ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 1-1 በመለያየት በድል አልባ ጉዞው ቀጥሏል።

በረከት ሳሙኤልን በሰንደይ ሙቱኩ ፣ ዮሴፍ ዳሙዬን በኢማኑኤል ላርያ ፣ ሳውሬል ኦልሪሽን በ አናጋው ባደግ እንዲሁም ዳኛቸው በቀለን በአትራም ኩዋሜ ምትክ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በማካተት ሲቀርብ ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማን ከረታው ስብስብ ምንም የተጫዋች ቅያሪ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ገብቷል።

ጨዋታው እንደተጀመረ በ1ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ከግብ ጠባቂው መሳይ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ እንግዶቹ ሲዳማ ቡናዎችን ቀዳሚ ሲያደርግ የአቻነት ጎል ለማግኘት ረጅም ደቂቃዎች የጠበቁት ድሬዎች ተቀይሮ በገባው ጋናዊ አጥቂ አትራም ኩዋሜ የ79ኛ ደቂቃ ጎል አቻ መሆን ችለዋል።

የአቻ ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ በ9 ነጥብ በወራጅ ቀጠናው 14ኘመ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሲዳማ ቡና በ13 ነጥብ 8ኛ ላይ ተቀምጧል።

በጨዋታው ዙርያ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ስምዖን አባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ከመጀመሪያው አጋማሽ ይልቅ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻልን ነበርን። በርካታ አጋጣሚዎችንም ብንፈጥርም አንድ ጎል ብቻ ነው ያስቆጠርነው። ካለፈው ጨዋታ የተወሰኑ ተጫዋቾች በጉዳት እና ከጨዋታ መደራረብ የአቋም መውረድ ምክንያት ለውጥ አድርገን ነበር የተጫወትነው።  በቀሪ ጨዋታዎች ከዚህ አስከፊ ውጤት ወጥተን እንቀርባለን። የድሬዳዋ ደጋፊም ከሌላው ጊዜ በተሻለ መልኩ ቢደግፉን የተሻለውን ድሬዳዋ እናያለን፡፡

አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና

ዛሬ በጨዋታው  ያገኘናቸውን መልካም  የግብ አጋጣሚን አግኝተን መጠቀም አልቻልንም። ጨዋታውን በ15 ደቂቃዎች ውስጥ መግደል እንችል ነበር።  ከእነሱ በተሻለ በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን አግኝተን ነበር። ባዬ ያመከናቸው ኳሶች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው። ከእረፍት በኃላ ተጋጣሚያችን የተሻሉ ነበሩ በተለይ በመስመር በኩል የሚመጡት ኳሶች ከባዶች ሆነውብናል።
በክለቡ ትሰናበታለህ አትሰናበትም በሚባለው ነገር አልፈራም። ውጤታማ ነኝ ፤ ውጤት እያመጣሁ ነው፡፡ ከዛ ባለፈ የዛሬው ጨዋታ አላስከፋኝም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *