አዲሱ የኢትዮዽያ ቡና አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ እኩለ ሌሊት ላይ አዲስ አበባ ይገባሉ 

የኢትዮጵያ ቡና ቀጣዩ አሰልጣኝ እንደሚሆኑ የተነገረው ዲዲዬ ጎሜስ ዛሬ እኩለ ለሊት ላይ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ታውቋል።

የመጀመርያው የውጭ ዜጋ አሰልጣኝ የሆኑትና በክረምቱ ለሁለተኛ ጊዜ ክለቡን ሊያሰለጥኑ የመጡት ሰርቢያዊው ድራጋን ፓፓዲች በህመም ምክንያት ከክለቡ ጋር በስምምነት ከተለየዩ በኋላ በሊጉ ጅማሮ ቀጣዩ አሰልጣኝ ሆነው የመጡት ኮስታዲን ፓፒች ከክለቡ እውቅና እና ፍቃድ ውጭ አባቴን ለማስታመም በሚል ምክንያት ከሀገር ወጥተው ለደቡብ አፍሪካ ክለብ እንደፈረሙ መታወቁን ተከትሎ ሌላ የውጭ አሰልጣኝ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ የቆየው ኢትዮዽያ ቡና ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስን ቀጣዩ አሰልጣኝ አድርጎ እንደሚሾም ይጠበቃል።

የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በክለቡ ይፋዊ ሬዲዮ ፕሮግራም ላይ አሰልጣኙ በቅድመ ሁኔታ እንደተስማሙ እና ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ አአ ገብተው በቀሩት ጉዳዮች ዙርያ ምክክር እንደሚያደርጉ ገልፀው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ አሰልጣኝ ጎሜዝ አዲስ አበባ አልደረሱም።

በጉዳዩ ዙርያ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ባገኘችው መረጃ መሰረት ዛሬ እኩለ ሌሊት ላይ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የታወቀ ሲሆን ለመዘግየታቸው እንደ ምክንያት የቀረበው የአውሮፓውያን የክረምት ወቅት በመሆኑ ከአየር ንብረቱ አመቺ አለመሆን ጋር ተያይዞ የአውሮፕላን በረራ በመሰረዙ እንደሆነ ተገልፆልናል። በ7ኛው ሳምንት ወደ ጅማ ተጉዞ ጅማ አባጅፋርን በሚገጥምበት ጨዋታም ቡድኑን እንደሚመሩ ለማወቅ ችለናል። (ጨዋታው ሰኞ ይካሄዳል)

የ48 አመቱ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ዳ ሮሳ በአፍሪካ እግርኳስ ላይ ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም በካሜሩኑ ኮተን ስፖርትስ፣ በሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ በቱኒዚያው ሲኤስ ኮንስታንቲን፣ በቅርቡ ደግሞ በአልጄሪያ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚገኘው ጄኤስ ሞውሊድያ ስኪክዳ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ሰርተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *