እስራኤል ሻጎሌን ተዋወቁት

እስራኤል ሻጎሌ ይባላል። የአጥቂ መስመር ተጨዋች ነው። የኢትዮጵያ ከ20 አመት ብሔራዊ ቡድን አባል ሲሆን በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጎልተው ሊወጡ ከሚችሉ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው።

እስራኤል ባለፈው አመት ከአርባምንጭ ተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለ ቢሆንም የመሰለፍ እድል ሳያገኝ ቀርቶ በዘንድሮ አመት አሰልጣኝ እዮብ ማለ ቡድኑን ከተረከበ ጀምሮ የመታየት እድልን ማግኘት እየቻለ ነው። አሰልጣኙ በሁለተኛው ዙር የአጥቂ መስመር ክፍተታቸውን ለመድፈን እምነት ከጣሉባቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው። ይህ ፈጣን አጥቂ በአሁኑ ወቅት በኢትዮዽያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የተካተተ ሲሆን ወደፊት የተሻለ ደረጃ ይደርሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

በአርባምንጭ ከተማ ልዩ ስሙ ጫሞ ቀበሌ የተወለደው እስራኤል በአካባቢው በተቋቋመው ፓራዳይዝ ሎጅ ፕሮጀክት ውስጥ እግርኳስን መጫወት ጀመረ። ቀጥሎም 2006 ላይ የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የእግርኳስ አካዳሚን ተቀላቅሎ ሁለት አመት ከቆየ በኋላ በ17 አመት በታች ውድድር የአርባምንጭ ዞንን በመወከል ተጫውቷል። በውድድሩ ባሳየው እንቅስቃሴም 2008 ላይ ደቡብ ክልልን በመወከል የመላው ኢትዮዽያ ጨዋታ ላይ መሳተፍ ችሏል።

እስራኤል በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይም ምርጥ ብቃቱን በማሳየት ለ17 አመት በታች ቡድን የመመረጥ እድል አግኝቶ ነበር። ሆኖም የመጨረሻው ዝርዝር ሳይካተት ቀርቷል። እስራኤል በወቅቱ የተከሰተውን እንዲህ ያስረዳል። ” በ2008 ሀዋሳ ላይ በተካሄደው የመላው ኢትዮዽያ ጨዋታ ላይ ባሳየሁት ምርጥ እንቅስቃሴ አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ለኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን እንድጫወት መርጦኝ አዲስ አበባ በመምጣት የተወሰኑ ቀናት ልምምድ ሰርቼ ከቆየው በኋላ የዕድሜ ምርመራ አድርጌ ዕድሜህ አንድ ወር አልፎታል ተብዬ ወደቅኩኝ። በጣም ነበር የከፋኝ። ምክንያቱም ራሴን የማሳይበት መልካም አጋጣሚ ስለነበር ነው። አጋጣሚው አለመሳካቱ ውስጤ ቁጭት ፈጥሮብኝ አንድ ቀን ተመልሼ በመምጣት የኢትዮጵያን ማልያ እለብሳለው ብዬ ወደ አርባምንጭ ተመለስኩ። ”

የእስራኤል ቀጣይ ጉዞ ወደ አርባምንጭ ከተማ ነበር። ከአጭር ጊዜ የተስፋ ቡድን ቆይታው በኋላ በፍጥነት ወደ ዋናው ቡድን ቢያድግም በክለቡ የጨዋታ ተሳታፊዎች ዝርዝር ላይ ለመካተት  ረጅም ጊዜ ፈጅቶበታል። የአሰልጣኝ እዮብ ማለ ቡድኑን መረከብም ለእስራኤል ተስፋ የፈነጠቀ አጋጣሚ ሆኗል። ” ከአዲስ አበባ ከተመለስኩ በኋላ አርባምንጭ ከተማ ተስፋ ቡድን አስገቡኝ። እዛ ብዙም አልቆየሁም። ለሁለት ወር ጊዜ ብቻ ሰራውና በፍጥነት ወደ ዋናው ቡድን አድጌ መስራት ጀመርኩ። ይህ የሆነው 2009 ላይ ነበር። ዋናው ቡድን ከገባው በኃላ መጫወት እየቻልኩ እና አቅሙ እያለኝ ገና ልጅ ነው እያሉ ቁጭ አደረጉኝ ። በልምምድ ወቅት የተሻለ ነገር አሳይ ነበር። ሆኖም የመሰለፍ እድል ማግኘት አልቻልኩም። አንዱን አመት ልምምድ ብቻ እየሰራው ሳልጫወት ቆየሁ። በ2010 በተለይ አሰልጣኝ እዮብ ማለ ከመጣ ወዲህ በእኔ ፍላጎት እና እምነት ኖሮት በአቅሜ ተማምኖ ጥሩ ነገርም እየሰጠኝ በልምምድ እያዘጋጀኝ ወደ መጫወቱ መጥቻለው። ”

የአርባምንጩ ዋና አሰልጣኝ እዮብ ማለ በእስራኤል ብቃት የተማመነ ይመስላል። ቡድኑን በሁለተኛ ዙር በበርካታ ለውጦች ታጅቦ እያዘጋጀ የሚገኘው አሰልጣኙ ላለመውረድ ለሚያደርገው ትግል የወጣቱን አጥቂ ግልጋሎት እንደሚያገኝ ይናገራል። ” በጣም ጥሩ ነገር ያለው ተጫዋች ነው። እንደነዚህ ያሉ ተስፋ የሚጣልባቸው ተጫዋቾችን መጠቀም አለብን። ድፍረቱ ከእኛ አሰልጣኞች እንዲኖር ያስፈልጋል። እስራኤል በሁለተኛው ዙር ለሚጠብቀን ጠንካራ ውድድር ቡድኑን ይጠቅማሉ ብዬ ከማስባቸው ተጫዋች አንዱ ነው። ጠንክሮ ከዚህ በተሻለ መስራት ከቻለ ወደፊት ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችል ተጫዋች ነው ። ” ሲል በአጥቂው ላይ ተስፋ እንደጣለ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ቡድናቸውን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ። ከመረጧቸው ተጫዋቾች መካከልም በ17 አመት በታች ቡድን አሰልጣኝነታቸው ወቅት አይናቸውን ያሳረፉበትና በእድሜ ተገቢነት ምክንያት ሳይጠቀሙበት የቀሩት እስራኤል ነው። የብሔራዊ ቡድን ማልያን የመልበስ ምኞቱ ከ2 አመት በፊት ያልተሳካው እስራኤል አሁን አረንጓዴውን መለያ ለመልበስ ተቃርቧል። ” ይህ ዕድል የማይገኝ እድል ነው። ከሺዎች መሀከል የምታገኘው እድል ነው። ይህን እድል ለመጠቀም በጣም ስለምፈልግ ራሴን ለማሳየት ከልቤ ጠንክሬ እየሰራው ነው። አሁን 25 ውስጥ መግባት ችያለው። በዚህም ደስተኛ ነኝ። በቀሩት የልምምድ ወቅቶች አሰልጣኞቼ የሚሰጡኝን ምክር ተቀብዬ በመጀመርያ አሰላለፍ በመግባት መጫወት አስባለው። ብሔራዊ ቡድናችንም ረጅም ርቀት እንዲሄድ ለማድረግ የምችለውን ሁሉ እሰራለው። ” ሲል ህልሙን ገልጿል።

የደደቢቱ አጥቂ ጌታነህ ከበደን ምሳሌ የሚያደርገውና በቀጣይ አመታት ከግብ አዳኙ የበለጠ ደረጃ መድረስን የሚያልመው እስራኤል በእሱ የእድሜ ክልል ለሚገኙ ወጣቶች በሚያስተላልፈው መልዕክት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ቆይታ ቋጭቷል። ” እንደኔ አይነት እድል ያላገኙ ብዙ ተጫዋቾች አሉ። እድል ቢያገኙ ደግሞ ከማንም እንደማያንሱ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ኢትዮዽያ ውስጥ ችግር አለ። በወጣቶች ላይ የማመን ሁኔታ የለም። እድልን እየሰጡ ቢያዩ ውጤትም ሊመጣ እና ቡድኖችም ሊቀየሩ ይችላሉ። በብዛት ወጣቶች እድል ስላላገኙ እኔ በዚህ አጋጣሚ ያገኘሁትን እድል ተጠቅሜ ለእነርሱ አርአያ በመሆን መንገድ መክፈት እፈልጋለሁ ። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *