​ዳዊት እስጢፋኖስ መከላከያን ዳግም ተቀላቀለ

ፋሲል ከተማን በዘንድሮ አመት ተቀላቅሎ የነበረው ዳዊት እስጢፋኖስ ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ ከክለቡ ጋር ስምምነት መለያየቱ ይታወሳል። ዳዊት ቀጣይ ማረፊያው ድሬዳዋ ከተማ አልያም መቐለ ከተማ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም የቀድሞ ክለቡ መከላከያን መቀላቀሉ ተረጋግጧል። 

በ1990ዎቹ መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው ቡድን ያደገው ዳዊት እስጢፋኖስ በሚሌንየሙ መጀመርያ መከላከያን ተቀላቅሎ ሁለት መልካም የውድድር ዘመናትን በማሳለፍ ወደ ደደቢት አቅንቷል። ከ7 አመታት ቆይታ በኋላም ዳግም ወደ ጦሩ ቤት የሚመልሰውን ኮንትራት ተፈራርሟል። መከላከያ አምበሉ ሚካኤል ደስታን ከለቀቀ በኋላ በአማካይ ክፍሉ የታየውን መሳሳት ለማሻሻል በዳዊት ዝውውር ላይ ተስፋውን ጥሏል።

ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገው ዳዊት እስጢፋኖስ ያለፉትን ሦስት አመታት ተረጋግቶ በአንድ ክለብ ከመጫወት ይልቅ ወደተለያዩ ክለቦች የመዟዟሩን ምክንያት ያብራራ ሲሆን በቀጣይ ግን ከመከላከያ ጋር የተረጋጋ ጊዜ ማሳለፍ እንደሚችል ገልጿል። ” አዎ ይህን ሦስት አመት የመርጋት ነገር የለም። ከፋሲል ከተለያየሁበት ምክንያት ውጭ ከሌሎች ክለቦች ጋር የተለያየሁት ክለቦቹ አብሬያቸው እንድቀጠል እየፈለጉ ከጥቅም ጋር በተያያዘ የተሻለ ክፍያ ለማግኘት ስል ነው የምለቅ የነበረው። በኢትዮዽያ እግርኳስ ውስጥ ረጅም አመት እንደመጫወቴ አሁን ወደ ማብቅያዬ አካባቢ ስሆን መጠቀምን አፈልጋለሁ። በዚህ ምክንያት ነው ክለብ ልቀያይር የቻልኩት ”
ዳዊት አክሎም ከፋሲል ከተማ ጋር የተለያየበትን ምክንያት ተናግሯል። ” ከአሰልጣኙ ጋር የአጨዋወት ፍልስፍና ጋር በተያያዘ መስማማት አለመቻል ነው። ለሌሎች ተጫዋቾች ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ለእኔ አለመሰጠቱ የአቅም ችግር እንደሌለብኝ ማሳያ ነው። ” ብሏል።

ዳዊት እስጢፋኖስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ መከላከያ ፣ ደደቢት ፣ ኢትዮዽያ ቡና ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከተማ ተጫውቷል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *