​”የተሰጠኝን ሚና በትጋት መወጣት ነው የምፈልገው” ሱሌይማን ሰሚድ

ሱሌማን ሰሚድ ይባላል። ለአዳማ ከተማ በቀኝ መስመር ተከላካይነት አመዛኙን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በመጀመርያ ተሰላፊነት እየተጫወተ ይገኛል። ከተለመደ ቦታው ውጪ እየተጫወተ የሚገኘው የአዳማው 24 ቁጥር ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያሳየ ይገኛል። ሱሌይማን በእግርኳስ ህይወቱ፣ በሚና ለውጡ እና በወደፊት እቅዶቹ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ።


የሱሌይማን ትውልድ እና እድገት በቅርብ አመታት ኮከቦችን ለኢትዮጵያ እግርኳስ እያበረከተች በምትገኘው አሶሳ ከተማ ነው። የወጣቱ የእግርኳስ ህይወት የተጀመረውም በዚሁ ከተማ መንደሮች በመጫወት ነው። ” ከመኖርያ ቤቴ አካባቢ 50 ሜትር ርቆ ትልቅ ስታድየም አለ። ከትምህርት ቤት ስመለስ የእኔ ታላላቆች ኳስ ሲጫወቱ ከጎል ጀርባ በመሆን የሚጫወቱበትን ኳስ እያቀበልኩ ሰው ሲጎድልባቸው ደግሞ አብሬ እየተጫወትኩ የእግርኳስ ተጨዋች የመሆን ፍላጎቴ እየጨመረ መጣ። በኋላም ለትምህርት ቤት ውድድር መጫወት ጀምሬ ባለበት አጋጣሚ በፍቃዱ የተባለ አሰልጣኝ የሚመራው ሲት ቦይስ የሚባል ፕሮጀክት ነበር። አሰልጣኙ የማደርገውን ጥሩ እንቅስቃሴ በመመልከት ‘ ና እዚህ ፕሮጀክት ስራ። እኔ እፈልግሀለው። ‘ ብሎ ሲጠራኝ በሙሉ ፍቃደኝነት ወደ ፕሮጀክት በመቀላቀል እግርኳስን ህይወቴን በአሰልጣኝ የመሰልጠን ጅማሮዬን አደረኩ” ይላል።
ሱሌማን በዚህ ፕሮጀክት በቆየባቸው የሁለት አመታት ብዙ የእግርኳስ መሰረታዊ ስልጠናዎችን እንዳገኘ ይገልፃል። በትልቅ ደረጃ እግርኳስ ተጨዋች ለመሆን የሚያስችለውን ህልሙን ሊያሳካ የሚችልበት መንገድ የተጠረገለት ግን በ2006 ሻሸመኔ ላይ በተደረገ ውድድር ነበር።

” በ2006 ሻሸመኔ ከተማ ላይ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የፕሮጀክት ምዘና ውድድር ላይ አሶሳን በመወከል ተሳትፌ ባሳየሁት ጥሩ እንቅስቃሴ ተመርጬ ከቤተሰብ ከትውልድ ስፍራዬ ርቄ ወደ አአ በመምጣት የኢትዮዽያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን ተቀላቀልኩ። ለሦስት ተከታታይ አመታት በጣም ጠቃሚ የሆኑ ስልጠናዎችን አግኝቻለሁ። አሁን ላለው የእግርኳስ ህይወቴ መሰረት የጣልኩበት ቆይታም አድርጌያለው። በአካዳሚ ቆይታዬ አበበ በቂላ ስታድየም ላይ በአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን በሚዘጋጀው የተስፋ ቡድኖች ጨዋታዎች ላይም ተሰላፊ ነበርኩ። ”
እውነት ለመናገር በአካዳሚ ውስጥ ገብቶ እግርኳስን መሰልጠን ብዙ ጠቀሜታ ቢኖረውም ዋናው ነገር ከቤተሰብ ከትውልድ መንደርህ ተለይተህ አካዳሚ ስትገባ የሆነ አላማ እንዳለህ ታስባለህ። ይህን አላማ ለማሳካት ደግሞ አሰልጣኞች ከሚሰጡኝ ስልጠና ባሻገር በግል የተለያዩ ልምምዶችን ጠንክረህ እንድሰራ አድርጎኛል። ስለዚህ አካዳሚ ገብቼ ያገኘሁት ጠቀሜታ በአላማ እንድትኖር ለአላማ እንድትሰራ ፣ ፕሮፌሽናል የመሆን ህልም እንዲኖርህ አንተን ብቁ ሊያደርግ የሚያስችል የስልጠና ማዕከል ነው ”
ተስፈኛው ወጣት በአካዳሚ በነበረው ቆይታ ቡድኑ በተስፋ ውድድር ላይ በሚያሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ጎልቶ መውጣት ችሏል። በአካዳሚው ለነበረው ቆይታ እና ለነበረው ጥሩ ጊዜ እንዲሁም ድጋፍ ላደረጉለት አካላት በሙሉ ምስጋናውን ያቀርባል። የሱሌይማን ቀጣይ ማረፍያ እና የመጀመርያ ክለቡ አዳማ ከተማ ነው። ተጫዋቹ በ2008 ክረምት አካዳሚን ለቆ በአሸናፊ በቀለ የሚሰለጥነውን ቡድን የተቀላቀለበትን መንገድ እንዲህ ያስረዳል።
” በአአ የተስፋ ቡድኖች ጨዋታ ላይ በነበረኝ አቋም ከሁለትም ሦስት ቡድን ፈልገውኝ ነበር። ሆኖም እኔ የመጀመርያ ምርጫዬ አዳማ ከተማ ስለነበር ከ2009 ጀምሮ በአዳማ ከተማ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስብስብ ውስጥ ተካትቼ በመስራት የመጀመርያ ጨዋታዬንም በአአ ሲቲ ካፕ ላይ የአዳማ ማልያ በመልበስ መጫወት ጀመርኩ። በመቀጠል በፕሪምየር ሊጉ አንደኛ ዙር ላይ ሙሉ ለሙሉ የመጫወት እድል አላገኘሁም ነበር። በኋላ በሁለተኛው ዙር ላይ አልፎ አልፎ ቢሆንም ተቀይሮ በመግባት የመጫወት እድል አግኝቻለሁ። የበለጠ ግን ዘንድሮ በአአ ሲቲ ካፕ ላይ ባሳየሁት መልካም እንቅስቃሴ በፕሪምየር ሊጉ ከ10 ጨዋታ በ8ቱ የቋሚ ተሰላፊነት እድል አግኝቼ በመጫወት ላይ እገኛለው። ”

ሱሌይማን ከተወለደበት መንደር በመውጣት የኢትዮጵያ ኮከብ የሆነው ሳላዲን ሰዒድን ምሳሌ ያደርጋል። የእርሱን ዱካ ተከትሎ የሀገሪቱ ምርጥ ተጫዋች መሆንም ይፈልጋል። በተስፋ ውድድር ላይ በአካዳሚ ማልያ ሲያደርገው የነበረው እንቅስቃሴም የሳላዲንን ፈለግ ተከትሎ ምርጥ አጥቂ እንደሚሆን ፍንጭ ሰጥቶ ነበር። ሆኖም አዳማ ከተማን ከተቀላቀለ ወዲህ በቀኝ መስመር ተከላካይነት እየተሰለፈ ይገኛል። ሱሌይማን ፍላጎቱ በአጥቂነት የመጫወት ቢሆንም በሚሰጠው ሚና ለመጫወት ዝግጁ እንደሆነ ይገልፃል።
” በአካዳሚ በነበረኝ ቆይታ የአጥቂ መስመር ተጨዋች ነበርኩ። ሆኖም ግን በአሁኑ ሰአት የተከላካይነት ስፍራ እንድጫወት ተደርጓል። ወጣት እንደመሆኔ መጠን ምንም እንኳን እግርኳስ መጫወት ስጀምር አጥቂ የመሆን ትልቅ ፍላጎት ቢኖረኝም ስራ እስከሆነ ድረስ አሰልጣኞች የሚሰጡኝ ሚና ሁሉ በትጋት በሚገባ መወጣት አለብኝ። ይህን ስታደርግ ደግሞ የፕሮፌሽናልነት አዕምሮ እንዲኖርህ ያደርገሀል።”
በአዳማ ከተማ ዘንድሮ በ8 ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው ሱሌይማን ቡድኑ በተጫዋች ስብስብ ጠንካራ እንደሆነ ገልጾ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ካለፉት አመታት የተሻለ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ለማጠናቀቅ እንደሚተጉ ተናግሯል። በግሉም ራሱን በማሻሻል ትልቅ ተጫዋች የመሆን ህልሙን ገልጿል።
” ትልቅ ተጫዋች የመሆን አላማ አለኝ። ጠንክሬ በመስራት በውጪ ሀገራት ክለቦች የመጫወት እና ለብሔራዊ ቡድን ከወጣት ቡድን ጀምሮ እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ድረስ መጫወት እፈልጋለው። ትልቅ ተጨዋች ለመሆን ካሰብክ እና አላማ ካለህ አዕምሮህን የፕሮፌሽናል አስተሳሰብ እንዲኖረው ማድረግ አለብህ። በትንሽ አድናቆት እና ሙገሳ አላማህን የምትስት ከሆነ ወደዚህ ህይወት የገባህው ለአላማ ሳይሆን በአጋጣሚ እንጂ ፈልገህ አይደለም ማለት ነው። ስለዚህ አሁን ባለኝ አቋም ተዘናግቼ አልቀመጥም። በዚህ እድሜ ይህን መስራት ከቻልኩ ነገ ከነገህ ወድያ ደግሞ የተሻለ ነገር መስራት እንደምችል ስለማስብ ጠንክሬ ስራዬን በመስራት አላማዬን ለማሳካት እጥራለው ። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *