​ስሞሃ በኡመድ ግቦች ታግዞ ወደ ድል ተመልሷል

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ጨዋታ ስሞሃን ያስተናገደው ኤል ናስር 2-0 ተሸንፏል፡፡ ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪም ከረጅም ሳምንታት ቆይታ በኃላ ግብ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ ኡመድ በ2 ደቂቃ ልዩነት አከታትሎ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ሰማያዊ ሞገዶቹን ወደ ድል መልሷል፡፡

በ19ኛ ሳምንት ባልተጠበቀ መልኩ በታንታ 1-0 የተሸነፈው ስሞሃ በ2019 ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት እንዲቀዛቀዝ አድርጎት ነበር፡፡ በካይሮ ኢንተርናሽናል ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ናስሮች በተለይ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ላይ በተሻለ ወደ ግብ ለመቅረብ እና ጫና ፈጥረው ለመጫወት ሲሞክሩ ስሞሃዎች ባልተሳካ የማጥቃት ሽግግሮች ጨዋታው ጀምረዋል፡፡ በመከራም ረገድ ስሞሃዎች ተቀዛቅዘው በታዩበት የመጀመሪያው 45 ኤል ናስሮች የነበራቸው ብልጫ ወደ ግብነት መቀየር አልቻሉም ነበር፡፡ በ44ኛው ደቂቃ ላይ ከስሞሃ የግብ ክልል በረጅሙ የተላከውን ኳስ መሃመድ ሃምዲ ዛኪ በግንባሩ በመጭረፍ ለኡመድ በማብረድ የቀድሞ የመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ወደ ግብነት እንዲለውጠው አስችሏል፡፡ ኡመድ በዚህ ግብ ብቻ ሳያበቃ ከደቂቃ በኃላ ከግራ መስመር ማንጋ ያሻገረውን ቅጣት ምት በግንባሩ በመግጨት የስሞሃን መሪነት አጠናክሯል፡፡

ከእረፍት መልስ ኤል ናስሮች ውጤቱን ለመቀልበስ በተደጋጋሚ ወደ ስሞሃ የግብ ክልል ቢደርሱም በሶስተኛው የሜዳ ክፍል በሚወስዱት የተቻኮለ ውሳኔ ግብ ለማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በተቃራኒው ስሞሃዎች በመልሶ ማጥቃት 5 ያለቀላቸውን የግብ እድሎች አምክነዋል፡፡ በተለይ ኡመድ ያገኛቸውን ሁለት የጠሩ የግብ እድሎች ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል፡፡ ኡመድ በ50ኛው ደቂቃ ግብ ክልሉ እየወጣ በነበረው የናስሩ ግብ ጠባቂ ሙስጠፋ ሃቲባ አናት ላይ ቢሰድም ኳስ በግቡ አናት ወጥቷል፡፡ ከደቂቃዎች በኃላም ኡመድ በአደጋ ክልሉ ያገኘውን እድል የናስር ተከላካዮች ጨርፈው ወደ ውጪ አውጥተውታል፡፡ ኡመድ በ69ኛው ደቂቃ ታሪቅ ጠሃ አቡዱልሃሚድ ተቀይሮ ከሜዳ ገብቷል፡፡ ስሞሃዎች ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር የሚችሉባቸውን እድሎች ሲያመክኑ አምሽተዋል፡፡ ሆኖም ናስሮች ውጤቱን መቀልበስ ተስኗቸው ስሞሃ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ወደ አሌክሳንደሪያ መውሰድ ችሏል፡፡ በጨዋታው ላይ ከስሞሃ በኩል መሃሙድ ሙአዝ እንዲሁም በኤል ናስር በኩል መሃመድ ሃጋግ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ኡመድ በዘንድሮው ሊግ ከአምናው በንፅፅር የተቀዛቀዘ ዓመት እያሳለፈ ቢገኝም በክለቡ በቋሚነት መሰለፉን ቀጥሏል፡፡ በዘንድሮው የሊግ ዘመን ያስቆጠረውን የግብ መጠን ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡

በታላት የሱፍ የሚመራው ስሞሃ በደረጃ ሰንጠረዡ በ32 ነጥብ አራተኛ ሲሆን ሊጉን አል አሃሊ በ45 ነጥብ ይመራል፡፡ የሽመልስ በቀለ ቡድን የሆነው ፔትሮጀት በ21 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በ20ኛ ሳምንት ጨዋታም ነገ ስዌዝ ላይ ኤንፒን ያስተናግዳል፡፡ ጨዋታው ከምሽቱ 12፡00 ይጀምራል።
የኡመድን ጎሎች ለመመልከት ሊንኩን ይጬኑ | LINK

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *