምስት ጎሎች ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን ሲችል አራቱን ጎሎች በአራት የተለያዩ ጨዋታዎች ላይ ማስቆጠሩ እና ቀሪውን አንድ ጎል አመቻችቶ ማቀበሉ የተጨዋቹን ደረጃ እና ያሳለፈውን ስኬታማ ወር በሚገባ የሚገልፅ ነው።


ጃኮ አራፋት (ወላይታ ድቻ)

ሀዋሳ ከተማን በመልቀቅ ወላይታ ድቻን የተቀላቀለው ጃኮ አራፋት በቀድሞው ክለቡ የነበረውን የአማካይ ክፍል ቅንጦት በድቻ አላገኘውም። ቡድኑም በሜዳ ላይ የሚፈጥራቸው ንፁህ የግብ ዕድሎች በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም ጃኮ በግሉ በሚያደርገው ጥረት እና በሚታወቅበት ታታሪነቱ  እስካሁን ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ከከፍተኛ ግብ አግቢዎቹ ተርታ መሰለፍ ችሏል። በመጀመሪያው አንድ ወር ያገባቸውን ጎሎች በሙሉ ግብ በማስቆጠር ብቻ ሳይሆን ከኳስ ውጪም በሚያደርገው እንቅስቃሴ የተጋጣሚን ተከላካዮች ቦታ በማሳት ከሚታወቀው ቶጎዊ አጥቂ ያገኘው ወላይታ ድቻ ወሳኝ ዝውውር ማድረጉ በግልፅ ታይቷል።


ፕሪንስ ሰቨሪንሆ (ወልዋሎ ዓ.ዩ)

አምና በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ብቅ ያለው ፕሪንስ ዘንድሮ በወልዋሎ ስኬታማ ጊዜን በማሳለፍ አመቱን ጀምሯል። ፕሪንስ በወሩ አንድ ግብ ማስቆጠር ሲችል ቀሪዎቹ የወልዋሎ ጎሎች ላይም ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል። በተለይ ቡድኑ በአራተኛ እና አምስተኛ የሊጉ ሳምንታት ሁለት ተከታታይ ድሎችን ሲያስመዘግብ ፕሪንስ የሚሰለፍበት የቡድኑ የቀኝ መስመር የአጥቂ ክፍል ለተጋጣሚዎች አስፈሪውና በርካታዎቹ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች የሚጀመርበት መስመር ሆኖ ታይቷል።

በሊጉ መልካም የሚባል ወር ያሳለፉ ሌሎች አጥቂዎችን ስንመለከት አቤል ያለው(ደደቢት) ፣ አቡዱለጢፍ መሀመድ (ሲዳማ ቡና) ፣ ዳዊት ፍቃዱ (ሀዋሳ ከተማ)፣ ዲዲዬ ለብሪ (ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ከድር ሳሊህ እና  ሙሉአለም ጥላሁን(ወልዋሎ ዓ.ዩ) የሚጠቀሱ ናቸው።


የወሩ ኮከብ ተጫዋቾች
1ኛ. ከድር ኩሊባሊ
2ኛ. ካሉሻ አልሀሰን
3ኛ. ፕሪንስ ሰቨሪንሆ


የወሩ ኮከብ አሰልጣኝ – ብርሀኔ ገ/እግዚአብሔር (ወልዋሎ ዓ.ዩ)

የአሰልጣኙ የወሩ ኮከብነት ቡድናቸው የሊጉ መሪ በመሆኑ ብቻ የሚገልፅ አይሆንም። በእርግጥ ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊጉ ላደገው ወልዋሎ በልጉ አናት በመቀመጥ ወሩን ማገባበዱ ትልቅ ስኬት ቢሆንም የቡድን ግንባታው እና አጠቃላይ ስብስቡ ይበልጥ ትኩረትን ይስባል። እስካሁን ሽንፈት ያልቀመሰው ወልዋሎ በብዛት በቀደሙ ክለቦቻቸው ስኬታማ የሚባል ጊዜን ባላሰለፉ ተጨዋቾች የተገነባ መሆኑ አሁን የሚገኝበትን ደረጃ አስገራሚ ያደርገዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ የአሰልጣኙ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ተጨዋችችን አፈራርቆ በመጠቀም ዋና ተሰላፊዎችን የመለየት ሂደት ቡድኑን ተጠቃሚ አድርጎት ከተከታታይ አቻ ውጤቶች በኃላ ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል።  በቡድኑ ላይም ሆነ በተጨዋቾች የግል ብቃት ላይ እየታዩ ለሚገኙት እድገቶችም አሰልጣኙ ግምባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *