በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከታዩ ድንቅ ተከላካዮች መሀል ያሬድ ባየህ አንዱ ነው። በ2004 በሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ክለብ መጫወት የጀመረው ያሬድ በአውስኮድ እና ዳሽን ቢራ ቆይታ ካደረገ በኋላ በ2009 ወደ ፋሲል ከተማ አምርቶ እየተጫወተ ይገኛል።
ከሁለት ወራት በላይ በጉዳት ከሜዳ የራቀው ያሬድ ስለ ጉዳቱ ፣ ስለ ፋሲል የ2010 የሊጉ ጉዞ እና ዳግም ከጉዳት አገግሞ በቋሚነት ወደ ሜዳ ስለመመለስ እንዲሁም ስለ ቀጣይ እቅዶቹ ከሶከር ኢትዮጵያው ቴዎድሮስ ታከለ ጋር ቆይታ አድርጎል፡፡
ከሜዳ ያራቀህ ጉዳት አይነት ምንድነው ?
ጉዳቱ ያው መሰንጠቅ ነው የገጠመኝ በቁርጭምጭሚቴ እና ጉልበቴ መሀል የሚገኘው አጥንት ላይ ነበር ጉዳቱ የገጠመኝ። ፕሪምየር ሊጉ ከመጀመሩ ሁለት ሳምንት በፊት በዝግጅት ወቅት በልምምድ ላይ ባለ ጨዋታ ተጋጭቼ ነው የተጎዳሁት።
ከጉዳትህ አገግመህ መቼ ወደ ሜዳ ትመለሳለህ?
የምመለስበትን ቀን እስከ አሁን አላወቅሁም። ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚወስድብኝ ሀኪም ነግሮኛል። በመጠኑ ግን አሁን በግሌ ጂም መስራት ጀምሬያለሁ። ከዝግጅት እንደመራቄም እንደ አዲስ ነው ወደ ሜዳ ተመልሼ ልምምድ የምጀምረው። ምክንያቱም ከእንቅስቃሴ ከራቅኩ ሁለት ወራት ሞልቶኛል። በቀጣይ እንደ ፈጣሪ ፍቃድ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅዬ ወደ ነበርኩበት ቋሚነት ለመመለስ እሰራለሁ።
ለረጅም ጊዜ ከሜዳ መራቅህ የፈጠረብህ ስሜት ምን ይመስላል ?
ጨዋታ ላይ መሆን እና ከሜዳ መራቅ በጣም የተለያየ ባህሪ ነው ያለው። እንኳን ከባድ ጉዳት ገጥሞህ ቀላል ጉዳት እያለብህ እንኳን የጨዋታ ቀን ጭንቅ ይልሀል። ልምምድ ላይ ቁጭ ብለህ ስትመለከት ጉጉት ያድርብሀል። በዛ ላይ በእንቅስቃሴ ውስጥ ስትሆን በነፃነት ያለ ጭንቀት ትጫወታለህ። ከሜዳ ውጭ ቁጭ ብለህ ስትመለከት ደግሞ በጣም ይጨንቃል። የመጫወት ፍላጎት ስላለ ሜዳ ውስጥ መገኘት የተሻለ ስሜት ይሰጥሀል። ጉዳት አጋጥሞህ እንዲህ ስትርቅ ደሞ ጭንቀቱ ይበልጥ ከባድ ነው፡፡
ከፋሲል ጋር ውልህ ዘንድሮ ይጠናቀቃል። የክለቡን የዘንድሮ ጉዞ ስለ ቀጣይ እቅድህ ንገረን
ጥሩ አመት አሳልፈን ከ1-4 ያለውን ደረጃ ይዘን ብናጠናቅቅ ደስ ይለኛል። በጥሩ አቋሜ ተመልሼ ከመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ጀምሮ የምመለስ ይመስለኛል፡፡ የዘንድሮ የፋሲልን የሊግ ጨዋታዎች እስከ አሁን አልተመለከትኩም ባህርዳር ተቀምጬ ራሴን እያስታመምኩ ነበር። እስከ አሁን ግን እንደ ሰማሁት ከሆነ እኔ የምጫወትበት የተከላካይ ቦታ የቡድኑ ጥንካሬ መሆኑን ሰምቻለሁ። ለዛም ነው ጥቂት ግብ ተቆጥሮበታል። ከዛ ባለፈ ግን በመልሶ ማጥቃት እና በፍጥነት በመከላከሉ የተሻለ ቡድን እንደሆነ ነው የተነገረኝ። ዘንድሮ ውሌ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ከተቻለ በዚሁ በፋሲል ከተማ ውሌን ባራዘም ደስ ይለኛል። በተጨማሪም እንደማንኛውም እግር ኳስ ተጫዋቾች በውጪ ሀገራት ሊጎች መጫወት እፈልጋለሁ። ለዚህም ጠንክሬ እሰራለሁ። አሁን ግን በክለቤ ደስተኛ ነኝ፡፡
ወደ ዋልያዎቹ ስብስብ በመደበኛነት ለመመለስ ያለህ ተነሳሽነትስ ምን ያህል ነው ?
የብሔራዊ ቡድኑ ጊዜ ደስ የሚል ጊዜ ነበር። ማንም አልጠበቀኝም ከብሔራዊ ሊግ መጥቼ እንዲሁም በፕሪምየር ሊግ የዳሽን የመጀመሪያ አመት ላይ ነበር የተጠራሁት። አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ነበር የመረጠኝ ፤ በቆይታዬ ብዙ ትምህርት ወስጃለሁ። በብሔራዊ ቡድኑ ወደ ፊት አሰልጣኞች አይን ውስጥ ለመግባት እንዲመርጡኝ ጠንክሬ ሰርቼ መመለስ ምኞቴ ነው፡፡
2006 ላይ ወደ ሀዋሳ ከተማ ለማምራት ከስምምነት ደርሰህ ሀሳብህን ቀይረህ ነበር። እና በወቅቱ ከስምምነት ደርሰህ ሳትቀላቀል የቀረህበት ምክንያት ምን ነበር?
ከሀዋሳ ጋር በወቅቱ ከስምምነት ደርሼ ነበር። በክለቡም በቀረበልኝ ውል ደስተኛ ነበርኩ። ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተሰብ መለየቱ ከበደኝ። በተለይ እናቴ ብቻዋን ነበረች ለዛም ሀዋሳ ሳልቀላቀል የቀረሁት።
እዚህ ለመድረሴ አስተዋጽኦ አድርጎልኛል የምትለው ማንን ነው?
በህይወቴ ብዙ ሰወች አስተዋጽኦ አድርገውልኛል። በቅድሚያ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው እዚህ ለመድረሴ በምክር እና በተግሳፅ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በመቀጠል አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ አምኖብኝ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካትቼ እንድጫወት አቅሜን አውቆ ስላሰለፈኝ ምስጋናዬን ማቅረብ ፈልጋለሁ፡፡
የያሬድ ጉዳት ሲዘረዘር
(በሳሙኤል የሺዋስ)
ቲቢያ (Tibia) በጉልበት እና በቁርጭምጭሚት መገጣጠሚያዎች መሃከል ከሚገኙ ሁለት አጥንቶች አንዱ እና በግዝፈቱም ከሰውነታችን ሁለተኛው ትልቅ አጥንት ነው። ይህ አጥንት ለእግር እንቅስቃሴ ወሳኝ ከሆኑ ጡንቻዎች እና ጅማቶች ጋር የተያያዘ ሲሆን የሰውነትንም ክብደት ከጉልበት ተቀብሎ ወደታች ያስተላልፋል። ቲቢያ ከሰው ልጅ ረጃጅም አጥንቶች ውስጥ በተደጋጋሚ የስብራት አደጋ በማስተናገድ ቀዳሚው ነው፤ ይህም በተለይ ከፊት ለፊት በዋነኛነት በቆዳ ብቻ የተሸፈነ እና ለአደጋ የተጋለጠ በመሆኑ የመጣ ነው። የቲቢያ ስብራት የሰውነት ንክኪ በሚበዛባቸው እንደ እግርኳስ ባሉ ስፖርቶች ላይ በብዛት የሚያጋጥም ሲሆን ስብራቱም በአጥንቱ ላይ የሚመጣ ቀጥተኛ የውጪ ኃይል ወይንም ተጫዋቹ ዘሎ በመጥፎ አቋቋም መሬት ላይ ሲያርፍ የሰውነቱ ክብደት በአጥንቱ ላይ በሚያሳርፈው ጉልበት ምክንያት ይከሰታል። ስፖርተኞች ያለ በቂ የማገገሚያ እረፍት ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ የሰውነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነም በየቀኑ የሚፈጠረው አነስተኛ ጉዳት ተደማምሮ ከጊዜ በኋላ ስብራት (Stress Fracture) ሊያስከትል ይችላል።
የቲቢያ ስብራት በቀዶ ጥገና ወይንም ያለ ቀዶ ጥገና ከውጪ በሚደረግ ህክምና ይጠገናል። የሁለቱም የህክምና ዘዴዎች ዓላማ የተሰበረው አጥንት ክፍል እርስበርሱ ተገናኝቶ ያለምንም መንሻፈፍ እና ማጠር እንዲድን ማስቻል ነው። ህክምናው በአግባቡ ከተሰጠ የቲቢያ ስብራት ያለባቸው ስፖርተኞች ሙሉ በሙሉ አገግመው ወደ ስፖርቱ የሚመለሱበት ዕድል ከ90 በመቶ በላይ ነው።