​ከፍተኛ ሊግ | ጅማ አባ ቡና ከአሰልጣኙ ጋር ሲለያይ ሀዲያ ሆሳዕና አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል

በዚህ ሳምንት ከከፍተኛ ሊግ ክለቦች ጋር የተያያዙ አጫጭር መረጃዎችን እነሆ ።


ጅማ አባ ቡና እና ግርማ ሀብተዮሀንስ ተለያይተዋል

(በቴዎድሮስ ታደሰ)

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ተከተው በክረምቱ ክለቡን የተቀላቀሉት አሰልጣኝ ግርማ ሀብተዮሀንስ በስምምነት ከክለቡ ጋር መለያየታቸው ተረጋግጧል። አሰልጣኝ ግርማ የውድድር ዓመቱ ከተጀመረ ሶስተኛው ሳምንት ጀምሮ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያስተናግዱ ቆይተዋል፡፡ በተለይም በስምንተኛው ሳምንት በአሰልጣኙ ላይ ሲደርስ የነበረው ተቀውሞ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ክለቡ ይህንን እና ተያያዥ ችግሮችን በቅርቡ እንደሚፈታ ገልጾ የነበረ ቢሆንም በአስረኛው ሳምንት ቡድኑ በሜዳው ከመቂ ባደረገው ጨዋታ አቻ መለያየቱን ተከትሎ ደጋፊው በክለቡ አመራሮች እና አሰልጣኙ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማቱ የሚታወስ ነው።

በዚህ ምክንያት የአባቡና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በገዛ ፍቃዳቸው ከክለቡ ስራዎች ራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን በዚህ ሳምንት ደግሞ አሰልጣኝ ግርማ ሀብተዮሀንስ ክለቡን ለቀዋል። ምክትል አሰልጣኝ የነበሩት ኤልያስ ተሻለ ከክለቡ ጋር እንዲቀጥሉ ቢጠየቁም ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የዋና አሰልጣኙን ፈለግ በመከተላቸው ቡድኑ ለተወሰኑ ቀናት ልምምድ ለማቆም እንዲገደድ አድርጎታል። ቡድኑ በአሁኑ ወቅት በግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ አማካኘነት ወደ ልምምድ መመለሱ ታውቋል።

የቀድሞ ተጫዋቾቹ የደሞዝ ክፍያ ዕዳ ያለበት ጅማ አባቡና ሌላ ፈተና ውስጥ ገብቷል። አንዳንድ የቀድሞ ተጫዋቾች ” የተለያዩ ወራት ክፍያ ሳይከፈለን ቀርቷል። ከዚህስ በኃላ የስራ አስፈፃሚው ከቦታው ከተነሳ ማንን እንጠይቀለን? ”  በማለት ለሶከር ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡


ሀዲያ ሆሳዕና አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

(በቴዎድሮስ ታከለ)

አሰልጣኝ እዮብ ማለን ለአርባምንጭ ከተማ አሳልፎ የሰጠው ሀዲያ ሆሳዕና ለተከታታይ ሶስት ሳምንት ያለ ዋና አሰልጣኝ ቀሰይቶ በመጨረሻም አሰልጣኝ ኢዘድን አብደላን በዋና አሰልጣኝነት እንደቀጠረ ክለቡ አስታውቋል፡፡ አሰልጣኙ በባለፈው ዓመት የስልጤ ወራቤ አሰልጣኝ የነበሩ ሲሆን ዘንድሮ የሀዲያ ሆሳዕና የቴክኒክ ክፍል ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።  አሰልጣኝ ኢዘዲን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በሜዳቸው ከድሬዳዋ ፖሊስ አድርገው በኢብሳ በፍቃዱ ሐት-ትሪክ በመታገዝ ድል ቀንቷቸው መውጣት ችለዋል፡፡


የክለቦች ቅሬታ

(አመሀ ተስፋዬ)

የከፍተኛ ሊግ ክለቦች (በተለይም በምድብ ሀ) በመርሃ ግብር መዛባት ምክንያት ያላቸውን ቅሬታ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ አካል ቅሬታቸውን በአካል በመቅረብ ገልፀዋል። ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ ምክንያት ሳይከናወን የቀሩትን ጨዋታ በአዲስ መርሃ ግብር እንዲከናወንም ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እነዚህን ተስተካካይ ጨዋታ ለማከናወን የወጣው መርሃ ግብር ክፍተት ስላለው ጥያቄያቸውን በአዎንታ የተቀበለው የከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ አካል ዛሬ ምሽት ላይ ስብሰባ እንዲሚያደርጉ አስታውቀዋል። ምናልባትም ጥያቄቸው ተቀባይነት ካገኝ የ13ኛው ሳምንት መርሃ ግብር ሳይከናወን በይደር ቆይቶ ተስተካካይ ጨዋታዋች በምትኩ ይደረጋሉ፡፡


ለገጣፎ ለገዳዲ

(አመሀ ተስፉዬ)

ለገጣፎ ከተማዎች ከአክሱም ከተማ ጋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ባለመደረጉ ቅሬታቸውን ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን አቅርበዋል። በሳለፍነው ሳምንት ለገጣፎ ከ አክሱም ከተማ እንዲጫወቱ መርሀ ግብር ቢወጣም የአክሱም 9 ተጫዋቾች በምግብ መመረዝ ታመዋል በሚል ምክንያት ጨዋታው እንዳይከናወን ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ጨዋታው ሳይከናወን ቀርቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ቅሬታቸውን ያቀረቡት ለገጣፎች የህክምና ቡድኑ በምን ያህል ፍጥነት ማረጋገጥ እንደቻለ ፣ ያም ቢሆን የታመሙት 9 ተጫዋች ሆነው ሳለ ውድድር ከመጀመሩ በፊት ክለቡ 30 ያህል ተጫዋቾችን እንደማስመዝገቡ በ21 ልጆች መጫወት ይችላሉ ፣ እንደዚ አይነቱ ድርጊት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚጠቅማት አይደለም ፣ ነገም ሌላ ክለብ 8 እና 9 ተጫዋች ታሞብኛል ብሎ ቢመጣ ጨዋታዋች ላይከናወኑ ነው ፤ የከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ አካል በነዚህ አይነት ምክንያቶች ጥያቄዎችን የሚቀበል ከሆነ ውድድሩ በታሰበበት ጊዜ መጨረስ ያዳግታል  የሚችለው እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ያካተተ ቅሬታውን ነው ለፌዴሬሽኑ ያቀረበው።


ኢትዮጵያ መድን ከአስራት ኃይሌ ጋር የነበረውን ችግር ፈትቷል

(አመሀ ተስፋዬ)

ከ9ኛው ሳምንት ጀምሮ በፌዴሬሽኑ በተላለፈበት እገዳ ምክንያት ውድድር ሳያከናውን የቆየው ኢትዮጵያ መድን በባለፈው እሁድ ከባህርዳር ከተማ ጋር ጨዋታውን አድርጓል፡፡

አሰልጣኝ አስራት እና ኢትዮጵያ መድን ጥር 18 ቀን 2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት የበላይ አመራሮች እንዲሁ ከክለቡ አመራሮች ጋር በወጣቶች ስፖርት ጉዳይ ሚኒስተር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስተር ዲኤታ ሰብሳቢነት በጋራ ባደረጉት ውይይት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል። በዚህም መሰረት ክለቡ ክፍተቶችን ወደፊት እንደሚያሉና እንዲስተካከሉ እንዲሁም ለአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የሰምንት ወር ደሞዝ እንዲከፈል ከስምምነት ደርሰዋል።

የኢትዮጵያ መድን ክለብ ከአሰልጣኝ አስራት ጋር ለደረሱት መግባባት ትልቁን ሚና የተጫወተው የወጣቶች ስፖርት ጉዳይ ሚኒስተር መስሪያ ቤት መሆኑን ገለጾ የሚጠበቅበት ክፍያን መፈፀሙንም ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል።

አምበሪቾ

(አመሀ ተስፋዬ)

የሁለት ጨዋታ ከሜዳ ውጭ እንዲጫወት ቅጣት ተላልፎበት የነበረው አምበሪቾ ከተማ ባቀረበው ይግባኝ ቅጣቱ ወደ አንድ ጨዋታ ዝቅ በማለቱ ባሰለፍነው እሁድ ከከፋ ቡና ጋር ከሜዳው ውጭ ተጫውቶ ቅጣቱን ጨርሶል ከሀላባ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ከትቆረጠበት ድቂቃ በዱራሚ ላይ ይከናወል ተብሎ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *