​ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት – የእሁድ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

ትናንት የጀመረው የሊጉ 9ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲውል አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ሲዳማ ቡናን እንዲሁም ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ መቐለ ከተማን የሚያስተናግዱባቸውን ጨዋታዎች በዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል። 

አዳማ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

አምና በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን የዘለቁት ሁለቱ ቡድኖች የዘንድሮ አቋማቸው ወጣ ገባ የሚባል አይነት ነው። ከተጋጣሚው የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ በአምስተኛው ሳምንት ሜዳው ላይ ሀዋሳ ከተማን ካሸነፈ በኃላ ዳግም ወደ ድል መመለስ አልቻለም። ያም ቢሆን ቡድኑ በእነዚህ ሳምንታት ሽንፈትን አለማስተናገዱ በደረጃው ሰንጠረዥ ይበልጥ  እንዳይንሸራተት ረድቶታል። ጨዋታው እስካሁን በሜዳቸው ሶስት ጨዋታዎችን ብቻ ያደረጉት አዳማዎች አንድ ግብ እና እንድ ድል ብቻ ያስመዘገቡበትን ደካማ የሜዳ ላይ ሪከርድ ለማሻሻል ሌላ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ይጠበቃል። ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ ላይ የ3-1 ድል የተጎናፀፈው ሲዳማ ቡና የሊጉን የመጀመሪያ ድል ከማሳካቱ ባለፈ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች እያሳየ የሚገኘው የግብ ማስቆጠር ሂደት ቡድኑ ላይ በጥሩ መልኩ የሚነሳ ነጥብ ሆኗል። ሲዳማዎች በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስን ከመረብ ጋር ማገናኘት ተቸግረው ከቆዩ በኃላ ወልድያ ላይ አንድ ፣ ደደቢት ላይ ሁለት እንዲሁም ወላይታ ድቻ ላይ ሶስት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። የዛሬው የአዳማ ጨዋታም ቡድኑ በፍጥነት ከታችኛው የደረጃ ሰንጠረዥ ክፍል ለመረቅ የሚያደርገው ይሆናል።

ሱራፌል ዳኛቸው እና ቡልቻ ሹራ ከጉዳት የተመለሱለት አዳማ ከተማ በምትካቸው አምበሉን ሱሊማን መሀመድን እና ሚካኤል ጆርጅን በጉዳት ምክንያት የጣቸው ተጨዋቾች ሆነዋል። በሲዳማ ቡና በኩል ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ እና ባዬ ገዛሀኝ ቅጣታቸውን ያልጨረሱ ሲሆን ከአራት ጨዋታዎች ቅጣት ተመልሶ አንድ ጨዋታ ማድረግ የቻለው ትርታዬ ደመቀ ከጉዳት ጋር ተያይዞ ለጨዋታው የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

ይህ ጨዋታ ጠንካራ የአማካይ ክፍል ተጨዋቾችን የያዘን ቡድን ስል የሆኑ የመስመር አጥቂዎች ባለቤት ከሆነ ቡድን ጋር የሚያገናኝ ነው። ሱራፌል ዳኛቸውን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው አዳማ ከተማ ሜዳው ላይ የሚያደርገው ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለማግኘት የሚቸገር አይመስልም። ከኢስማኤል ሳንጋሪ እና አዲስ ህንፃ ፊት ለፊት የሚያጣምራቸው ሱራፌል ዳኛቸው ፣ ከንአን ማርክነህ እና ኤፍሬም ዘካሪያስ አይነት ተጨዋቾችን የያዘው አዳማ ከተማ ከፊት እንደሚሰለፍ ለሚጠበቀው ዳዋ ሁቴሳ የመጨረሻ ኳሶችን ከማድረስ ባለፈ በራሳቸውም ሙከራዎችን ማድረግ  የሚችሉ አይነት ተጨዋቾች መያዙ በእንደዛሬው አይነት ጨዋታ ላይ ተጠቃሚ ያደርገዋል። ቡድኑ በድክመቱ በሚነሳው የሲዳማ ቡና የአማካይ ክፍል ላይ የቁጥርም ሆነ የክህሎት ብልጫ የሚኖረው በመሆኑ በተጋጣሚው ሳጥን ዙሪያ ጫና የመፍጠር ዕድል ይኖተዋል። ሆኖም በእንቅስቃሴ ወደ ሲዳማዎች የግብ ክልል ከመድረስ ባለፈ ምን ያህል የመጨረሻ የግብ አጋጣሚዎችን ሊፈጥር ይችላል የሚለው በአምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ላስቆጠረው አዳማ ጥያቄ ሆኖ የሚነሳ ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን የመሀል ክፍላቸው ኳስ ይዞ የመቆየት አቅም ባይኖረውም የሲዳማዎች ማጥቃት ኳስ ከመሀሉ ክፍል ወደ መስመሮች በሚወጣበት ወቅት ላይ ይጀምራል። ይህም ቡድኑ በጨዋታው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢወሰድበት እንኳን የአዳማ አማካዮች የቅብብል ስህተት በሚፈፅሙበት ቅፅበት በሁለተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ለመገኘት የሚያስችለው ጠንካራ ጎኑ ነው። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ቡድኑ ካስቆጠራቸው አምስት ግቦች አራቱን ከመረብ ያገናኙት የመስመር አጥቂዎች አዲስ ግደይ እና አብዱለጢፍ መሀመድ ዛሬም የአዳማ ከተማን የመስመር ተከላካዮች እንደሚያስጨንቁ ይጠበቃል። ለሲዳማዎች በጨዋታው እንቅስቃሴ ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር ፈጣን መሆን እና የነዚህ ሁለት ተጨዋቾች ነፃ የሆነ የቦታ አያያዝ ጨዋታውን ለማሸነፍ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ መቐለ ከተማ 

ዘንድሮም በርካታ ግቦችን እያስቆጠረ እና በምላሹም ተመጣጣኝ የግብ መጠን እያስተናገደ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ አዲስ አዳጊው መቐለ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ 9 ሰዐት ላይ በሀዋሳ ይደረጋል። መቐለ ከተማ አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ሲሆን የሊጉ ሰንጠረዥ በቡድኖቹ መሀከል የአንድ ነጥብ እና የአራት ደረጃዎች ልዩነትን ያሳያል። በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ድርድር የማያውቀው ሀዋሳ ከተማ እስካሁን ከሰበሰባቸው 11 ነጥቦች 9ኙን ያገኘው ሜዳው ላይ ያስተናገዳቸውን ወልድያ ፣ ወላይታ ድቻ እና ድሬደዋ ከተማ በማሸነፍ ነው። የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን የዛሬውን ጨዋታም በተመሳሳይ ማሸነፍ ከቻለ እስከ 4ኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድል ይኖረዋል። ከሁለት ሳምንታት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ከሜዳቸው ውጪ ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻን በጋይሳ አፖንግ ጎል ማሸነፍ የቻሉት መቐለዎች ከዛ በፊት ከአርባምንጭ ጋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ተጋርተው ተመልሰዋል። ሊጉን ከተቀላቀሉ በኃላ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ደቡብ የተጓዙት መቐለ ከተማዎች በጨዋታው ከእስካሁኑ ከፍ ያለ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ይገመታል።

እስራኤል ደርቤን እና ጂብሪል አህመድን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው ሀዋሳ ከተማ ዳንኤል ደርቤ ፣ ላውረንስ ላርቴ ፣ ተክለማርያም ሻንቆ እና ዮናታን ገዙ ከጉዳት ዝርዝር መውጣት ያልቻሉ ተጨዋቾቹ ናቸው። በመቐለ ከተማ በኩል የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች ያሬድ ከበደ እና ጋናዊው የተከላካይ አማካይ ሚክልኤል አካፉ በጉዳት ለጨዋታው እንደማይደርሱ ሰምተናል።

በጨዋታው ሀዋሳዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመውሰድ አብዛኛውን ሰዐታቸውን በመቐለዎች ሜዳ ላይ እንደሚያሳልፉ ይጠበቃል። በቀላሉ ለተጋጣሚ ክፍተት የማይሰጡት መቐለዎችም ክፍት ቦታዎችን ለመዝጋት እና የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ሌላው ተጠባቂ ጉዳይ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በዐመለ ሚልኪያስ እና ሚካኤል ደስታ ጥምረት በቂ የሚባል ሽፋን እንደሚያገኝ የሚጠበቀው የመቐለ ከተማ የኃላ ክፍል የአጥቂ አማካዩ ያሬድ ከበደን ተከትሎ ሚካኤል የሚና ለውጥ ካደረገ ለጥቃት ሊጋለጥ የሚችልበት ዕድል ይኖራል። እዚሁ ቦታ ላይ የሀዋሳ ከተማዎች የማጥቃት አማካዮች ታፈሰ ሰለሞን እና ሙሉአለም ረጋሳ ክፍተቶችን ተጠቅሞ የመጨረሻ ኳሶችን ለአጥቂዎች ለማድረስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቡድኑ ለሚፈጥራቸው ዕድሎች ወሳኝ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው። በመሆኑም የእንግዶቹ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው የመስመር አማካዮች አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና መድሀኔ ታደሰ የመከላከል ተሳትፎ ከፍ ማለት ቡድኑ እዚሁ ቦታ ላይ የሚፈጠርበትን ጫና ለመቀነስ የግድ ይሆናል። ሀዋሳ ከተማዎች በዳዊት ፍቃዱ እና ፍሬው ሰለሞን በሚመራው የመስመር ጥቃታቸው መነሻነት በተጋጣሚያቸው ሁለቱ ክንፎች ላይ የሚያሳድሩት ተፅእኖ ሌላኛው የጨዋታው ወሳኝ ነጥብ ነው። በዚህ ረገድ ሀዋሳ በሁለቱ መስመሮችም ሆነ በሜዳው ቁመት መሀል ለመሀል የተጋጣሚን የመከላከል መስመሮች ለመስበር የሚያበቃ ስብስብ መያዙ ተጠቃሚ ያደርገዋል። ሆኖም የተከላካይ አማካዩ ጂብሪል አህመድ እንደቀደሙት አመታት አለመሆን ከቡድኑ የተከላካይ መስመር ድክመት ጋር ተዳምሮ የያሬድ ከበደ አለመኖር ሊጎዳው ለሚችለው መቐለ ከተማ የፊት መስመር የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ሊያስገኝ እንደሚችል መናገር ይቻላል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *