​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ሰበታ እና ለገጣፎ ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል

በ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ጨዋታዎች እሁድ ሲካሄዱ ለገጣፎ አአ ከተማን በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን አጥብቧል። ሰበታም ነጥቡን ከአአ ከተማ ጋር አስተካክሏል።

አአ ከተማ 0-3 ለገጣፎ ለገዳዲ

(በኦምና ታደለ)

በመድን ሜዳ በተደረገው ጨዋታ ለገጣፎ በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠራቸው ሶስት ግቦች ወሳኝ ሶስት ነጥቦችን ከሜዳው ውጪ እንዲጨብጥ አስችለውታል፡፡

በጨዋታው የለገጣፎ አማካዮች የመቀባበያ አማራጮችን በመፍጠር እና በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት ከአዲስ አበባ ከተማ በእጅጉ ተሸለው ታይተዋል፡፡ እምብዛም ግብ ሲያስተናግድ የማይታየው አዲስ አበባ በአንፀሩ በጨዋታው ላይ የተከላካይ ክፍሉ ተዳክሞ ታይቷል፡፡

ጨዋታው በተጀመረ በሶስተኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ነፃ የነበረው ጌትነት ደጀኔ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ለገጣፎን መሪ ማድረግ ሲችል ከስድስት ደቂቃዎች በኃላ ከግራ መስመር የተሰነጠቀውን ኳስ ፈጣኑ የለገጣፎ አጥቂ ፋሲል አስማማው የአዲስ አበባው የመሃል ተከላካይ ጊት ጋትኮችን በመቅደም ከግብ በመውጣት ላይ በነበረው ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን ላይ አስቆጥሮ ለገጣፎን ላልተጠበቀ የ2-0 መሪነት አብቅቷል፡፡

ሁለት ግቦችን በመከላከል ችግር ያስተናገዱት አዲስ አበባዎች ወደ ጨዋታውን ለመመለስ በ11ኛው እና በ15ኛው ደቂቃ በእንዳለማሁ ታደሰ አማካኝነት የሞከሯቸውን ሙከራዎች ግብ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ በአንፃሩ ለገጣፎዎች በአጭር ቅብብል እና አልፎ አልፎ ወደ ፊት በሚላኩ ረጅም ኳሶች ተጋጣሚያቸውን መፈተን ቀጥለው ታይተዋል፡፡ በ33ኛው ደቂቃ አማካዩ ዘካሪያስ ከበደ በግንባሩ የጨረፈለትን ኳስ ፋሲል ቢያገኝም ፍሬውን መርታት ሳይችል ኳስ ወደ ግብ ጠባቂው እጅ አምርታለች፡፡ በ42ኛው ደቂቃ ዘካሪያስ ከቀኝ መስመር ወደ አደጋ ክልሉ የላከውን ኳስ ፍሬው ማውጣት ሳይችል ለገጣፎ 3-0 መሪ መሆን ችሏል፡፡ አምና በቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳለፈው ዘካሪያስ ግሩም የሆነ ግብ ነበር ከመረብ ማዋሃድ የቻለው፡፡ ለለገጣፎ ብልጫ ምላሽ ያልሰጡት ባለሜዳዎቹ ፍቃዱ አለሙ በነፃ አቋቋም ሆነ ያገኘውን ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ የአጋማሹ መገባደጃ ላይም በተመሳሳይ እሱባለው ሙልጌታ በሳጥኑ ውስጥ ኳስን ይዞ ቢገባም ሙከራው ከግቡ አናት በላይ ሆኗል፡፡

ለእረፍት መልስ አዲስ አበባዎች ተጭነው ለመጫወት ሲሞክሩ ለገጣፎዎች በበኩላቸው በጥንቃቄ የነበራቸውን መሪነት አስጠብቅው ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር የሞከሩበት አጋማሽ ነበር፡፡ ሃይል የቀላቀለበት አጨዋወት እና እምብዛም የጠሩ የግብ እድሎችን በዚህኛው አጋማሽ የታዩ ነበሩ፡፡ የተሞከሩት ሙከራዎችም ለግብ ጠባቂዎቹ ፈታኝ ያልነበሩ ሲሆኑ በይበልጥ ጨዋታው ተመጣጣን ሆኖ አልፏል፡፡ በ57ኛው ደቂቃ በሁለተኛው 45 ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የአዲስ አበባው አማካይ ጌታነህ ሙሉነህ ከርቀት የሞከረውን ኳስ ለገጣፎው አንተነህ ሃብቴ ሲያመክንበት ከአምስት ደቂቃ በኃላ የለገጣፎው ዳዊት ቀለመወርቅ የመታውን ኳስ ፍሬው አድኖበታል፡፡ በጨዋታው ማብቂያ ላይ አንተንህ የፋሲል ጌነታቸው ሙከራ ወደ ውጪ ካወጣበት ውጪ ይህን ያህል የሚጠቅ ሙከራ በጨዋታው ላይ ሳይስተናገድ ቀርቷል፡፡

ለገጣፎ ለገዳዲ በ16 ነጥብ ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ ሲል መሪው አዲስ አበባ ከተማ አሁንም የሰንጠረዡ አናት ላይ ሰባታ ከተማን በግብ ክፍያ በመብለጥ ተቀምጧል፡፡

በመድን ሜዳ በጨዋታው ወቅት አምቡላንስ አለመገኘቱ እና የተጎዱ ተጫዋቾች ማንሺያ ቃሬዛ በግዜው በጨዋታ አለመኖሩ (ጨዋታው ከተጀመረ ከብዙ ደቂቃዎች በኃላ በጨዋታው ታዛቢ ትዕዛዝ እንዲመጣ ተደርጓል) ክፍተቶች የሆኑ እና ለወደፊት መታረም ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሌሎች መርሀ ግብርሮች 
(በአምሀ ተስፋዬ)

8፡00 የጀመረው የካ ክፍለ ከተማ እና ፌደራል ፖሊስ ጨዋታ በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና እየሰለጠነ የሚገኘው ፌደራል ፖሊስ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ 3-0 ማሸነፍ ችሏል። ለፌደራል ሊቁ አልታየ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ቀሪዋን ግብ ደረጄ አስቆጥሯል፡፡

ሰበታ ላይ ቡራዩ ከተማን ያስተናገደው ሰተበታ ከተማ 1-0 በማሸነፍ ነጥቡን ከመሪው አአ ከተማ ጋር አስተካክሏል። ለሰበታ ከተማ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል ያስቆጠረው ከሳምንታት የኋላ ወደ ጎል የተመለሰው አብይ ቡልቲ ነው።

ኢኮስኮ ከረጅም ሳምንታት በኃላ ጨዋታ ማድረግ የቻለው ደሴ ከተማን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። ሱሉልታ ያያ ቪሌጅ ላይ በተደረገው ጨዋታ በ3ኛው ደቂቃ አበበ ታደሰ ነው የኢኮስኮን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው።

ባህርዳር ላይ ሱልልታ ከተማን የገጠመው አማራ ውሃ ስራ ያለ ግብ ነጥበ ተጋርቶ ሲወጣ ሽረ ላይ ሊደረግ ታስቦ ወደ አዲስ አበባ የተዛወወረው የሽረ እንዳስላሴ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ በለገጣፎ ስታዲዮም እንዲደረግ መርሃ ግብር ቢወጣም በዕለቱ የተገኙት የፀጥታ ክፍሉ ኃላፊ በቂ የፀጥታ ኃይል እንደሌለ እና ኃላፊነት እንደማይወስዱ በመግለፃቸው ጨዋታው ሳይከናወን ቀርቷል፡፡ የፌዴሬሽን አካል ከሚመለከተው አካል ጋር ተገቢውን የመረጃ ልውውጥ አለማድረጉ ለጨዋታዋች መደራረብ ምክንያት እየሆነም ይገኛል።

በዚህ ምድብ ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ መድን እና ነቀምት ከተማ ጨዋታ መድን በፌዴሬሽኑ እገዳ ምክንያት ሳይደረግ ቀርቷል። መድን ከፌዴሬሽኑ ጋር እገዳው እንዲነሳ በመስማማቱ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ጨዋታ ማድረግ እንደሚጀምር ታውቋል።

ከነቀምት ጋር በተያመዘ ዜና በ3ኛው ሳምንት ከቡራዩ ከተማ ጋር ባደረጉትጠጨዋታ ያልተገባ ተጫዋች አሰልፈዋል በሚል በቡራዩ በቀረበባቸው ክስ መሰረት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለቡራዩ ከተማ የ3-0 ፎርፌ አሸናፊነት ወስኗል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *