​” አሰልጣኞች ለመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ነፃነት መስጠት አለባቸው ” ኄኖክ አዱኛ 

ጅማ አባጅፋር በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ የውድድር ዘመን ተሳትፎው በአንደኛው ዙር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች አጠናቆ ባስመዘገበው ውጤት በሊጉ የመሪዎቹን ጎራ መቀላቀል ችሏል። በዚህ የቡድኑ የስኬት ጉዞ ውስጥ ትልቁን አስተዋፆኦ በማበርከት ላይ ከሚገኙ ቁልፍ የቡድኑ ተጫዋቾች መካከል ኄኖክ አዱኛ አንዱ ነው።

ኄኖክ የዘንድሮ የውድድር አመት ከመጀመሩ አስቀድሞ በአአ ሲቲ ካፕ ላይ ባሳየው ጥሩ አቋም ሁለት ጊዜ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ መመረጥ ችሏል። በዚህ አቋሙ መነሻነትም በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የአሰልጣኝነት ዘመን ለመጀመርያ ጊዜ ለኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦለት መጫወት ችሏል። አሁንም በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ለጅማ አባጅፋር ጥሩ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ኄኖክ የማጥቃት ተሳትፏቸው ከፍተኛ ከሆኑ የመስመር ተከላካዮች መካከል አንዱ ሲሆን ይህ የሆነበትን ምክንያትም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ አስረድቷል። 

” ዋናው ነገር አሰልጣኞች የሚሰጡት ነፃነት እና የጨዋታ አቀራረብ ነው። አሰልጣኞች የመስመር ተከላካዮች ወደ ፊት በመሄድ የማጥቃት እንቅስቃሴውን ማገዝ የሚችሉበት እንቅስቃሴ መፍጠር እና ነፃነት መስጠት አለባቸው። እኔ በግሌ የማደርገው ጥረት ቢኖርም አሰልጣኝ ገብረመድህን እየሰጠኝ የሚገኘው ነፃነት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ‘ አንተ ተከላካይ ነህ። ተከላከል ፤ ቁም ‘ አይለኝም። ወደ ፊት ሄደህ ተጫወት ብሎ ነው የሚፈቅድልኝ። እሱ የሚሰጠኝን ነፃነት ተጠቅሜ ያለኝን አቅም አውጥቼ መጫወት መቻሌ ነው በማጥቃት ሂደቱ በተደጋጋሚ ከመስመር እየተነሳሁ ወደ ፊት እንድሄድ ያደረገኝ ብዬ የማስበው። 

” የውጭ የሊግ ውድሮችን እንደምናየው ሁሉንም ማለት ይቻላል የመስመር ተከላካዮች ወደ ፊት በመሄድ ማጥቃቱን ያግዛሉ። ለእኔ የሚያሰለጥነኝ አሰልጣኝ በዚህ ረገድ ወደ ፊት እንድሄድ ነፃነቱን በመስጠት አግዞኛል ። በፍፁም ቆሜ መጫወት አልፈልግም። ወደ ፊት በመሄድ ቶሎ ቦታዬ ላይ ክፍተት እንዳይኖር እመለሳለው ። ይህን ድርሻ ተጨዋቾቹ መወጣት የሚችሉት በአሰልጣኙ ነው። አብዛኛው ቡድን ደግሞ አቻ ውጤትን ስለሚፈልግ ይህን ማድረግ አልቻሉም። እኔ የምመክራቸው ግን ወደ ፊት ሄደው እንዲጫወቱ ነው። ” ሲል ስለማጥቃት አበርክቶቱ ያስረዳል። አክሎም በተደጋጋሚ ልምምድ ብቃቱን ማሻሻል እንደቻለ ይናገራል።

” ደጋግሞ በመስራት ከልልምምድ የተገኘ ነው ብዬ የማስበው። ሁሌም የቆሙ ኳሶች እና በፍጥነት የሚሄዱ ኳሶችን እንዴት ማሻገር እንዳለብኝ እሰራለው። ከዚህ በተጨማሪ ፍጥነቴን ለማምጣትም ሆነ ጉልበቴን ለማጠንከር ከመደበኛ ልምምድ ውጭ ጂም ላይ እሰራለው እነዚህ ነገሮች የረዱኝ ይመስለኛል ። ከዚህ በተረፈ አብረውኝ የሚጫወቱ የቡድን አጋሮቼ ድጋፍ ነው ። ጅማ ከመጣው በኋላ በጣም መሻሻል እያሳየሁ እገኛለው በዚህም ደስተኛ ነኝ ። ”

ጅማ አባጅፋር በሊጉ የመጀመርያ አመት ተሳትፎ ጥሩ አጀማመር ባያደርግም በሒደት ወደ ውጤታማነት በመምጣት መልካም ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። የመጀመርያውን ዙርም 2ኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቅ ችሏል። ኄኖክ እና የቡድን አጋሮቹም ቡድኑ ስላሳየው መሻሻል እና ስለ አስደናሺ የውድድር አመታቸው እንዲህ ይላል። ” አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም ዝግጅታችን አጭር ነበር የተወሰኑ ተጨዋቾች ጉዳት ነበሩበት። ከዛ ባለፈ በመጨረሻ ደቂቃ በሚቆጠሩ ጎሎች ነጥብ እንጥል ነበር። ከሜዳ ውጭም ስንጫወት በጣም ጫናዎች ይኖራሉ። ከተወሰኑ ሳምንት በኋላ ግን ከፍተኛ መሻሻል እያሳየን በሜዳችን አብዛኛውን ነጥብ ሰብስበን በደረጃ ሰንጠረዡ ውስጥ መግበት ችለናል ያለን ነገር ጥሩ ነው። በሁለተኛው ዙር በተሻለ ሁኔታ በመቅረብ ለዋንጫ እንጫወታለን። ”

በሀላባ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ክለቦች አሳልፎ ዘንድሮ ጅማ አባጅፋርን ለተቀላቀለው ኄኖክ አመቱ በክለብ ደረጃ ስኬታማ እየሆነበት የሚገኝበት ከመሆኑ በተጨማሪ ለመጀመርያ ጊዜ የብሔራዊ ቡድኑን ማልያ የለበሰበት ነው። አቋሙን ጠብቆ በመንቀሳቀስም በመደበኛነት የዋልያዎቹ ተሰላፊ የመሆን ህልሙን ገልጿል። ” አሁን አቋሜ ጥሩ ነው።  ይህን አቋሜን ጠብቄ ለመዝለቅ በጣም ጠንክሬ እሰራለው ። ለብሔራዊ ቡድን በመጫወት ሀገሬን ማገልገል ትልቁ ሀሳቤ ነው ። በብሔራዊ ቡድን መጫወት የሚፈጥረው ስሜት ትልቅ ነገር ነው። በ2020 የቻን ውድድር ላይ በተለይ መጫወት እፈልጋለው። ለዚህም በምችለው ሁሉ ጠንክሬ እሰራለው። የወደፊቱ ጥሩ ይሆናል ብዬም አስባለው ። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *