ወላይታ ድቻ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በፕሪምየር ሊግ ሊጉ እና በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በወቅታዊ መልካም ጉዞ ላይ የሚገኘው የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀው ወላይታ ድቻ ሁለት ተጫዋቾችን ለሁለተኛው ዙር ወደ ክለቡ አምጥቷል። ከአርባምንጭ ጋር የተለያየው ታዲዮስ ወልዴ ለአንድ አመት የውል ኮንትራት ሲፈርም ፀጋዬ ባልቻ ደግሞ ከሲዳማ ቡና እስከ ውድድር ዘመን ፍፃሜው ድረስ በውሰት ውል ወደ ክለቡ አምርቷል።

ታዲዮስ አርባምንጭ ከተማን በስምምነት ከለቀቀ በኋላ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅሏል ቢባልም ከክፍያ ጋር በተያያዘ ከክለቡ ጋር ከስምሞነት ባለመድረሱ ምክንያት ኮንትራት ሳይፈርም ቀርቶ ወላይታ ድቻን ተቀላቅሏል፡፡

ሌላኛው ክለቡን የተቀላቀለው ፀጋዬ ባልቻ ነው። የቀድሞው የወልቂጤ ከተማ የመስመር አጥቂ ፀጋዬ ወልቂጤን በመልቀቅ ሲዳማ ቡና ተቀላቅሎ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን መልካም እንቅስቃሴን ቢያደርግም ዘንድሮ ግን እድል በማጣቱ ምክንያት ተጫዋቹ ቀሪ የግማሽ ወራት ውል ከሲዳማ ጋር እያለው በውሰት ውል እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ ድረስ ለወላይታ ድቻ የሚጫወት ይሆናል።

ወላይታ ድቻ ባለፈው ሳምንት ዮናታን ከበደን መስፈረሙ የሚታወስ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ተጨማሪ ጠንካራ የሚሏቸው ተጫዋቾችን ባላቸው ክፍት ቦታ ላይ ለማስፈረም እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *