በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመራ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ በመጀመርያው የውድድር አመት መልካም ጉዞ እያደረገ የሚገኘው መቐለ ከተማ በክረምቱ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ማሰናበቱን ቀጥሎበታል።
የአካል ብቃት ዝቅተኛ መሆን ፣ የሚሰጠውን ታክቲክ መተግበር አለመቻል እንዲሁም ከጨዋታ ፍጥነት ጋር ያለመሄድ ችግር አለባቸው በሚል ለዘጠኝ ተጨዋቾች ክለቡ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መስጠቱ ይታወቃል። ከነዚህም መካከል እስካሁን ከአምስቱ ጋር የሁለት ወር ደሞዛቸውን በመስጠት በስምምነት ሲለያይ ትላንት ደግሞ ከግራ መስመር ተከላካዩ አለምነህ ግርማ ጋር በስምምነት መለያየቱ ታውቋል።
ከመቐለ ከተማ ጋር እስካሁን አብረው ልምምድ እየሰሩ የሚገኙት ቶክ ጀምስ ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና እያሱ ክለቡ ስለመፈረማቸው ማረጋገጫ ባይሰጥም በቅርቡ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከውጭ ካስመጣቸው እና ፊርማቸውን ካኖሩ ተጨዋቾች መካከል ጋናዊ አማካይ ሰይዱ አብዱልዱሩ በሀገሩ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማለቅ የሚገባው ወረቀት በፍጥነት ተፈፅሞ ባለመላኩ ዝውውሩ ሳይሳካ ቀርቶ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ከቡድኑ እንደሚለቅ ሲጠበቅ የነበረው ሚካኤል አኩፎ ደግሞ ባጋጠመው ሀዘን ምክንያት ከክለቡ በተሰጠው ፈቃድ ወደ ሀገሩ ያቀና በመሆኑ ከክለቡ ጋር አብሮ የማይገኝ ተጨዋች ሲሆን በቅርቡ ከክለቡ ጋር ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል።