የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ [ክፍል አንድ]

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዙር ዛሬ በሚደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ሲጀመር መቐለ ፣ አዳማ እና አዲስ አበባ ላይ የሚካሄዱትን ጨዋታዎችን በክፍል አንድ የቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።


መቐለ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሆኖ ወደ መቐለ የሚዝጓ ሲሆን ከበድ ያለ ፈተና እንደሚጠብቀውም ይገመታል። መቐለ ከተማ ምንም እንኳን የመጀመሪያውን ዙር በመከላከያ ሽንፈት ገጥሞት ቢያገባድድም ከኢትዮጵያ ቡና ያለግብ ከተለያየበት ጨዋታ አስቀድሞ ሶስት ጨዋታዎችን በተከታታይ ማሸነፉ ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አግዞታል። በተመሳሳይ በፋሲል ከተማ ተሸንፎ የአመቱን አጋማሽ የጨረሰው አርባምንጭ ከተማ ከዚያ አስቀድሞ ከአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኃላ ድሬደዋን እና አዳማን አሸንፎ ከሀዋሳ አቻ የተለያየበት ሂደት ወደ መሻሻል የሚያመራው ይመስል ነበር። ሆኖም ቡድኑ ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ካገኘ ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ህልምን ሰንቋል። በአንፃሩ መቐለ ደግሞ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ቦታውን ለማደላደል እንደሚፋለም ይጠበቃል።

ከሌሎቹ የሊጉ ተሳታፊዎች ይልቅ በዝውውር መስኮቱ በርካታ ለውጦች ያደረጉት ሁለቱ ክለቦች ናቸው። መቐለ ከተማ ሚካኤል አኩፎ ፣ አለምነህ ግርማ ፣ ሙሉጌታ ረጋሳ ፣ ተመስገን አዳሙ ፣ ዱላ ሙላቱ ፣ ዮሴፍ ኃ/ማርያም እና ዮሴፍ ድንገቶ የለቀቃቸው ተጫዋቾች ናቸው። ለውጡ በተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ከሚጀምሩት ተጨዋቾች ውጪ በተጠባባቂነት የሚጠቀምባቸውን ተጨዋቾችን በመለውጥ ላይ ያተኮረ ነው። ክለቡ በተጠቀሱት ተጨዋቾች ምትክም ጋቶች ፓኖም ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና እያሱ በቀለን አስፈርሟል። አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በቡድኑ ውስጥ ወሳኝ ሚና የነበራቸውን ወንድሜነህ ዘሪሁን እና ገ/ሚካኤል ያዕቆብን እንዲሁም ሲሳይ ባንጫ ፣ ዮናታን ከበደ እና ታድዮስ ወልዴን ያሰናበተ ሲሆን በረከት አዲሱ ፣ ዘካርያስ ፍቅሬ እና ፍቃዱ መኮንን ተተኪዎቹ ተጨዋቾች ሆነዋል። አርባምንጭ በአመዛኙ ክፍተት ሲታይበት የነበረውን የፊት መስመሩን በማጠናከር ላይ ያተኮሩ ዝውውሮችን ፈፅሟል። ሆኖም አስልጣኝ እዮብ ማለ በቡድኑ ሌሎች ክፍሎች ላይ የሚታዩትን ችግሮችን በነባር ተጨዋቾች ለመቅረፍ ያሰቡ ይመስላሉ።

አርባምንጭ ከተማ ከሜዳው ውጪ ያለውን ጥሩ ያልሆነ ሪከርድ ከማሻሻል ባለፈ በዛሬው የመቐለ ጨዋታ ጥንቃቄን መርጦ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በመሆኑም ቡድኑ የአማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ጋይሳ አፖንግን የጥቃት መስመር በመቆጣጠር ከመልሶ ማጥቃት በሚገኙ እድሎች ጠንካራውን የባለሜዳዎቹን የኃላ ክፍል የሚፈትን ይሆናል። በጠንካራ የመከላከል መሰረት ላይ የተገነባው መቐለ ለኳስ ቁጥጥር እምብዛም ቦታ የማይሰጥ ቡድን ቢመስልም ከተጋጣሚው አቀራረብ አንፃር በሀብታሙ ተከሰተ ፣ ያሬድ ከበደ እና ሚካኤል ደስታ አማካይነት መሀል ሜዳ ላይ ሊያገኝ ከሚችላቸው የቅብብል ዕድሎች በመስመሮች በኩል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ፊት ላይ ለሚኖረው ብቸኛ አጥቂ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ዕቅድ እንደሚኖረው ይታሰባል። ያም ሆኖ ጨዋታው በቀላሉ ግብ የሚቆጠርበት አይመስልም።

መቐለ ከተማ አዲስ ፈራሚው ጋቶች ፓኖምን እና የመሀል ተከላካዩ አሌክስ ተሰማን በጉዳት እንዲሁም አመለ ሚልኪያስን በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ምክንያት የማይጠቀም ይሆናል። በአርባምንጭ በኩል ደግሞ ፀጋዬ አበራ በጉዳት እንዲሁም እስራኤል ሻጎሌ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በመካተቱ ምክንያት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ሆነዋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– የመቐለ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደግ ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ አርባምንጭ ላይ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን ያለግብ ነበር ያጠናቀቁት።

– መቐለ ከተማ እስካሁን በሊጉ ሜዳው ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት የገጠመው ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ ካስተናገዳቸው አራት ቡድኖች ስምንት ነጥቦችን ማግኘት ችሏል።

– እስካሁን ከሜዳው ውጪ ድል ቀንቶት የማያውቀው አርባምንጭ ከተማ ከሰባት ጨዋታዎች የአቻ ውጤት ማሳካት የቻለው በሁለቱ ብቻ ነበር።

ዳኛ

ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ሲሆን አርቢትሩ እስካሁን በዳኛቸው ስድስት የሊግ ጨዋታዎች 25 የቢጫ እና 3 የቀርድ ካርዶችን መዟል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


አዳማ ከተማ ከ ወልዲያ

አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም የሚደረገው ይህ ጨዋታ በበርካታ ወጣት ተጨዋቾች የተገነባው ባለሜዳውን ቡድን የተጫዋቾች እጥረቱን ለመሙላት በሂደት ላይ ከሚገኘው ወልዲያ ጋር የሚያገናኝ ነው። ብዛት ያላቸው የአቻ ውጤቶችን እያስመዘገበ የመጀመሪያውን ዙር ያገባደደው አዳማ ከተማ በሂደት እየተሻሻለ ቢመጣም የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎቹንም ነጥብ በመገራት ነው የጨረሰው። በ16 ቀናት ውስጥ አራት ጨዋታዎችን ያደረገው ወልዲያ ደግሞ ያገኛቸው ሰባት ነጥቦች ከደረጃው ግርጌ ቢያላቅቁትም የመጨረሻው የሶዶ ጉዞው ግን በሽንፈት የተደመደመ ነበር። ሆኖም ቡድኑ በቂ ተቀያሪ ተጨዋቾችን ሳይዝ ባደረጋቸው ተሰተካካይ ጨዋታዎቹ ያገኘው ስኬት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

አዳማ ከተማ በዝውውር መስኮቱ አንጋፋ ከሚባሉት ተጨዋቾቹ ጋር በመለያየት አሁንም ወጣቶችን ወደ ቡድኑ ማምጣቱን ገፍቶበታል። በዚህም ታፈሰ ተስፋዬን እና አላዛር ፋሲካን በሲዳማ ቡናው ጫላ ተሺታ እና በሀዋሳ ከተማው ፍርድአወቅ ሲሳይ ተክቷል። ክለቡ በወጣት ተጨዋቾች ላይ ያሳደረው እምነት ከፈጠረለት ውጤታማነት በመነሳት ተመሳሳይ መንገድን መምረጡ ይበል የሚያሰኝ ነው። በተለይም በሲዳማ ቡና ዕድል ተነፍጎት የቆየው ጫላ ተሺታ ከነባር ተጨዋቾች ብርቱ ፉክክር የሚጠብቀው ቢሆንም ጎልቶ በወጣበት የ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የነበረውን ብቃር መድገም ከቻለ ለአዳማ ስኬታማ ዝውውር እንደሆነ ከወዲሁ መናገር ይቻላል።

በሶስቱ ተጨዋቾቹ ላይ ዕገዳ ያስተላለፈው ወልዲያ መስፍን ኪዳኔ ፣ አሳልፈው መኮንን እና ሞገስ ታደሰን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። በሙከራ ላይ የነበሩት አልሳዲቅ አልማሂ እና በላይ ታደሰም በክለቡ የተፈለጉ ቢሆንም ተጨዋቾቹ ፊርማቸውን ከማኖራቸው በፊት የታገዱት ተጨዋቾች ጉዳይ መፈታት ያለበት በመሆኑ ዝውውራቸው እክል ገጥሞታል። ወልዲያ የተረጋጋ የመጀመሪያ አሰላለፍን ፈጥሮ ጥሩ የሚባል ቡድን ለመገንባት የዝውውር ጉዳዮቹን በጊዜ መጨረስ ይጠበቅበታል። በዚህ ሁኔታ ግን አሰልጣኙ የሚፈልገውን የጨዋታ ዘይቤ በቡድኑ ውስጥ ለማስረፅ እና በድግግሞሽም ለማጎልበት ሁለተኛው ዙር የራሱን የሆነ ከባድ ፈተና ይዞ መምጣቱ የማይቀር ነው። ቡድኑን በአዲስ መልክ ከተቀላቀሉት ተጨዋቾች መሀከል ግን መስፍን ኪዳኔ በመከላከያ የመጀመሪያው ዘር ጉዞ በበርካታ ጨዋታዎች መሰለፍ መቻሉ በፍፁም ገ/ማርያም የግራ መስመር ቦታ ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ጥሩ አማራጭ ያደርገዋል።

አዳማ ሜዳው ላይ ካለው ጥንካሬ አንፃር በዛሬው ጨዋታ ሙሉ የማጥቃት ኃይሉን ተጠቅሞ ጫና በመፍጠር እንደሚጫወት ለመገመት ቀላል ነው። የከንዐን ማርክነህ ፣ በረከት ደስታ እና ዳዋ ሁቴሳም ጥምረት በኤሚክሪል ቤሌንጌ ፊት ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለአዳማዎች የማጥቃት ሂደት ዋነኛ መሳሪያ እንደሚሆን ይጠበቃል። በጨዋታው በተለይ አማካይ ክፍላቸው ላይ በርካታ ተጨዋቾችን የሚያጡት ወልዲያዎች ሊመርጡት ከሚችሉት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት አንፃር ደግሞ አንጋፋው አጥቂ አንዷለም ንጉሴ በምኞት ደበበ ከሚመራው የአዳማ ከተማ የተከላካይ መስመር ጋር የሚገናኝባቸው አጋጣሚዎች ልዩነት ፈጣሪነታቸው የጎላ ይሆናል።

ሚካኤል ጆርጅ ፣ ሙጂብ ቃሲም ፣ ተስፋዬ በቀለ እና ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት ላይ የሚገኙ የአዳማ ከተማ  ተጨዋቾች ሲሆኑ አዲስ ፈራሚው ፍርዳወቅ ሲሳይም ለዛሬው ጨዋታ አይደርስም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወጣ ገባ አቋም እያሳየ የሚገኘው የቡልቻ ሹራ የመሰለፍም ጉዳይም አለየለትም። ወልዲያ ብሩክ ቃልቦሬ እና ምንያህል ተሾመን በጉዳት ሲያጣ አዲስ ፈራሚው ሞገስ ታደሰ አስቀድሞ ጉዳት አለብኝ ብሎ እስከ አሁን ከክለቡ ጋር ባለመኖሩ ምክንያት ለማሰናበት ከጫፍ እንደደረሱ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ሌሎቹ አዲስ ፈራሚዎች መስፍን ኪዳኔ እና አሳልፈው መኮንን ክለቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡

 

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በፕሪምየር ሊጉ 5 ጊዜያት ተገናኝተዋል፡፡ ሁለቱም ሁለት ጊዜ ድል ሲያስመዘግቡ አንድ ጊዜ አቻ ተለያተዋል፡፡ ቡድኖቹ በማሸነፍ ብዛት ብቻ ሳይሆን በማስቆጠሩት የጎል መጠንም እኩል ናቸው፡፡ (4 ጎሎች)

– በአዳማ አበበ ቢቂላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁለቱንም አዳማ ከተማ አሸንፏል፡፡

– በዚህ ዓመት በመጀመርያው ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ ወልዲያ በአንዷለም ንጉሴ እና ኤደም ኮድዞ ጎሎች 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ጎል (አንዷለም ንጉሴ) ፣ ፍፁም ቅጣት ምት (አንዷለም ንጉሴ) እና የማስጠንቀቂያ ካርድ (ተስፋዬ በቀለ) የተመዘገቡትም በዚህ ጨዋታ ላይ ነበር፡፡

– አዳማ ከተማን በሜዳው ማሸነፍ የማይታሰብ እየሆነ መጥቷል፡፡ አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ ሽንፈት ካጋጠመው ሁለት አመት ሊደፍን አንድ ወር ብቻ ቀርቶታል፡፡ ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ በሚያዝያ ወር 2008 በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፈ ወዲህ በሜዳው ካደረጋቸው 27 ጨዋታዎች 18 ድል እና 9 የአቻ ውጤቶች አስመዝግቧል፡፡ በተቃራኒው ተጋጣሚው ወልዲያ ከሜዳው ውጪ ዘንድሮ ምንም ጨዋታ አላሸነፈም፡፡  በአጠቃይ በሊግ ተሳትፎ ታሪኩ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው 43 ጨዋታዎችም ማስመዝገብ የቻለው ሁለት ድል ብቻ ነው፡፡

ዳኛ

ይህን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ ሚካኤል አርዓያ በዋና ዳኝነት ይመራዋል፡፡ ዘንድሮ 5 ጨዋታዎችን የመራው ሚካኤል 34 የማስጠንቀቂያ ካርድ ሲመዝ ምንም ቀይ ካርድ አላሳየም።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ፋሲል ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ፋሲል ከተማ ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎቹ መሀከል በሜዳው ያደረጋቸውን የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታዎች ማሸነፉ የሰበሰበውን የነጥብ ብዛት ከአምናው ጋር እንዲመጣጠን አድርጎታል። ሆኖም እስከ 11ኛው ሳምንት ድረስ ያለሽንፈት ከመጓዙ ጋር ሲነፃፀር ለመሪዎቹ የመቅረብ ሰፊ ዕድል እንደነበረው መናገር ይቻላል። ከመልካም አጀማመር በኃላ የቀዘቀዘው ወልዋሎ ዓ.ዩ ደግሞ ሀዋሳ ከተማን ሜዳዉ ላይ ያስተናገደበትን ጨዋታ ከማሸነፉ በቀር የመጨረሻዎቹን ሳምንታት ከውጤት ተራርቆ ቆይቷል። በፀጥታ ጉዳዮች ምክንያት አዲስ አበባ ላይ የሚደረገው ይህ ጨዋታ 2-2 እንደተጠናቀቀው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ሁሉ በፉክክር የተሞላ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ከዳዊት እስጢፋኖስ ፣ ሮበርት ሴንቴንጎ እና አቤል ውዱ ጋር የተለያየው ፋሲል ከተማ ሰንደይ ሙቱኩን እና ሀሚስ ኪዛን አስፈርሟል። በዐይናለም ሀይለ እና ያሬድ ባየህ ጉዳት ምክንያት የተጨዋች ሽግሽግ አድርጎ ቢቆይም ወደ መጨረሻው ላይ በርካታ ስህተቶችን ሲሰራ ለታየው የአፄዎቹ የኃላ ክፍል መጠናከር የሰንደይ ሙቱኩ መምጣት ጥሩ አማራጭ ይመስላል። ቡድኑ ሌላው ደካማ ጎኑ የነበረው የፊት መስመር አጥቂ ቦታ ላይም ብዙ ሚና ያልነበረው ሮበርት ሴንቴንጎን በአዲስ ተጨዋች መተካቱ ሌላ አማራጭ እንደሚፈጥርለት ይጠበቃል። አማካይ ክፍል ላይ ግን በዳዊት እስጢፋኖስ ምትክ የመጣ ተጨዋች አለመኖሩ ቡድኑ በነበረው ታታሪ እና ብዙ ሜዳ አካሎ የመጫወት ባህሪ ባላቸው የመሀል ክፍል ተሰላፊዎቹ ላይ ተመስርቶ የውድድር ዘመኑን ለማገባደድ እንዳሰበ የሚነግረን ነው።

ወልዋሎ ዓ.ዩ  ብሩክ አየለ ፣ ሔኖክ አየለ እና በለጠ ተስፋዬን አሰናብቶ የቀድሞውን የአፄዎቹ ግብ ጠባቂ ዮሀንስ ሽኩር ፣ አለምነህ ግርማ ፣ ማናዬ ፋንቱ እና ጋናዊው አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎን ወደ ቡድኑ አምጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም ከሳምንታት በፊት በአሰልጣኝነት በሾማቸው ፀጋዬ ኪነዳማርያም የሚመራ ይሆናል።

በዝውውሮቹ ሁለት አጥቂዎች መካተታቸው በአመዛኙ በሙሉአለም ጥላሁን ላይ ተጥሎ የነበረውን የፊት አጥቂነት ኃላፊነት በተለያዩ ተጫዋቾች ለማጠናከር ያሰቡ ይስመስላቸዋል። ከበረከት አማረ እና ዘውዱ መስፍን ብሩቱ ፉክክር የሚጠብቀው ቢሆንም  አምና በጉዳት ከመገለሉ በፊት በፋሲል አስገራሚ ግስጋሴ ውስጥ ትልቅ አስተዋፅኦ የነበረው ዮሀንስ ሽኩርም መምጣት ለቢጫ ለባሾቹ መልካም የሚባል ዜና ነው። ሆኖም ወልዋሎ ከዓለምነህ ግርማ መምጣት በተጨማሪ ብዙ ክፍተት ሲታይበት የነበረውን የቡድኑን የተከላካይ መስመር ውህደት በሚገባ አስተካክሎ መምጣት ይጠበቅበታል።
በዛሬው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች አዘውትረው በሚጠቀሙት የጨዋታ ዘይቤ የተጋጣሚያቸውን መረብ ለማግኘት እንደሚፋለሙ ይጠበቃል። በዚህ ሂደትም ባለሜዳዎቹ ፋሲሎች መሀል ሜዳ ላይ የበላይነትን ለማግኘት የሚሞክረውን የተጋጣሚያቸውን የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ በመስበር እና የመስመር አጥቂዎቻቸውን በመጠቀም በፍጥነት ከወልዋሎ የተከላካይ መስመር ጀርባ ለመገኘት ጥረት እንደሚያደርጉ ይታሰባል። በወልዋሎዎች በኩልም ከኳስ ቁጥጥሩ መነሻነት ከድር ሳሊህ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆን ማዕከል ያደረገ የመስመር ጥቃት የግብ ዕድሎችን መፍጠሪያ አማራጭ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህም በጨዋታው መሀል ሜዳ ላይ ከሚኖረው ፉክክር ባለፈ የቡድኖቹ የመስመር አጥቂዎች ከተቃራኒ ቡድን መስመር ተከላካዮች ጋር የሚያደርጉትን ትንቅንቅ ተጠባቂ ያደርገዋል።

የፋሲል ከተማው ራምኬል ሎክ እና የወልዋሎ ዓ.ዩው ብርሀኑ አሻሞ በቅጣት ከዚህ ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ዐይናለም ኃይለ ከፋሲል እንዲሁም ሳምሶን ተካ ከወልዋሎ ጉዳት የገጠማቸው ሌሎች ተጨዋቾች ሆነዋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ዓዲግራት ላይ በተደረገ ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

– ወልዋሎ ካለፉት 10 ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማስመዝገብ የቻለው በአንድ ጨዋታ ላይ ብቻ ነው፡፡

– ሁለቱ ክለቦች ዘንድሮ በአዲስ አበባ ስታድየም ባደረጓቸው ጨዋታዎች ወልዋሎ አንድ አሸንፎ ፣ 1 አቻ ተለያይቶ ፣ አንድ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ ፋሲል ከተማ ደግሞ አንድ አሸንፎ ፣ 2 አቻ ተለያይቶ ፣ አንድ ተሸንፏል፡፡

– ዘንድሮ በሰሜናዊ የሀገሪቷ ክፍል በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ፋሲል እና ወልዲያ ከመቐለ እና ወልዋሎ እርስ በእርስ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስተድየም እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ ጨዋታም በአዲስ አበባ ስታድየም የሚካሄድ 4ኛው ጨዋታ ነው፡፡

ዳኛ

ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ይመራል፡፡ ዘንድሮ 6 ጨዋታዎችን የዳኘው ብሩክ 26 የማስጠንቀቂያ እና 1 የቀይ ካርድ የመዘዘ ሲሆን ምንም ቢጫ ካርድ ካልታየባቸው ሁለት ጨዋታዎች መካከል በአንደኛው ላይ ዳኝቷል፡፡


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


መከላከያ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ሁለቱ የመዲናዋ ክለቦች ዘንድሮ አያያዛቸው ያማረ አልሆነም። መከላከያ በ15 ነጥቦች ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ ተገኝቶ የመጀመሪያውን ዙር አገባዷል። ይህም ሊሆን የቻለው በመቐለ ከተማ ላይ ያገኘውን ድል ተከትሎ ነው እንጂ ደረጃው ከዚህም የባሰ ይሆን ነበር። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ሽንፈት አለማስተናገዱ ከተጋጣሚው የተሻለ ያደርገዋል። በዚህ ወቅት የሰበሰባቸው አምስት ነጥቦችም በሰንጠረዡ ግርጌ ከመቀመጥ አትርፎታል። የዛሬው ጨዋታም በአደጋ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ሁለት ቡድኖችን እርስ በእርስ የሚያገናኝ በመሆኑ ብርቱ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል።

መከላከያ በውድድሩ አጋማሽ የአሰልጣኝ ለውጥ አድርጓል። የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ወደ ቡድኑ መምጣትም ብዙ ነገሮችን እንደሚቀይር ይታሰባል። ከአሰልጣኝ ቅጥሩ ባለፈ ቡድኑ መስፍን ኪዳኔን ወደ ወልዲያ ሸኝቶ ዳዊት እስጢፋኖስን ዳግመኛ ማምጣቱ የሚታወስ ነው። የአሰልጣኝ ቅጥሩም ሆነ ዝውውሩ መከላከያ ሊገነባው ሲሞክር በሚታየው ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሚሰጥ አይነት ቡድን ላይ ተጨማሪ ማሻሻያዎችን አድርጎ በዛው ለመቀጠል ማሰቡን ያስረዳል። ቡድኑ እጅግ ደካማ የነበረበትን የጎል ማስቆጠር ችግርን ለመቅረፍም አጥቂዎችን ፍለጋ ወደ ገበያ መውጣቱ የማይቀር ቢመስልም የአማካይ ክፍል ችጉሩን ማስተካከል ከቻለ እና የቦታው ተጨዋቾች በግብ ፊት ያላቸውን በራስ መተማመን ካስተካከለ ከነበረው የተረጋጋ የተጫዋቾች ስብስብ አንፃር ወደ ውጤታማነት ለመመለስ ረጅም ጊዜ ላይወስድበት ይችላል።

አሰልጣኝ አሸነፊ በቀለ ሞገስ ታደሰን ወደ ወልዲያ ሸኝተው ከቀድሞ ክለባቸው ታፈሰ ተስፋዬን በማምጣት ሁለተኛውን አጋማሽ የውድድር ጊዜ ጀምረዋል። አሰልጣኙ በነባር ተጨዋቾቻቸው ከኃላ የነበረውን ትልቁን የቡድኑን ደካማ ጎን ሲያሻሻሉ ምንም ሚና ያልነበረው ሞገስን ማሰናበታቸው እምብዛም የሚያስገርም አይደለም። ሆኖም ፊት ላይ በርካታ የተጨዋች አማራጮችን ይዘው ታፈሰን ወደ ክለቡ ማምጣታቸው አነጋጋሪ ሆኗል። ቡድኑ ከአማካይ መስመር እየተነሳ ግብ የሚያስቆጥረው ካሉሻ አልሀሰንን እንዲሁም ኃይሌ እሸቱ እና ዲዲዬ ለብሪን የመሳሰሉ አጥቂዎችን መያዙ ሲታሰብ በአዳማ ከተማ ከጉዳት መልስ በወጣቶቹ አጥቂዎች ቦታው የተያዘበት ታፈሰ ተስፋዬ በቀላሉ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ይገባል ለማለት ያስቸግራል። ከፊት መስመሩ ይልቅ ዕድሳት የሚያስፈገግው የአማካይ ክፍሉ ግን በነባሮቹ ተጨዋቾች ላይ እምነቱን ጥሎ የሚቀጥል ይመስላል።

ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የቡድን አወቃቀር እና ከመከላከያ የቀደመ ጊዜ አጨዋወት አንፃር ጦሩ በዛሬው ጨዋታ የመሀል ክፍል የበላይነትን ለመቆጣጥር እንደሚያቅድ ማሰብ ይቻላል። በዚህም ከበሀይሉ ግርማ እና ቴዎድሮስ ታፈሰ ጥምረት ፊት የሚኖሩት ሶስት አማካዮች ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የተሻሻለ የተከላካይ መስመር ፊት ከሚኖራቸውን የቅብብል ስኬት የሚነሱ ኳሶች እንዲሁም ፊት ላይ ምንይሉ ወንድሙ በሚያደርገው የጎንዮሽ እንቅስቃሴ ከቀይ ለባሾቹ የመሀል ተከላካዮች ጋር የሚገናኝባቸው ቦታዎች ወሳኝ ይሆናሉ። በኢትዮ ኤሌክትሪክ ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ ውስጥ ደግሞ የመስመር አጥቂዎቹ በመልሶ ማጥቃት ወደ ውስጥ ይዘው ለመግባት የሚሞክሯቸው ኳሶች ጥራት ለቡድኑ የመጨረሻ ዕድሎች ዋነኛ መነሻ እንደሚሆኑ ይገመታል። ዲዲዬ ለብሪ እና ኃይሌ እሸቱም በመሰል እንቅስቃሴዎች ከጦሩ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ ተጠባቂነቱ የላቀ ነው።

በመከላከያ በኩል ረጅም ጉዳት ላይ ያሉት አዲሱ ተስፋዬ እና ቴዎድሮስ በቀለ አሁንም ወደ ሜዳ የማይመለሱ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወሳኙን አማካይ ካሉሻ አልሀሰንን የማይጠቀም ይሆናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– መከላከያ በ1997 ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገ ወዲህ በሊጉ 25 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 11 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን 10 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል፡፡ ለወትሮው ኤሌክትሪክን ለማሸነፍ የሚቸገረው መከላከያ ደግሞ 4 ድል አስመዝግቧል፡፡ ኤሌክትሪክ 37 ጎሎች ሲያስቆጥር መከላከያ በአንፃሩ 26 ጎሎች አስቆጥሯል፡፡

ዳኛ

ጨዋታውን ፌዴራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሀል ዳኝነት ይመራዋል፡፡ በአመቱ 4 ጨዋታዎችን ብቻ የዳኘው ኃይለየሱስ 20 ቢጫ ካርዶች እና 2 ቀይ ካርድ መዟል፡፡


የክፍል 2 ፅሁፍን በዚህ ማያየዣ ተጠቅመው ያገኛሉ | LINK


 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *