ዛሬ በተካሄዱ 2 ወሳኝ የብሄራዊ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ሱሉልታ ከነማ እና አዳማ ከነማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል፡፡
በ4 ሰአት በተካሄደው የአዳማ ከነማ እና የጥቁር አባይ ትራንስፖርት ጨዋታ የናዝሬቱ ክለብ 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፡፡ ለአዳማ ከነማ የድል ግቦቹን ወንድወሰን ሚልኪያስ እና ሄኖክ ገምቴሳ አንድ አንድ ግብ ሲያስቆጥሩ በታላላቅ ክለቦች የሚፈለገው በረከት አዲሱ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡
በአሸናፊ በቀለ የሚመራው አዳማ ከነማ ድሉን ተከትሎ ባለፈው አመት የተሰናበተውን ፕሪሚየር ሊግ መልሶ ለመቀላቀል 1 ጨዋታ ብቻ ቀርቶታል፡፡ በግማሽ ፍፃሜው የአዳማ ከነማ ተጋጣሚ ሱሉልታ ከነማ ነው፡፡
በ8 ሰአት በተደረገው ሁለተኛው የእለቱ ጨዋታ ሱሉልታ ከነማ አዲስ አበባ ከነማን ከከፍተኛ ትግል በኋላ በመለያ ምቶች በማሸነፍግማሽ ፍጻሜውን አረጋግጧል፡፡ የጨዋታው ሙሉ 90 ደቂቃ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን በመለያ ምቶች ሱሉልታ ከነማ 4-3 አሸንፏል፡፡
የግማሽ ፍፃሜው ተፋላሚዎች የታወቁ ሲሆን እሁድ በ8 ሰአት ወልቂጤ ከነማ ከ ወልዲያ ከነማ ፣ በ10 ሰአት ደግሞ አዳማ ከነማ ከ ሱሉልታ ከነማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ከአራቱ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ቡድኖች መካከል የፕሪሚየር ሊግ ልምድ ያለው ከ1994 እስከ 2005 ድረስ በሊጉ የቆየው አዳማ ከነማ ብቻ ነው፡፡