ለዳኞች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ትላንት ተጠናቀቀ

ለ120 የፕሪምየር ሊግ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች ከመጋቢት 1 ለተከታታይ አራት ቀናት በተሻሻሉት የጨዋታ ህጎች ዙርያ እና የብቃት ደረጃቸውን ለማሳደግ የሚረዳ በኢትዮዽያውያን ኢንስትራክተሮች አማካኝነት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ትላንት ማምሻውን ተጠናቋል።
ስልጠናው በመሰረታዊነት የህግ አተገባበርን አስመልከወቶ በተግባር እና በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ለጨዋታ አመራሮች ማለትም ለዳኞች እና ለውድድር ታዛቢ ኮሚሽነሮች ግንዛቤ ለመስጠት ታስቦ በኢትዮዽያ ዳኞች ብሔራዊ ኮሚቴ አዘጋጅነት በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ ነበር። በመጀመርያው ምዕራፍ ስልጠናው ከመጋቢት 1 – 2  ድረስ በአዲስ አበባ ስታድየም የተግባር ስልጠና ( የአካል ብቃት ፈተና ) የተሰጠ ሲሆን ኤም ኢንስትራክተር በሆኑት በፍቃዱ ግርማ እና ፍስሀ ገ/ማርያም አማካኝነት በተሰጠው ስልጠና በዋናነት ያተኮረው ዳኞች ያሉበትን የአካል ብቃት ደረጃን ለማወቅ እና በውድድር ወቅት እንዲሁም በልምምድ ጊዜ ምን ሊያደርጉ እንደሚገባቸው ስልጠና እና ፈተና ተሰጥቷቸዋል። በዚህ የሁለት ቀን ስልጠና ከተጠናቀቀ በኋላ በተሰጠው ፈተና ከአንድ ዋና ዳኛ ፈተናውን መውደቅ በስተቀር ሁሉም ዳኞች የአካል ብቃት ፈተናውን በአግባቡ ማለፍ ችለዋል።  ሆኖም በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ላይ በብቃታቸው ላይ ጥያቄ የሚነሳባቸው የተወሰኑ ዳኞች የአካል ብቃት ፈተናውን አለመውሰዳቸውን ለማወቅ ችለናል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ስልጠና ከመጋቢት 3 – 4 ድረስ በንድፈ ሀሳብ እና በምስል በታገዘ አቀራረብ  በኢትዮዽያ ሆቴል ኤም ኢንስትራክተር በሆኑት ግዛቴ አለሙ ፣ ሽፈራው እሸቱ እና ሰለሞን ገ/ስላሴ አማካኝነት  የሙሉ ቀን ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል። ይህ ሁለተኛ ስልጠና በዋናነት ያተኮረው አዳዲስ በተሻሻሉ ህጎች ዙርያ ፣ የህግ አተረጓጎም ፣ ዳኞች በህብረት ጨዋታን መምራት በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ሲሆን ከ17 የጨዋታ ህጎች ውስጥ ከአንዱ በስተቀር በተሻሻሉ ህጎች ላይ ለምሳሌ የተጨዋች ቅያሪ ፣ የቅጣት እና የጥፋት ውሳኔ አሰጣጥ ፣ የተጨዋቾች ትጥቅ አጠቃቀም ፣ ከጨዋታ ውጭ የሚሰሩ ጥፋቶች ፣ ከስፖርታዊ ስነ ስርአት ውጪ ለሚሰሩ ጥፋቶች እና በሌሎች መሰረታዊ የተሻሻሉ ህጎች ዙርያ ዳኞች የህግ አተገባበር ብቃታቸው እንዴት ነው የሚለውን ስልጠና ተሰጥቷል።

እስከ ዛሬ ከተወሰዱ ስልጠናዎች በብዙ ነገሩ የተለየ እንደሆነ በተነገረለት በዚህ ስልጠና ዳኞች ከፍተኛ እውቀት ያገኙበት እንደሆነ እና በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛው ዙር ውድድር ላይ ለሚተገበሩ አዳዲስ ህጎች እንዲሁም ዳኞችን በየጨዋታው የሚሰሩትን ስህተቶችን ለመቀነስ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል ። ስልጠናው በዋናነት በዚህ ወቅት የተሰጠበት ምክንያት በአንደኛው ዙር ላይ በዳኞች የተፈጠረውን ክፍተት ለማጥበብ ታስቦ እንደሆነም ለማወቅ ችለናል።

በመጨረሻም የፌዴሬሽኑ አመራሮች እና ፕሬዝደንቱ አቶ ጁነይዲ ባሻ በመዝግያው ላይ በመገኘት መልክት በማስተላለፍ ስልጠናው ተጠናቋል ።

ስልጠናው በቀጣይ በተለያዩ ጊዚያት በተሻሻሉ ህጎች አተገባበር ዙርያ ለተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች እንዲሁም ለስፖርት ቤተሰቡ እንዲሰጥ ቢደረግ መልካም ነው እንላለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *