ኦኪኪ አፎላቢ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር የአፍሪካ ውድድሮች ላይ መጫወትን ያልማል

አጀማመሩ ያላማረው ጅማ አባ ጅፋር ኢትዮጵያ ቡና እና አርባምንጭ ከተማን በማሸነፍ ተከታታይ ድሎችን በፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በማሳካት በደረጃ ሰንጠረዡ መሻሻልን በከፍተኛ ሁኔታ አሳይቷል፡፡ በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በሚመራው ቡድን ውስጥ ቁልፍ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል ናይጄሪያዊው የፊት አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ይጠቀሳል፡፡ አፎላቢ ጅማ አባ ጅፋር በሊጉ ካስቆጠራቸው 7 ግቦች ውስጥ 6ቱን ከመረብ በማዋሃድ ወሳኝነቱን አሳይቷል፡፡

ኦፎላቢ ባሳለፍነው ሰኞ አርባምንጭ ከተማ ላይ ሐት-ትሪክ የሰራ ሲሆን ለጅማ አባ ጅፋር ወደ መልካም አቋም መመለስ የቡድኑን ህብረት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያምን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡ “በቡድኑ ውስጥ ያለው ጥሩ መንፈስ፣ ህብረት እና ከአሰልጣኛችን ጋር ያለን ግንኙነት ነው ባለፉት ጨዋታዎች ላይ የነበረብንን ድክመት እንድናሻሽልን እና ወደ ማሸነፍ እንድንመጣ ያስቻለን፡፡ ሁሌም ነገሮችን ማሻሻል እንደምንችል እና መጨነቅ እንደለሌብን ይነገረናል፡፡ ከፈጣሪ ጋር ውጤታችንን ለማሻሻል እየሞከርን ነው፡፡”

ጅማ አባ ጅፋር ግብ የማስቆጠር ችግር እንዳለበት ባለፉት ስምንት ሳምንታት ያስቆጠራቸው ሰባት የሊግ ማሳያ ናቸው፡፡ ከነዚህ ግቦች ውስጥ አፎላቢ ስድስት በማስቆጠር የኮከብ ግብ አግቢነት ደረጃ አናት ላይ ከጋናዊው ካሉሻ አልሃሰን ጋር እየተፎካከረ ይገኛል፡፡ ለተከላካዮች ፈተና የሆነው አፎላቢ የቡድን ስራ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት የኢትዮጵያ ቆይታው ግቦችን እንዲያስቆጥር እንደረዳው ይናገራል፡፡ “ግቦቼ የመጡት ከቡድን ስራ ነው፡፡ ሁላችንም አንድ ላይ ነው የምንሰራው በዚህም ደስተኛ ነን፡፡ ጥሩ ለመሆን ነው ፍላጎታችን፡፡ በጅማ ሰዎች ይወዱኛል ይህም ጠንካራ እንድሆን እና ለቡድኔ ጥሩ ግልጋሎት እንድሰጥ ያደርገኛል፡፡” ይላል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ አመቱን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ያጠናቀቀው ብቸኛ የውጪ ሃገር ተጫዋች ሳሙኤል ሳኑሚ ነው፡፡ ዘንድሮ በአግቢዎች ሰንጠረዥ ላይ በርካታ የውጪ ዜጎችን እየተመለከትን እንደመሆኑም የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብር ከ3 የውድድር ዘመናት በኋላ ወደ ውጪ ዜጎች ሊያመራ ይችላል፡፡ አፎላቢም የሳኑሚን ታሪክ መድገም ብቻ ሳይሆን ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ሩቅ እንደሚያልም ይናገራል፡፡ “ኮከብ ግብ አግቢ ብሆን ደስ ይለኛል፡፡ ግን የመጀመሪያ አላማዬ ጅማ አባ ጅፋር በአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ማድረግ ነው፡፡ ኮከብ አግቢ የመሆን እድል አለኝ፡፡ ጠንክሬ መስራት ነው ከእኔ የሚጠበቀው፡፡ ሁሌም የተሻለ እና ብቁ አጥቂ ለመሆን ፍላጎት አለኝ፡፡ ይህ ደግሞ በጠንካራ ስራ ብቻ መሳካት የሚችል በመሆኑ እዚህ ላይ ትኩረት አደርጋለው፡፡ አሰልጣኜ (ገብረመድህን) ‘ኦኪኪ ጠንክረ ስራ’ እያለ ይመክረኛል፡፡ ይህንን ማድረግ ከቻልኩ በጥሩ ብቃት ከመቀጠል አልፎ ለኮከብ ግብ አግቢነት እንደምበቃ አምናለው፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *