ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታን ይመራሉ

የቶታል ካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ፡፡ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ በሚደረጉት ወሳኝ ፍልሚያዎች ላይ የሚመሩ አርቢትሮችን ካፍ አስቀድሞ ያሳወቀ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን አርቢትሮችም እድሉን አግኝተዋል፡፡

ኬፕ ታውን ደቡብ አፍሪካ ላይ ኬፕ ታውን ሲቲ ከሞዛምቢኩ ክለብ ዴስፖርቲቮ ኮስታ ዶ ሶል የሚያደርጉት ጨዋታ ኢትዮጵዊያን ዳኞች ይመሩታል፡፡ በላይ ታደሰ የመሃል ዳኛ ሲሆን ሃይለራጉኤል ወልዳል እና በላቸው ይታየው ረዳቶቹ ሆነዋል፡፡ ዘንድሮው የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅን ያገኘው ዳዊት አሳምነው አራተኛ ዳኛ ሆኗል፡፡ በላይ ከዚህ ቀደም በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪ ዳሬ ሰላም ላይ ያንግ አፍሪካንስ የሲሸልሱን ሴንት ሉዊን 1-0 የረታበትን ጨዋታ በመሃል አርቢትርነት መመምራት ችሏል፡፡ በታዋቂው የቀድሞ የባፋና ባፋና አጥቂ ቤኒ ማካርቲ የሚመራው ኬፕ ታውን ሲቲ በመጀመሪው ጨዋታ ማፑቶ ላይ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡

በተያያዘ ዛማሌክ የኢትዮጵያዊውን ወላይታ ድቻ ካይሮ ላይ በሚያስተናግድበት ጨዋታ ኬንያዊያን ዳኞች በካፍ ተሹመዋል፡፡ የመሃል አርቢትር ዴቪስ ኦምዌኖ ረዳቶቹ ጊልበርት ቼሮይት እና ኦሊቨር ኦዲሃምቦ ጨዋታ የሚመሩ ይሆናል፡፡ ሉጎጎ ላይ ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ (ኬሲሲሴ) ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚያስተናግድበት ጨዋታም በተመሳሳይ ኬንያዊ አርቢትሮች ይመሩታል፡፡ አንድሪዊ ኦቴኖ በስታር ታይምስ ስታዲየም ቅዳሜ የሚደረገውን ጨዋታ ይመራል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *