​ቶክ ጄምስ ወደ መቐለ ከተማ አምርቷል

ያለፉትን 10 ወራት አንድ ክለብ አልባ ሆኖ የቆየው ቶክ ጄምስ በአጭር ጊዜ ውል ለመቐለ ከተማ ለመፈረም ተስማምቷል፡፡ ቶክ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2009 የውድድር ዘመን አጋማሽ ከተለቀቀ በኃላ ለየትኛውም ክለብ ሳይፈርም ከእግርኳስ ርቆ ቆይቷል፡፡

በሊጉ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ካላቸው ክለቦች ተርታ የሚመደበው መቐለ ከተማ ቶክን እስከውድድር ዓመቱ መጨረሻ የሚቆይ ውል ነው የሚያፈርመው፡፡ ቶክ ዝውውሩን ሰኞ የሚያጠናቅቅ ሲሆን እሁድ ወደ መቀለ እንደሚጓዝ ይጠበቃል፡፡ ከሁለተኛው ዙር ጀምሮም ለመቐለ የሚሰለፍ ይሆናል።

ቶክ ስለዝውውሩ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እምነትን ማግኘቱ እንዳስደሰተው ገልፆ ወደ ጥሩ አቋም ለመመለስ እድሉን እንደሚጠቀምበት ተናግሯል፡፡ “እግርኳስ ስራዬ ነው፡፡ የትም ስጫወት ራሴን እየጠበቅኩ ነው የምገኘው፡፡ ስለዚህ በተቀመጥኩባቸው ግዜያቶች የተለያዩ የአካል ብቃት ልምምዶችን ያለማቋረጥ እየሰራው ነበር፡፡ በጨዋታ ላይ ካለ ተጫዋች ያላነሰ ልምምድ ነው ስሰራ የነበረው፡፡ በልምምድ  ዙሪያ ምን ችግር አልነበረብኝም። የነበረኝንም ብቃት ዳግም ለመመለስም ብዙ የምቸገር አይመስለኝም፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ከዚህ በፊት አሰልጥኖኝ ያውቃል፡፡ ሁለታችንም በሚገባ ባህሪያቶቻችንን እናውቃለን፡፡ ከእሱ ጋርም ዳግም መስራት በመቻሌ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡” ሲል ቶክ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በዓመቱ መጀመሪያ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አምርቶ በኢራቅ ያልተሳካ የሙከራ ግዜን ያሳለፈው ቶክ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከተለያየ በኃላ የተረጋጋ የእግርኳስ ህይወት መምራት ተስኖት ቆይቷል፡፡ በወልዲያ የወራት ቆይታ እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጫወት ቢችልም በአቋም መውረድ እና ተደጋጋሚ ጉዳት ምክንያት የሚጠበቀውን ያህል እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻለም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *