​አሰልጣኝ ምንተስኖት በፋሲል ይቆያሉ 

የፋሲል ከተማ የቦርድ አመራር ትላንት ምሽት በክለቡ ወቅታዊ አቋም ዙርያ ውይይት በማድረግ እና ከአሰልጣኝ ምንተስኖት ጋር ለመቀጠል በመስማማት ተለያይተዋል።

ክለቡ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ጎል አስተናግዶ መሸነፉን እና የአቻ ውጤት መብዛቱን ተከትሎ አሰልጣኙ ምንተስኖት ጌጡ ላይ ተቃውሞ መበርታቱን እንዲሁም ክለቡ በዘንድሮ አመት ከአምናው በተሻለ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ብዛት ያላቸውን ተጫዋቾችን በከፍተኛ ብር ያስፈረመ ሆኖ ሳለ እስካሁን ያስመሰገበው ውጤት ዝቅተኛ ነው በሚል አሰልጣኙ ከክለቡ ሊሰናበቱ ይችላል ቢባልም ትላንት ምሽት የክለቡ የቦርድ አመራር ባደረጉት ሰፊ ስብሰባ የክለቡ ወቅታዊ ችግር በዝርዝር ተመልክተዋል። አሰልጣኙም ከክለቡ ጋር እንደሚቀጥሉ ወስነው ወጥተዋል።

ክለቡ እንደድክመት ያነሳው በዋናነት የአቻ ውጤት መብዛቱ ፣ የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾች በጉዳት ለረጅም ጊዜ መራቅ ፣ ጎል የማስቆጠር ከፍተኛ ችግር መኖር ፣ አሰልጣኙ ተጫዋቾችን የሚቆጣጠርበት መንገድ አነስተኛ መሆን እና ሌሎችም ክፍተቶች እንደድክመት የተቀመጡ ሲሆን በቀጣይ መስተካከል አለባቸው በተባሉ ጉዳዮች ላይም ስብሰባው ሲነጋገር አምሽቷል ።

አጼዎቹ በ13ኛው ሳምንት እሁድ ጥር 20 ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ጎንደር አፄ ፋሲል ስታድየም የሚያከናውኑት ጨዋታ ወሳኝ እንደሆነ እና በዚህ ጨዋታ ላይ የሚመዘገበው ውጤት የወደፊቱን ጉዞ የሚወስነው እንደሆነ ሲነገር እንዲሁ በቀጣይ ከሁለተኛው ዙር ከመጀመሩ አስቀድሞ ቡድኑ መጠናከር ባለበት ነገር ላይ ከወዲሁ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች መፍትሄ ያስቀመጠ መሆኑ ታውቋል። የቡድኑ አሰልጣኞች አባላት በቀጣይ ስራቸው ላይ አተኩረው እንዲሰሩም መመርያ ተሰጥቷቸው ስብሰባው ተጠናቋል ።

በሌላ ዜና ፋሲል ሁለት የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጨዋቾችን አስመጥቶ ስማቸውን ለፌዴሬሽኑ ቢያስመዘግብም ፊርማቸውን አለማኖራቸው የታወቀ ሲሆን ከቡድኑ ጋር ልምምድ እየሰሩ ይቆዩና ጥሩ አቋም እንዳላቸው ከተረጋገጠ ሊፈርሙ እንደሚችሉ ታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *