ፊፋ የ2017 መጨረሻ የሃገራት ደረጃን ይፋ አድርጓል

የአለምአቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ የፈረንጆቹ 2017 ከመጠናቀቁ አስቀድሞ የኮካ ኮላ የሃገራት ደረጃን ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ በደረጃውም ኢትዮጵያ ከዓለም 143ኛ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ኢትዮጵያ በህዳር ወር ከነበረችበት 145ኛ ደረጃ ሁለት ደረጃ በታህሳስ ወር መምጣት ችላለች፡፡ በወሩ በተካሄደው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫላይ ተሳትፎ ያደረገችው ኢትዮጵያ በምድብ ስትሰናበት ባደረገችው ሶስት ጨዋታዎች ደቡብ ሱዳንን 3-0 ስታሸንፍ፣ በብሩንዲ 4-1 ተሸንፋ እንዲሁም ከዩጋንዳ ጋር 1-1 ተለያይታለች፡፡ የሴካፋ ዋንጫ ጨዋታዎችም በፊፋ የሃጋረት ደረጃ ላይ በነጥብ አሰጣጡ ላይ መካተቱን ተከትሎ በውድድሩ ላይ የተሳተፉ 9 ሃገራት የደረጃ ለውጦችን አሳይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው ወር ከነበራት ነጥብ 0.5 በመጨመር በ196 ነጥብ መሰብሰብ ችላለች፡፡

2017 ለኢትዮጵያ እግርኳስ መጥፎ አመት ሆኖ ተገባዷል፡፡ ብሄራዊ ቡድን ባደረጋቸው አብዛኞቹ ጨዋታዎች ሽንፈት የቀመሰ ሲሆን እስከ151ኛ ደራጃም ለመንሸራተት በቅቶ ነበር፡፡ 112ኛ ሆኖ ዓመቱን የጀመረችው ኢትዮጵያ በመጋቢት ወር 103ኛ ደረጃን የያዘችበት ወቅት በአመቱ በንፅፅር የተመዘገበው መልካም የሆነው ደረጃ ሲሆን በተቀሩት ወራት ከ120 ደረጃ በታች ላይ ተገኝታለች፡፡ ቡድኑ ከአፍሪካ ሃገራት ደረጃም ኢትዮጵያ 41ኛ ላይ ትገኛለች፡፡

በሴቶች የሃገራት ደረጃ ኢትዮጵያ ሶስት ደረጃዎችን አሻሽላ በ1143 ነጥብ ከዓለም 90ኛ እንዲሁም ከአፍሪካ 9ኛ ደረጃን መያዝ ችላለች፡፡ ሆኖም በ2017 ብሄራዊ ቡድኑ አንድም ጨዋታ ማድረግ አልቻለም፡፡ በ2016 ህዳር ወር ዩጋንዳ ባዘጋጀችው የሴካፋ ሴቶች ቻምፒዮንሺፕ ላይ ተሳትፎ ካደረገ በኃላም ከጨዋታዎች ርቋል፡፡ በደረጃው ላይም በተለይም በአፍሪካ ዞን የሚገኙት ሃገራት አብዛኞቹ አመቱን ሙሉ ጨዋታዎችን ለማድረግ አለመቻላቸው እየታወቀ የደረጃ መሻሻል ማሳየታቸው አግራሞትን ያጭራል፡፡

ከሴካፋ ዞን አሁንም ዩጋንዳ የተሻለውን ደረጃ የያዘች ሆናለች፡፡ ከዓለም 75ኛ እንዲሁም ከአፍሪካ 16ኛ ላይ ስትገኝ የሴካፋ ቻምፒዮኗ ኬንያ ከዓለም 106ኛ እንዲሁም ከአፍሪካ 26ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ከአፍሪካ ዓመቱን ሴኔጋል በመሪነት ስታጠናቅቅ ቱኒዚያ እና ግብፅ ተከታዩን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

የዓለም ደረጃ

1 ጀርመን

2 ብራዚል

3 ፓርቹጋል

4 አርጀንቲና

5 ቤልጂየም

6 ስፔን

7 ፖላንድ

8 ስዊዘርላንድ

9 ፈረንሳይ

10 ቺሊ

 

የአፍሪካ ደረጃ (በቅንፍ የተጠቀሰው የዓለም ደረጃዎች ናቸው)

1 ሴኔጋል (23)

2 ቱኒዚያ (27)

3 ግብፅ (31)

4 ዲ.ሪ. ኮንጎ (39)

5 ሞሮኮ (40)

6 ቡርኪና ፋሶ (44)

7 ካሜሮን (45)

8 ጋና (50)

9 ናይጄሪያ (51)

10 አልጄሪያ (58)

16 ዩጋንዳ (75)

26 ኬንያ (106)

30 ሩዋንዳ (113)

38 ሱዳን (136)

40 ቡሩንዲ (142)

41 ኢትዮጵያ (143)

44 ታንዛኒያ (147)

46 ደቡብ ሱዳን (153)

51 ጅቡቲ (186)

53 ኤርትራ (206)

54 ሶማሊያ (206)

 

የሴቶች የሃገራት ደረጃ

1 ዩናይትድ ስቴትስ

2 ጀርመን

3 እንግሊዝ

4 አውስትራሊያ

5 ካናዳ

6 ፈረንሳይ

7 ኔዘርላንድ

8 ብራዚል

9 ጃፓን

10 ስዊድን

 

የአፍሪካ ደረጃ (በቅንፍ የተጠቀሰው የዓለም ደረጃቸው ነው)

1 ናይጄሪያ (37)

2 ጋና (46)

3 ካሜሮን (48)

4 ኤኳቶሪያል ጊኒ (53)

5 ደቡብ አፍሪካ (54)

6 ግብፅ (74)

7 ማሊ (80)

8 ዚምባቡዌ (83)

9 ኢትዮጵያ (90)

10 ዛምቢያ (96)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *