​ወልዲያ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ | ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

ከ12ኛው ሳምንት በኃላ በሊጉ ላይ ያልተመለከትነው ወልዲያ ዛሬ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማስተናገድ ተስተካካይ ጨዋታዎቹን ማድረግ ይጀምራል። ይህን ጨዋታም እንደተለመደው በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

ከ7ኛው ሳምንት ተላልፎ ዛሬ ላይ የመጣው ጨዋታ ለክለቦቹ ደረጃ መሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። መጠነኛ መነቃቃት በማሳየት ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ማሳካት የቻለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታው ከወራጅ ቀጠናው መውጣትን እያሰበ ነው ወደ ወልዲያ ያቀናው። ቡድኑ ይህን ጨዋታ አሸንፎ ነጥቡን 16 ማድረስ ከቻለ ቢያንስ ከበላዩ ያሉት ቡድኖች ተስተካካይ ጨዋታቸውን እስኪያደርጉ ድረስ እስከ 10ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ይችላል። ከውድድር ከራቀ ከወር በላይ የሆነው እና ከታች ያሉ ቡድኖች በቅርብ ሳምንታት ነጥብ መሰብሰብ መጀመራቸውን ተከትሎ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጠው ወልዲያ ደግሞ በእጁ የሚገኙት አራት ተስተካካይ ጨዋታዎች መሪዎቹን እስከመቅረብ ሊያደርሱት ይችላሉ። ከሁሉም በፊት ግን ዛሬ በኢንታርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ የሚመራውን በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። 

ወልዲያ ወደ ውድድር ይመለስ እንጂ የበርካታ ተጨዋቾቹን አገልግሎት አያገኝም። ከነዚህ ውስጥ ታደለ ምህረቴ ፣ ያሬድ ብርሀኑ እና ፍፁም ገ/ማርያም እስካሁን ቡድኑን ያልተቀላቀሉ ሲሆን አዳሙ መሀመድ ፣ ተስፋዬ አለባቸው  እና ሰለሞን ገ/መድህን ደግሞ ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጨዋቾች ናቸው። በፌዴሬሽኑ የስድስት ወራት ቅጣት የተላለፈበት የአማረ በቀለ ጉዳይ ዛሬ እልባት ይገኝለታል ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን ለዚህ ጨዋታ መድረሱ አልተረጋገጠም። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩልም ቢኒያም አሰፋ ፣ ምገስ ታደሰ ፣ ጥላሁን ወልዴን እና በሀይሉ ተሻገር አሁንም ጉዳት ላይ ሲገኙ ከታህሳስ አጋማሽ ጀምሮ ጉዳት ላይ የነበረው ዐወት ገ/ሚካኤል ግን ማገገሙን ሰምተናል።

እውነታ

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በ2007 እና 2009 የውድድር አመቶች ለአራት ያህል ጊዜ ተገናኝተዋል። በእነዚህ ጊዜያት ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሜዳው ሁለት ጊዜ ከሜዳው ውጪ ደግሞ አንድ ጊዜ ባለድል ሆኗል። ቀሪው አንድ ጨዋታም በአቻ ውጤት የተገባደደ ነበር። ግብ በማስቆጠሩም በኩል ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሰባት ጎሎች ቀዳሚ ሲሆን ወልድያ በአራቱ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ነገሮች ለወልዲያ ቀላል አይመስሉም። ክለቡ በውድድር ላይ በነበረባቸው ሳምንታት በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በተከታታይ ይገቡ ከነበሩ ተጨዋቾቹ ውስጥ አምስት ያህል የሚሆኑትን መጠቀም አለመቻሉ ለአሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ብዙ የቤት ስራን የሚሰጥ ነው። ይህ ሁኔታ ቡድኑ ከውድድር መራቁ ሊያመጣበት ከሚችለው የተጨዎች የጨዋታ ብቁነት ጥያቄ ጋር ሲዳመር ወልዲያን በዛሬው እና በቀጣይ ተስተካካይ ጨዋታዎች በአዲስ አቀራረብ እንድንጠብቀው የሚያደርገን ይሆናል። በዛሬው ጨዋታ ግን መሀል ሜዳ ላይ ሐብታሙ ሸዋለም ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና ምንያህል ተሾመ ከአንዷለም ንጉሴ እና ኤዶም ኮድዞ ጋር የሚኖራቸው ጥምረት በእጅጉ ተጠባቂ ይሆናል። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ መምጣት በኃላ የመከላከል ድክመቱ እየተሻሻለ ሲመጣ ግብ የማስቆጠር ጥንካሬውን ደግሞ እየወረደ ይገኛል። ምንም እንኳን በተደጋጋሚ ጉዳት የቡድኑ የኃላ መስመር ተጨዋቾችን አቀያይሮ በመጠቀም ጫላ ድሪባን በመስመር ተከላካይነት እስከማሰለፍ ቢደስም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለቴ ግብ ሳይቆጠርበት ወጥቷል። ይህ አግሞ በርካታ ግቦችን በማስተናገድ በሊጉ ቀዳሚ ለሆነ ክለብ ጥሩ ሪከርድ ተደርጎ ይወሰዳል። በሌላ በኩል የአልሀሰን ካሉሻ እና ዲዲዬ ለብሪ እንደወትሮው አለመሆን የኤሌክትሪክን መሻሻል ሙሉ እንዳይሆን አድርጎታል። ላለፉት አምስት ጨዋታዎች ግብ ያላስቆጠረው ካሉሻ ወደ አጥቂ መስመር ተሰላፊነት መምጣቱ ተፅእኖ ያሳደረበት ይመስላል። ነገር ግን በድሬደዋው ጨዋት ወደ አጥቂ አማካይነት ሚናው ተመልሶ ለኃይሌ እሸቱ ግብ አመቻችቶ ማቀበሉ ወደ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ መልሶታል። ከኳስ ውጪ ያለው እንቅስቃሴው አሁንም ጥሩ የሆነው ዲዲዬ ለብሪ ግን ከኳስ ጋር ባለው እንቅስቃሴ አጠቃላይ ውሳኔዎቹ በስህተት የተሞሉ ሆነዋል። ያም ቢሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተሸናፊነት ስነ ልቦናውን ከማደስ አንፃር ከሲዳማ አንድ ነጥብ ይዞ መመለሱ እና ድሬደዋን ማሸነፉ ለዛሬው ጨዋታ ትልቅ እገዛ ይኖራቸዋል።                

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *