ወላይታ ድቻ በአልሰላም ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመርያ ዙር የመልስ ጨዋታ ነገ ዛማሌክን የሚገጥመው ወላይታ ድቻ ትላንት 42 የልዑካን ቡድን አባላትን አካቶ ወደ ስፍራው በማቅናት ኖቫ ሆቴል ማረፊያውን አድርጓል።

የጦና ንቦች ትላንት ከሰአት በካይሮ ስታዲየም ሁለተኛ የመለማመጃ ሜዳ ላይ የመጀመርያ ልምምዳቸውን የሰሩ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ጨዋታውን በሚያደርጉበት አል ሰላም ስታድየም በእኛ አቆጣጠር 1 ሰአት ላይ የመጨረሻ ልምምዳቸውን አከናውነዋል። በዛሬው ልምምድ ከኳስ ጋር የተያያዙ ስራዎችን ቀለል ባለ መልኩ ለአንድ ሰአት ያክል የሰሩ ሲሆን የዛማሌክ የመስመር አጨዋወትን መመከት ላይ ያተኮረ ፣ ሜዳውን ለመላመድ በሁሉም የሜዳ ክፍል ኳስ መቀባበልን እና የኳስ ቁጥጥርን የተመለከቱ ስራዎች ሲሰሩ ምናልባት ጨዋታው ወደ መለያ ምት ከተሸጋገረ በሚል በመጨረሻ የልምምዱ አካል የመለያ ምቶች ልምምድ ሆኗል፡፡

ወላይታ ድቻን ለመደገፍ ወደ ስፍራው ትላንት በርከት ያሉ ደጋፊዎች ያቀኑ ሲሆን በግብፅ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያኖችም ክለቡን ለመደገፍ እንደተዘጋጁ ተገልጿል፡፡ ደጋፊዎቹ ከወዲሁ ቡድኑን በማነቃቃት ላይ ከመገኘታቸው በተጨማሪ ኢትዮጵያዊው የፔትሮጄት አማካይ ሽመልስ በቀለ ለጨዋታ ወደ አሌሳንድሪያ ከማምራቱ ቀደም ብሎ ቡድኑን ይጎበኛል ተብሏል።

ጨዋታው ነገ ከምሽቱ 1 ሰአት ላይ 30 ሺህ ተመልካቾችን በሚያስተናግደው አልሰላም ስታዲየም ሲደረግ አራቱም ዳኞች ከኬንያ ተመድበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *