​የአለም ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል

የፊፋ የዓለም ዋንጫ በሩሲያ አስተናጋጅነት በያዝነው ዓመት መጨረሻ ይደረጋል፡፡ ፊፋ ከውድደሩ ጅማሮ አስቀድሞ እንደሚያደርገው ሁሉ የዓለም ዋንጫው በተመረጡ ሃገራት ጉዞ ያደርጋል፡፡ ፊፋ ዋንጫው የሚጓዝባቸው ሃገራትን ዛሬ ይፋ ሲያደርግ ከ51 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ ተካታለች፡፡

የዓለም ዋንጫው በኮሎምቦ ስሪ ላንካ ዛሬ ጉዞውን የጀመረ ሲሆን በሩሲያዋ ቭላዲቮስቶክ በሚያዚያ 23 የጉብኝት ጉዞውን እንደሚያጠናቅቅ ይጠበቃል፡፡ በ6 አህጉራት በሚገኙ 51 ሃገራት የሚዘዋወረው ዋንጫው በ91 የአለም ከተሞች ለደጋፊዎች ለጉብኝነት ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ ከነዚህ ከተሞች መካከል የተመረጠችው አዲስ አበባ ነች፡፡ ዋንጫው በኢትዮጵያ መዲና በቅዳሜ የካቲት 17 እና እሁድ 18 እንደሚመጣ የተያዘለት መርሃ ግብር ያሳያል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው በ12 ከተሞች እንደሚዘዋወር ይጠበቃል፡፡

የለስላሳ መጠጦች አምራች የሆነው ኮካ ኮላ የሚያዘጋጀው ይህ ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ከ8 ዓመታት በኃላ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ አስቀድሞ ዋንጫው በተለያዩ ሃገራት ሲዘዋር ወደ አዲስ አበባም የመምጣት አጋጣሚን አግኝቶ ነበር፡፡ በወቅቱም እግርኳስ ወዳዱ ህብረተሰብ በሚሌኒየም አዳራሽ ተገኝቶ ዋንጫውን የመመልከት እድል ማግኘቱ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *