ሶከር-ህግ | የመጫወቻ ሜዳ ቅድመ ሁኔታዎች

ከእግር ኳስ ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ህጎች ፣ መመሪያዎች እና ደንቦችን በምንመለከትበት የሶከር-ህግ አምዳችን የመጀመሪያ ክፍል ስለ ጨዋታ ውጪ እና ቅጣት ምት ህግጋት ማስነበባችን ይታወሳል። በዛሬው ፅሁፋችን ደግሞ የመጫወቻ ሜዳዎች ቅድመ ሁኔታዎችን እና የሀገራችን እግርኳስ ተጨባጭ ሁኔታን እንዳስሳለን።


በሳሙኤል የሺዋስ እና ብሩክ ገነነ


እንደሚታወቀው በሀገራችን በተለያዩ ከተሞች አዳዲስ እና ግዙፍ ስቴዲየሞች እየተሰሩ ነው፤ አንዳንዶቹም የግንባታ ሂደታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባህር ዳር፣ መቐለ፣ ሃዋሳ እና ወልዲያ የተገነቡ ዘመናዊ ስቴዲየሞችም ጨዋታዎችን እያስተናገዱ ነው። ቢሆንም በአብዛኛው የሀገር ውስጥ ውድድሮችን የሚያስተናግዱ ሜዳዎች ከስፋት እና ርዝመት አንፃር እንኳን በፊፋ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ካለማሟላት ጀምሮ አመቺ ያልሆነ የመጫወቻ ወለል ድረስ የተለያዩ ችግሮች ይስተዋሉባቸዋል።


ፊፋ በደንብ መፅሀፉ ላይ ያስቀመጣቸውን እና በማህበሩ አባላት ስር የሚደረጉ የእግርኳስ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ሜዳዎች ሊያሟሉ የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንመልከት።


የሜዳው አይነት

አንድ የመጫወቻ ሜዳ ከተፈጥሯዊ አልያም ከሰው ሰራሽ ሳር፤ ህጉ በሚፈቅድባቸው ውድድሮች ደግሞ ሁለቱንም ያቀላቀለ (Hybrid) ሆኖ ሊሰራ ይችላል። የሰው ሰራሽ ሳሩ ቀለም አረንጓዴ፣ ደረጃውም በፊፋ የጥራት ፕሮግራም የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟላ ሊሆን ይገባል። ይህም የሚወሰነው በውድድሩ ደንብ መሰረት ነው (ሰው ሰራሽ ሜዳን የማይፈቅዱ ውድድሮች አሉ)::

የጨዋታ ሜዳ መጠን በርዝመቱ እና ስፋቱ ይለካል።
ትልቁ የርዝመት መጠን 120 ሲሆን ትንሹ 90 ሜትር ነው።
በስፋት ደግሞ ትልቁ 90 ሜትር፣ በትንሹ ደግሞ 45 ሜትር ሊሆን ይገባዋል። ሆኖም በሀገራዊ ጨዋታዎች ላይ የርዝመቱ እና ስፋቱ ቁጥር በጥቂቱ ሊያንስ ይችላል።


ሜዳ ላይ የሚሰመሩ መስመሮች

የአራት ማዕዘን ቅርፅ ያለው የመጫወቻ ሜዳ ቦታዎችን የሚያመላክት ነጭ መስመር ይኖረዋል። የመሃል ሜዳው ክብ 9.15 ሜትር ራዲየስ ሊኖረው እንደሚገባ ደንቡ ያስቀምጣል።

– መስመሮቹ የተለያዩ የጨዋታ ቦታዎችን ለመከለል ይጠቅማሉ።

– የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን 16.5 ሜትር ርዝመት አለው።

– የፍፁም ቅጣት ምት መምቻ ነጥብ ደግሞ ከጎሉ 12 ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

– ከሳጥኑ ጫፍ ላይ 9.5 ሜትር ርዝመት ያለው አርክ (ግማሽ ጨረቃ) ይሰመራል። ጥቅሙም ፍፁም ቅጣት ምት ሲመታ ተጫዋቾች የሚቆሙበትን ቦታ መጠቆም ነው።

– የማዕዘን ምት መምቻ ጋር የሚገኘው እንጨት ከ1.5 ሜትር መብለጥ የሌለበት እና ሹል ያልሆነ እንዲሆን በህገ ደንቡ ተፅፏል።

– የማዕዘን ምት መምቻ ጋር ያለው አርክ ከ1 ሜትር ማነስ የለበትም።


ጎል

የጎሉ ስፋት 7.32 ሜትር ቁመቱ ደግሞ 2.44 ሜትር መሆን አለበት። የጎሉ ቋሚ እና አግዳሚ በቀለም ነጭ፣ በስፋት ደግሞ እኩል እና ከ12 ሴንቲሜትር ያልበለጡ መሆን ይገባቸዋል።


ቴክኒካል ቦታ

የቴክኒካል ቦታ አሰልጣኞች እና የቡድኖች የቴክኒክ ሰራተኞች የሚቆሙበት ሲሆን በየስቴዲየሙ ቢለያይም መሰረታዊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች አሉት።

– ከመጫወቻ ሜዳው ቢያንስ 1 ሜትር ርቆ ይገኛል።
– የቴክኒካል ቦታውን የሚያሳየው መስመር በግልፅ መታየት ይኖርበታል።
– በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ሰው በቴክኒካል ቦታ ላይ እንዲቆም አይፈቀድም።
– አሰልጣኙ እና ሌሎች ሰራተኞች የጨዋታውን ስርዓትን ማክበር እና ምግባረ ሰናይ ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል።


በአውሮፓ ሃገራት ሊጎች የውድድሩ ሻምፒዮን፣ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና ኮከብ ተጫዋቾች ተመርጠው እንደሚሸለሙት ሁሉ በውድድር ዓመቱ የክለባቸውን የመጫወቻ ሜዳ ተንከባክበው ለጨዋታ አመቺ እንዲሆን ያደረጉ የሜዳ ሃላፊዎችም እውቅና ይሰጣቸዋል። ዘመናዊ መንገዶችን በመጠቀም ሜዳዎችን የሚንከባከቡት እና ከዛም አልፎ በተለያዩ ዲዛይኖች የሚያስውቡት እነዚህ ሰራተኞች እንደ ተጫዋቾቹ ሁሉ ከፍተኛ የፊርማ ክፍያ እና የደመወዝ ስምምነት እያደረጉ ከአንድ ክለብ ወደ ሌላው ሲዘዋወሩ የሚታይበት አጋጣሚም አለ።

በሃገራችን ከመጫወቻ ሜዳ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ሁሉም የእግርኳስ ቤተሰብ በግልፅ የሚያውቀው ነው። በእግርኳሳችን ያሉ የታክቲክ፣ ቴክኒክ እና አካል ብቃት ማነስ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ተጫዋቾች ከሜዳ አለመመቸት የተነሳ ኳስ በአግባቡ መቀባበል ባለመቻላቸው ፍሰት ያለው ጨዋታ ለማየት ሳንታደል ቀርተናል። ተጫዋቾችም ከሜዳው ጥራት መጉደል የተነሳ ለጉዳት የሚጋለጡበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ቀደም ሲል የተዘረዘሩትን የሜዳ ጥራት ቅድመ ሁኔታዎች በአግባቡ የሚያሟሉት ስቴዲየሞችስ ስንት ናቸው የሚለው መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ

የብሔራዊ ቡድኖች እና የክለቦቻችን ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በሃገራችን ስታዲየሞች በሚስተናገዱበት ጊዜም የመጫወቻ ሜዳዎቻችን ዝቅተኛ ጥራት በአፍሪካ እና በዓለም መነጋገሪያ ሆኖ መጥፎ ገፅታ ሲያሰጠንም ተስተውሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ2 ዓመታት በፊት አልጄሪያን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አስተናግዶ 3-3 በተለያየበት ጨዋታ ላይ የነበረው ዝቅተኛ የሜዳ ጥራት በተለያዩ ኢንተርናሽናል ጋዜጠኞች እና ተመልካቾች መነጋገሪያ የነበረበት ሂደት ለዚህ አንድ ማሳያ ነው። በወቅቱ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የሌስተር ሲቲ የሻምፒዮንነት ጉዞ ትልቁን ሃላፊነት ሲወጣ የነበረው ሪያድ ማህሬዝ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሜዳ ምክኒያት ጉዳት እንዳያጋጥመው በክለቡ ማህበረሰብ ውስጥ ስጋት ፈጥሮ እንደነበርም ይታወሳል።


በእግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል ሁሉን አቀፍ የሆነ የስታዲየሞች የመጫወቻ ሜዳ ወለልን ጨምሮ፣ የተመልካቾች መቀመጫ፣ የቡድኖች መልበሻ ክፍል እና የቴክኒካል ስፍራ፣ ከዚያም አልፎ በስታዲየሙ ያሉ የመፀዳጃ ቤቶች ድረስ የሚቆጣጠር መመሪያ አለመኖር ለችግሩ ትልቁን አስተዋፅኦ አድርጓል። በዓመት ለአንድ ተጫዋች በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጡት የፕሪምየር ሊጋችን ክለቦች በሜዳቸው ላይ መሻሻሎችን ለማድረግ አቅም እንደማያንሳቸው ግልፅ ነው። ፌዴሬሽኑ በየሊጎቹ ለመሳተፍ ግዴታ የሆኑ ዝቅተኛ የስታዲየም ደረጃዎችን በማውጣት እና ይህንን የማያሟሉ ክለቦች በውድድሮቹ እንዳይሳተፉ በማገድ ክለቦቹ የበጀታቸውን የተወሰነ ክፍል በስታዲየም መሠረተ-ልማት ላይ እንዲያውሉ ሊያስገድድ ይችላል።

አብዛኞቹ የሃገራችን ክለቦች የራሳቸው ንብረት የሆነ ስታዲየም ባይኖራቸውም በሚገለገሉባቸው ስታዲየሞች ያሉትን የመጫወቻ ሜዳዎች አመቺ የሆነ የተፈጥሮ ወይንም የሰው ሰራሽ ሳር በማልበስ አስፈላጊውን እንክብካቤ ቢያደርጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ። በሃገሪቱ የተለያዩ ከተማዎች እየተገነቡ የሚገኙ ግዙፍ ስቴዲየሞችም ለሜዳው ጥራት ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን የሜዳ እንክብካቤ እና የውሃ ማስረጊያ ዘዴዎችን በማካተት መገንባታቸው ለስታዲየሞቹ ዘላቂ ጠቀሜታ ወሳኝ ነው። እግር ኳሳችን እንዲያድግ ከተፈለገ ደንብን ያከበሩ እና ጥራታቸውን የጠበቁ የመጫወቻ ሜዳዎች በሁሉም ውድድሮቻቸን ያስፈልጉናልና በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲደረግ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *