​ከፍተኛ ሊግ | ቡራዩ የምድቡ መሪ ሲሆን ባህርዳር ተጠግቷል 

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረጉ የቀሩ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ጀምረዋል። ቡራዩ ከተማ ነጥብ ተጋርቶ የምድቡን መሪነት ሲረከብ ባህርዳር ከተማ ወደገአናት የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጥሏል።

በ9ኛ ሳምንት መካሄድ የነበረበትና በወቅቱ መድን በእገዳ ላይ የነበረ በመሆኑ ሳይካሄድ የቀረው የኢትዮጵያ መድን እና ቡራዩ ከተማ ጨዋታ መድን ሜዳ ላይ ተካሂዶ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በርከት ያለ የስፖርት ቤተሰብ የተደመበት ጨዋታ በፈጣን እንቅስቃሴ የታጀበ የነበረ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ለጎል የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። በመድን በኩል በ3ኛው ደቂቃ ላይ ናይጀሪያው አጥቂ አዳም በግንባሩ የገጫት ኳስ የቡራዩ ግብ ጠባቂ ሲያድንበት በ25ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀ የነበረውና ለቡራዩ ከተማ ተከላካይ ከፍተኛ ጫና ሲፈጥር የነበረው ዮናታን ብርሃነ በቀኝ መስመር እየገፋ የመታውን ኳስ በድጋሚ የቡራዩ ግብ ጠባቂ ከግብ ታድጎታል። በተጨማሪም በ45ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ መንገሻ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበታል። የጥንቃቄ ጨዋታን መርጠው ወደ ሜዳ በገቡት ቡራዩዎች በኩል በ5ኛው ደቂቃ ሚካኤል ደምሴ ከርቀት የመታው ኳስ በግቡ አግዳሜ በግራ ክፍል ሲወጣበት በ22ኛው ደቂቃ ላይ ኢሳያስ ታደሰ ከቀኝ መስመር እየገፋ ገብቶ ወደ ግብ መትቶ የመድን ግብ ጠባቂ ሲያድንበት ከግብ ጠበቂው የተመለሰውን ኳስ አምበሉ አቡበከር ደሳለኝ መትቶ በግቡ አናት ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየ ቢሆንም ቡራዩ ከተማ አምበሉ አቡበከርን ቀይረወ ካስወጡ በኃላ በቀኝ መስመር የነበራቸው እንቅስቃሴ ቀንሶ ታይቷል። በቀሪዎቹ ደቃቃዎች መድን በናይጀሪያው አጥቁ ሳሙኤል ካዚቶ ፣ ሐብታሙ እና ዮናታን አማካኝነት በርካታ ሙከራዎች ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አአ ከተማ እና ሰበታ ከተማ እየተፈራረቁ ሲመሩት የነበረውን ምድብ ሀ ቡራዩ ከተማ በ23 ነጥቦች በግብ ልዩነት በመብለጥ መምራት ጀምሯል።

በ5ኛው ሳምንት ሊካሄድ ታስቦ በፀጥታ ጉዳዮች ምክንያት ሳይካሄድ የቀረው የባህርዳር ከተማ እና የደሴ ከተማ ጨዋታ ዛሬ በባህርዳር ኢንተናሽናል ስቴድዮም ተከናውኖ ባህርዳር ከተማ 3-0 በመርታት ከመሪዎቹ ተርታ መሰለፍ ችሏል። የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ጌታሁን ገብረጊዮርጊስን ያሰናበተው ደሴ ከተማ በምክትሉ ቴዎድሮስ ቀነኒ እየተመራ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ባህርዳር ከተማ በበ34ኛ ደቂቃ የሳላምላክ ተገኝ ጎል የመጀመርያውን አጋማሽ በ1-0 መሪነት ወጥተዋል። ከዕረፍት መልስ ባህርዳሮች በ61ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት እንዳለ ከበደ ወደ ግብነት ለውጦ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ሲያደርግ በ75ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞ የባንክ ተጫዋች ደረጀ መንግስቴ አስቆጥሮ ጨዋታው በባህርዳር 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 22 በማድረስ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *