ድራማዎች ያልተለዩት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ መደረግ ከሚገባው 4 ወራት ተሻግሮ እዚህ ቀን ላይ ደርሷል። ቀን ከተቆረጠለት የካቲት 24 ወደ ሌላ ጊዜ ሊራዘም የሚችልበት ፍንጭም እየታየ ይገኛል።
ቅዳሜ የካቲት 10 የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት በጁፒተር ሆቴል በመሰብሰብ ባልተለመደ ሁኔታ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተነጋግረው ምርጫው በተያዘለት እለት (የካቲት 24) በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ላይ እንደሚደረግ እና ከየካቲት 15 ጀምሮ ለምርጫው ተሳታፊ አካላት በሙሉ የጥሪ ደብዳቤ እንደሚላክ በመወሰን የምርጫ አስፈፃሚው ኮሚቴ ለሚዲያው እና ለህዝቡ መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ከትላንት (የካቲት 15) ጀምሮ በምርጫው ላይ ለሚሳተፉ አካላት በሙሉ የጥሪ ደብዳቤ ይበተናል ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን ምንም አይነት ደብዳቤ አለመውጣቱን ለማወቅ ችለናል። ዛሬ ስብሰባ የተቀመጠው የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫውን በተመለከተ ያሳለፈው ውሳኔ ምን እንደሆነ ማወቅ ባንችልም የምርጫው ሂደት በምን መንገድ ላይ ይገኛል ብለን ባጣራነው መሰረት ለፊፋ የምርጫ ታዛቢ እንዲልክ እና የምርጫውን ቀን እንዲያውቅ ለተላከው ደብዳቤ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን እየተጠበቀ እንደሚገኝ ሰምተናል ።
ይሁን እንጂ በአንዳንድ ለምርጫው ቅርበት ባላቸው ሰዎች ዘንድ የምርጫው ሁኔታ ለሁለት በተከፈለ ሀሳብ እንደሚገኝ እየተነገረ ይገኛል ። በአንደኛው ወገን እንደሚነገረው ከሆነ ካፍ ለተላከለት ደብዳቤ ምላሽ እንደሰጠ እና የፊፋ ምላሽ እየተጠበቀ ነው የሚባለው ሆን ተብሎ ምርጫውን በድጋሚ ለማራዘም የሚፈልጉ አካላት የፈጠሩት ምክንያት ነው ፤ ፊፋ ደብዳቤ ልኮ ተደብቆ ቢሆንስ የሚል ጥርጣሬ እንዳደረባቸው ሲገለፅ በሌላ ወገን ” ፊፋ ታዛቢ ሳይልክ እና ምርጫው እንደሚካሄድ ሳያውቅ ምርጫው በተባለበት ቀን ቢደረግ እና ፊፋ ከምርጫው በኋላ ለምርጫው እውቅና አልሰጥም ቢል ትልቅ ኪሳራ የሚያጋጥመን ይሆናል” በሚል የፊፋን የእውቅና ደብዳቤ እስኪመጣ ድረስ ምርጫውን አለማድረጉ ይሻላል የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ለማወቅ ችለናል ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው የምርጫው ሂደት በሁለት የተለያዩ ሀሳቦች የተነሳ ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሻግሯል ።
የምርጫ አስፈፃሚው ኮሚቴ ከሰኞ ጀምሮ ምርጫውን ለማስፈፀም ሁሉም የኮሚቴ አባላት ከያሉበት ክልል ወደ አዲስ አበባ በመግባት ስራቸውን እንደሚጀምሩ እንጂ ምንም ነገር እንደማያውቁ እየተነገረ ሲሆን አንዳንድ የፌዴሬሽን አመራሮች ስልክ በመደወል ከፊፋ የዕውቅና ደብዳቤ ካልመጣ በቀር ምርጫውን ማድረግ እንደሚከብድ እየነገሯቸው መሆኑንም ሰምተናል ።
አሁን ባገኘነው መረጃ የምርጫውን ሁኔታ ወደ ሌላ አስገራሚ መልክ የሚቀይር ሌላ ጉዳይ ብቅ ብሏል። ለፕሬዝደንትነት ምርጫ እጩ ሆነው በቀረቡት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ላይ ያነጣጠረ ከ50 ገፅ በላይ የሚሸፍን ሰነድ በሦስት ግለሰቦች መዘጋጀቱ ታውቋል። ሰነዱ እጩ ፕሬዝደንቱ ሰርተውታል የተባለውን የምርጫ ስነ ምግባር ጥሰት በዝርዝር የያዘ ሲሆን አዘጋጆቹ ተመራጭ እጩውን ከምርጫው ለማስወጣት ያዘጋጁት እንደሆነና በምርጫው ወቅት ሊቀርብ እንደሚችል መገመት ይቻላል።
በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ አሰልቺ እየሆነ የመጣው ይህ ጉዳይ በየጊዜው በሚቀያየሩ ውሳኔዎች እና በየሰአቱ በሚለዋወጡ የሰዎች ሀሳብ ምክንያት እየተንዛዛ እዚህ የደረሰ ሲሆን በቀጣይ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ለማወቅ አዳጋች መልክን ይዟል።