​ሴካፋ 2017፡ ዛንዚባር በአስገራሚ ግስጋሴዋ ስትቀጥል ሩዋንዳ ከምድብ ለመሰናበት ከጫፍ ደርሳለች

በሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የሐሙስ ጨዋታዎች ዛንዚባር ተጋጣሚዎቿን መርታቷን ስትቀጥል ሊቢያ እና ሩዋንዳ አቻ ተለያይተው ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ እድላቸውን አጥብበዋል፡፡ በወንድማማቾች ደርቢ ዛንዚባር ከኃላ ተነስታ ታንዛኒያን 2-1 አሸንፋለች፡፡ ቡሩንዲ በበኩሏ ኢትዮጵያን 4-1 በመርታት እንደዛንዚባር ሁሉ ምድቧን መምራት ጀምራለች፡፡

ዛንዚባር ታንዛኒያን ማቻኮስ ላይ ተገናኝተው ጨዋታው በዛንዚባር 2-1 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ ጥሩ ፉከክር በታየበት ጨዋታ ታንዛኒያ በሃሚድ ማኦ ግብ 1-0 መምራት ብትችልም በሁለተኛው አጋማሽ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ታንዛኒያን የፈተኑት ዛንዚባሮች 2-1 አሸንፈው ሙሉ ሶስት ነጥብ አሳክተዋል፡፡ ሃሚድ በጥሩ ቅብብል ያገኘውን ኳስ በቮሊ በማስቆጠር ነበር የኪሊማንጃሮ ከዋክብቶቹን በ29ኛው ደቂቃ መሪ ያደረገው፡፡ ቃሲም ሱሌማን በግሩም ሁኔታ በ67ኛው ደቂቃ ዛንዚባርን አቻ ሲያደርግ ከ12 ደቂቃዎች በኃላ ለኢብራሂም ሃማድ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ በማቀበል ወሳኝ ሚናን ተወጥቷል፡፡ ሃማድ ከቃሲም የተሻገረለትን ኳስ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ ዛንዚባርን የምድቡ አናት ላይ እንድትቀመጥ አስችሏል፡፡ ዛንዚባር ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሴካፋ ውድድር ላይ በምድብ በፍጥነት የሚሰናበት እና የግብ ጎተራ የሚሆን ብሄራዊ ቡድን የነበራት ቢሆንም በአሁኑ ውድድር ግን ለተጋጣሚዎች ፈተና የሆነ ጥሩ ቡድን ይዛ ቀርባለች፡፡

ሩዋንዳ እና ተጋባዧ ሊቢያ ማራኪ እንቅስቃሴ ባልታየበት ጨዋታ ቡድኖቹ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ የሊቢያ ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ እና የሩዋንዳ ያልተሳኩ የግብ ሙከራዎች የጨዋታው መገለጫዎች ነበሩ፡፡ ጀስቲን ሚኮ ለአማቩቢዎቹ ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ የቻለ ሲሆን የግቡ አግዳሚ ግብ እንዳያስቆጥር አግዶታል፡፡

ዛሬ በምድብ ሁለት ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ይጫወታሉ፡፡

የሐሙስ ውጤቶች

ታንዛኒያ 1-2 ዛንዚባር

ኢትዮጵያ 1-4 ቡሩንዲ

ሩዋንዳ 0-0 ሊቢያ

የዛሬ ጨዋታ

9፡00 – ዩጋንዳ ከ ደቡብ ሱዳን (ካካሜጋ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *