​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | በሐት-ትሪክ በደመቀው ሳምንት ደቡብ ፖሊስ በሜዳው ጎል ማዝነቡን ቀጥሏል

በምድብ ለ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 12ኛ ሳምንት 6 ጨዋታዎች ሶስት ሐት-ትሪኮች ሲመዘገቡ ደቡብ ፖሊስ በተጋጣሚዎቹ ላይ ጎል እያዘነበ መሸኘቱን ቀጥሏል። ሀዲያ ሆሳዕና ፣ ቡታጅራ ፣ መቂ እና ካፋ ቡናም ድል ቀንቷቸዋል።

ሀምበሪቾ 0-1 ካፋ ቡና

ሀምበሪቾ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በተላለፈበት ቅጣት ምክንያት ከሜዳው 150 ኪ/ሜ ርቀት ሀዋሳ ላይ ጨዋታውን አድርጎ በካፋ ቡና  1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ  ክፍለ ጊዜ ሀምበሪቾዎች በካፋ ቡና ላይ በርካታ የግብ አጋጣሚን መፍጠር የቻሉ ሲሆን በተለይ አጥቂው ፍፁም ደስይበለው የካፋ ቡና የተከላካይ ስፍራ በተደጋጋሚ ሲረብሽ ተስተውሏል። 23ኛው ደቂቃ ላይ ጎይቶም ገ/መድህን ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ ፍፁም አግኝቷት ሳይጠቀምባት የቀራት አጋጣሚ እና በአንፃሩ ካፋ ቡናወች በአኒ ኡጅሉ አማካኝነት አንድ ለግብ የቀረበች መልካም አጋጣሚ በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀሱ ናቸው።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ተሽለው የቀረበት ካፋ ቡናዎች በሳፎ ቁሪ መሪነት የጎል አጋጣሚዎችኝ ሲፈጥሩ ሀምበሪቾዎችም በፍፁም ደስይበለው አማካኝነት 55ኛ እና 59ኛው ደቂቃዎች ሁለት ግልፅ የግብ እድልን አምክነዋል።

በ65ኛው ደቂቃ ላይ ኦኒ ኡጁሉ በግሩም ሁኔታ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ትዕዛዙ ፍቃዱ ከመረብ አሳርፎ የካፋ ቡናን የማሸነፊያ ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ከግቧ በኃላ አሁንም የበላይ መሆን የቻሉት ካፋዎች በተደጋጋሚ ለግብ የቀረቡ ሙከራወችን አድርገው ወደ ግብነት መለወጥ ሳይችሉ ቀርተዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ ሀምበሪቾው ግብ ጠባቂ ሄኖክ ወንድማገኝ እና የካፋ ቡናው አጥቂ ሳፎ ቁሪ በፈጠሩት ሰጣ ገባ የእለቱ ዋና ዳኛ ተከተል ተሾመ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወግዷቸዋል፡፡ በቀሪ ደቂቃዎች ሁለቱም ክለቦች ጫና ፈጥረው ካፋዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሀምበሪቾወች አቻ ለመሆን ጥረት ቢያደርጉም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በካፋ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ደቡብ ፖሊስ 7-3 ነገሌ ከተማ

የሀምበሪቾ እና ካፋ ቡናን ጨዋታ ተከትሎ በሀዋሳ ስታዲየም የተደረገው የደቡብ ፖሊስ እና ነገሌ ከተማ ጨዋታ በድምሩ 10 ጎል ተቆጥሮበት በደቡብ ፖሊስ 7-3 አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት ሲሆን 18ኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ለማ የሰጠውን ኳስ ብሩክ ኤልያስ የነገሌ ቦረናው ግብ ጠባቂ እስራኤል ዮሀንስ መውጣትን ተመልክቶ ባስቆጠራት ግሩም ጎል ደቡብ ፓሊስን ቀዳሚ አድርጓል። በ36ኛው ደቂቃ የደቡብ ፓሊሱ ተከላካይ ደረጀ ፍሬው በአንተነህ ሀይሉ ላይ በሳጥን ውስጥ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን ፍ/ቅጣት ምት ራሱ አንተነህ መትቶ የፖሊሱ ግብ ጠባቂ ሀብቴ ከድር አድኖበታል።

ጨዋታው በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ተጋግሎ ቀጥሎ 40ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ወገኔ ላይ በተሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ በኃይሉ አስቆጥሮ ደቡብ ፓሊስ 2-0 እንዲመራ አስችሏል፡፡ በ42ኛው ደቂቃ ወደ ፖሊስ የግብ ክልል በረጅሙ የተላከችውን ኳስ የደቡብ ፓሊሱ ግብ ጠባቂ ሀብቴ ከድርና የተከላካዩን ደረጀ ፍሬውን ያለመናበብ ተጠቅሞ ይሁን ደጀን አስቆጥሮ ነገሌዎችን ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ ያስቻለችን ግብ ሲያስቆጥሩ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ነገሌ ቦረናዎች በያለው በለጠ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ሁለት አቻ በሆኑበት ቅፅበት በመጀመሪያ አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃ ላይ በኃይሉ ወገኔ ግሩም ግብ አስቆጥሮ በደቡብ ፓሊስ 3-2 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ደቡብ ፖሊሶች ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ ብልጫን ያሳዩበት ሲሆን ብሩክ ኤልያስም ደምቆ የዋለበት ሆኗል። 50ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ወገኔ በረጅሙ በግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ብሩክ ኤልያስ በሚገባ ተቆጣጥሮ ለአበባየሁ ዮሀንስ ሲያመቻችለት አበባየሁ አስቆጥሮ ልዩነቱን ሲያሰፋ በ52ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም አድማሱ ከመሀል ሜዳ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ብሩክ ኤልያስ በድንቅ አጨራረስ ለራሱ ሁለተኛ ለክለቡ አምስተኛ ግብ ከመረብ አሳርፎ የፖሊስን ልዩነት ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል።
71ኛው ደቂቃ ላይ ነገሌ ቦረናዎች በነብዩ ዳርፈታ አማካኝነት ልዩነቱን ቢያጠቡም ብሩክ ኤልያስ 85ኛ ደቂቃ ላይ ከሚካኤል ለማ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል። ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ደግሞ ብሩክ ኤልያስ የደቡብ ፓሊስን ግብ ወደ ሰባት በማሳደግ በውድድር አመቱ 4 ጎል በአንድ ጨዋታ ያስቆጠረ የመጀመርያው ተጫዋች መሆን ችሏል።

ሌሎች ጨዋታዎች

ወደ ቤንች ማጂ ቡና ያቀናው ወልቂጤ ከተማ 2-2 አቻ ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል። ወልቂጤዎች በመጀመርያው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-0 መምራት ቢችሉም ባለሜዳዎቹ አከታትለው ባስቆጠራቸው ጎሎች ነጥበ ተጋርተው መውጣት ችለዋል።

ናሽናል ሲሜንትን ያሰተናገደው ቡታጅራ ከተማ 4-0 አሸንፏል፡፡ ኤፍሬም ቶማስ ሶስት ጎሎች በማስቆጠር ሐት-ትሪክ የሰራ ሌላው ተጫዋች ሲሆን ቀሪውን ግብ አየለ ፍቃደ አስቆጥሯል።

መቂ ላይ መቂ ከተማ ስልጤ ወራቤን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል። ከዕረፍት በፊት እንግዳዎቹ መሪ መሆን ቢችልም መቂዎች ከዕረፍት መልስ በላይ ያደሳ በ52ኛው እና 71ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራቸው ጎሎች አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ሆሳዕና ላይ ኢዘዲን አብደላን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው ሀዲያ ሆሳዕና ድሬዳዋ ፖሊስን 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋችነቱነ እያሳየ የሚገኘው ኢብሳ በፍቃዱ ሶስት ግቦች በማስቆጠር ሐት-ትሪክ መስራት ሲችል የጎሎቹን መጠን 8 በማድረስም የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ደረጃውን መምራት ቀጥሏል።

ሻሸመኔ ከተማ ከ ሀላባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ዲላ ከተማ ከ ጅማ አባ ቡና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።

ፎቶ – በአንድ ጨዋታ አራት ጎሎች ያስቆጠረው ብሩክ ኤልያስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *