ሀዋሳ ፣ ይርጋለም እና ድሬደዋ ላይ የሚደረጉ ሶስት የ16ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን በክፍል ሁለት ዳሰሳችን እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር
የአመቱን አጋማሽ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ያጠናቀቀው ሀዋሳ ከተማ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋርን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚያስተናግዱ ከሚጠበቁ የሳምንቱ ጨዋታዎች አንዱ ነው። ሀዋሳ ከተማ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቋሙን በማስተካከል ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን መርታቱን ተከትሎ ባገኛቸው ነጥቦች የሰንጠረዡን አጋማሽ ላይ ተቀመጠ እንጂ ከዛ አስቀድሞ በስድስት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ብቻ እንደማሳካቱ ቢሆን ኖሮ ደረጃው ከዚህም በላይ ዝቅ ባለ ነበር። በአንፃሩ የጅማው ክለብ ከአስረኛው ሳምንት ጅምሮ ከሽንፈት በመራቁ እና ሶስት ጨዋታዎችን ማሸነፉን ተከትሎ ራሱን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ እንዲያገኘው አድርጓታል። በመጀመሪያ አመት ተሳትፎው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ አመቱን ማጋመሱም ለክለቡ ትልቅ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል። የዛሬው ጨዋታ ግን አባ ጅፋር ይህን ውጤቱን ለማስቀጠል ሀዋሳ ከተማም ቀጣይነት ያለው ጥሩ አቋምን ለማሳየት የሚገናኙበት ይሆናል።
በዝውውር መስኮቱ ሀዋሳ ከተማ ፍርድአውቅ ሲሳይ እና ሳዲቅ ሴቾን አሰናብቶ አብዱልከሪም ሀሰን እና አላዛር ፋሲካን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። በተደጋጋሚ ጉዳቶች ሲታመስ የቆየው የቡድኑ የፊት መስመር ክፍል ሁለቱን አጥቂዎቹን መሸኘቱ አሳማኝ ቢመስልም የአላዛር ወደ ቡድኑ መምጣት ብቻውን የፊት መስመሩን ሙሉ ለሙሉ ያስተካክለዋል ለማለት ያስቸግራል። በሌላ በኩል ደግሞ ቡድኑ እንደ እስራኤል እሸቱ ባሉ ወጣት አጥቂዎች ላይ ይበልጥ እምነቱን እንዲጥል የሚያደርገው ውሳኔ ሆኖም አልፏል። አማካይ ክፍል ላይ የአብዱልከሪም ሀዋሳን መቀላቀል ግን ቡድኑ ከሚመራበት አጨዋወት አንፃር ሲታይ እንዲኖረው በሚያስፈልገው የፈጠራ ክህሎት ላይ ተጨማሪ ኃይል እንደሚሆነው ይጠበቃል።
የተረጋጋ የመጀመሪያ አሰላለፍን ይዞ በሊጉ የዘለቀው ጅማ አባ ጅፋር ሁለት ዝውውሮችን ፈፅሟል። ግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ወደ ሜዳ የተመለሰው ነጂብ ሳኒን ማግኘቱ በቦታው በርካታ አማራጮች እንደሚፈጥርለት ይታመናል። ነጂብ በፍጥነት ወደ መልካም አቋም ከመጣ እዚህ ቦታ ላይ ሲሰለፍ የቆየው የቡድኑ አምበል ኤልያስ አታሮ ወደ ዋናው የመሀል ተከላካይነት ሚናው የመመለስ ዕድልን ያገኛል። ሌላው ፈራሚ ደግሞ ጋናዊው አማካይ አሮን አሞሀ ነው። የአሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻው የመሀል ክፍል ጥምረት አባ ጅፋርን እስካሁን ቢያዘልቀውም በተለይ የአሚኑ ተደጋጋሚ ተቀይሮ መውጣት ቡድኑ ቦታው ላይ ተጨማሪ ተጨዋች እንደሚያስፈልገው የሚያሳይ ነበር። ዝውውሩ ቡድኑ በጥቅሉ ከመጀመሪያው አሰላለፍ ጋር የሚመጣጠን ተቀያሪ እንዲኖረው የሚያችልም ነው።
በዚህ መልኩ ራሳቸው ያጠናከሩት ሁለቱ ቡድኖች በጨዋታው የአማካይ ክፍል ላይ የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው። የኳስ ቁጥጥር ላይ አመዝኖ የተገነባው የሀዋሳ ቡድን ጥሩ መናበብ ላይ ሲገኝ ምን ያህል ልዩነት ሊፈጥር እንደሚችል የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ አሳይቶናል። ጅማ አባ ጅፋርም መሰል አጨዋወትን በሚተገብርባቸው ጨዋታዎች ላይ በመከላከሉ ሚዛኑን የሚጠብቅ እና በማጥቃት ሂደትም ውስጥ የመጨረሻ ዕድሎችን መፍጠር የማይከብደው የመሀል ክፍልን ይዟል። ቡድኑ በዛሬውም ጨዋታ በዮናስ ገረመው እንቅስቃሴ ላይ ተመስርቶ እና በኦኪኪ የግብ አጨራረስ ታግዞ በፈጣን ቅብብሎች ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ የሚጫወተውን የሀዋሳ ከተማ የሳሳ የተከላካይ መስመር በተለይም የቀኙን ክፍል እንደሚፈትን ይጠበቃል። በሜዳቸው በሚደረጉ ጨዋታዎች በተሻለ የኳስ ቅብብል ስኬት ተጋጣሚያቸውን መፈተን የማይከብዳቸው ሀዋሳዎችም የታፈሰ ሰለሞን እና ፍሬው ሰለሞንን ቅንጅት በመጨረሻው የሜዳ ክፍል ከጅማ የአማካይ ተከላካዮች ለሚገጥማቸው ፈተና የእንቅስቃሴ መነሻ አድርገው እንደሚጠቀሙበት ይታሰባል። ቡድኑ ወደ ቀኝ መስመር ያደላ ማጥቃትን እንደሚተገበር ሲታሰብም ከአባ ጅፋር የግራ መስመር የመከላከል ክፍል ጋር የሚያደርገውን ፍልሚያ በወሳኝነቱ የሚነሳ ነው።
በሀዋሳ ከተማ በኩል አምስት የቢጫ ካርዶችን የተመለከተው አዲስ አለም ተስፋዬ በቅጣት እንዲሁም መሳይ ጳውሎስ ፣ ዮሀንስ ሴጌቦ እና ፀጋአብ ዮሴፍ በ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በመካተታቸው ለጨዋታው አይደርሱም። ከዚህ ውጪ አዲስ ፈራሚዎቹ አላዛር ፋሲካ እና አብዱልከሪም ሀሰንም የወረቀት ጉዳያቸው ባለማለቁ ወደ ሜዳ የማይገቡ ይሆናል፡፡ በተቃራኒው ጅማ አባ ጅፋር ያለ ጉዳት እና ቅጣት ወደ ሀዋሳ ማምራቱን ሰምተናል።
እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ዘንድሮ ሲሆን በመጀመርያው ሳምንት ጅማ ላይ ባደረጉት ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር በኦኪኪ አፎላቢ ጎሎች 2-0 አሸንፏል፡፡
– አምና በሜዳው 3 ጨዋታ የተሸነፈው ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ ምንም ሽንፈት ባያስመዘግብም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ድል በፊት 3 ተከታታይ ጨዋታዎችን አቻ ተለያይቷል፡፡ ተጋጣሚው ጅማ አባ ጅፋር በአንፃሩ ዘንድሮ ሁለት ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ ሲያሸንፍ ያለፉትን 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት አላጋጠመውም፡፡
ዳኛ
ይህን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ይመራዋል፡፡ ዘንድሮ በፕሪምየር ሊጉ 4 ጨዋታ የዳኘው አሸብር 17 የማስጠንቀቂያ ካርዶች አሳይቷል፡፡
Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ
ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ቡና
በመሀከላቸው የሁለት ነጥብ ልዩነት ብቻ ያለው ቡድኖቹ የመጀመሪያውን ዙር ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ በአንዱ 0-0 በሌላው ደግሞ 1-1 ነበር የተለያዩት። ከዚያ አስቀድሞም በሊጉ ላይ የነበራቸውን ደካማ አጀማመር ወደ ኃላ ላይ በመጠኑ ማስተካከላቸውም የሚያመሳስላቸው ሌላው ነጥብ ነው። አሁን ላይ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃርም ይህን ጨዋታ የሚያሸንፈው ቡድን ከ20 በላይ ነጥብ ካላቸው ቡድኖች ተርታ መሰለፍ የሚያስችለው መሆኑ ጨዋታውን ወደ መሪዎቹ በመጠኑ ለመጠጋት የሚያችል ፍልሚያ ያደርገዋል።
ሲዳማ ቡና ከአሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ ጋር የተያየው የመጀመርያው የውድድር ዘመን አጋማሽ እንደተጠናቀቀ ነበር፡፡ ቡድኑ ከአምናው ጋር ሲነጻፀር በጥሩ ሁኔታ ላይ የማይገኝ እንደመሆኑ የአሰልጣኝ ለውጡ ሌላ በሊጉ ልምድ ያለው እና በቶሎ ሲዳማ ቡናን ወደ ውጤታማነት ጎዳና የሚመልስ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም ያ ሳይሆን ቀርቶ የቀድሞው የቡድኑ አምበል እና የአለማየሁ ረዳት የነበረው ዘርዓይ ሙሉን በኃላፊነት ሾሟል፡፡ ሹመቱ ለቡድኑ ምን ይጨምራል የሚለው ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው ቢሆንም የሊጉ ሁኔታ ተገማች ባለመሆኑ አሰልጣኙ በፍጥነት ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ክለቡ ዮሴፍ ዮሃንስ እና ጫላ ተሺታን ከመልቀቁ ውጪ በዝውውር መስኮቱ ምንም የዝውውር እንቅስቃሴ ባለማድረጉ በአንደኛው አጋማሽ የነበረውን ስብስብ ይዞ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት አቋማቸው በእጅጉ ወርደው የታዩ የቡድኑ ተሰላፊዎች ብቃት መሻሻል ከመጀመርያው ዙር የተሸለ ውጤት እንዲያስመዘግብ የሚያደርገው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በዝውውር መስኮቱ ማናዬ ፋንቱ ፣ አብዱሰላም ኑር እና በረከት ይስሃቅን ሸኝቶ ባፕቲስቴ ፋዬ እና ቦባን ዚሩንቱሳን በማስፈረም የአጥቂ መስመሩን ለማደስ ጥረት አድርጓል፡፡ ቡድኑ የሚተማመንበት የፊት አጥቂ አለመያዙ በመጀመርያው አጋማሽ የተጠበቀውን ያህል ነጥብ እንዳያስመዘግብ እንደማድረጉ የሁለቱ የውጭ ዜጎች መምጣት የፊት መስመሩን ሊያሻሽለው ይችላል፡፡ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ቡድናቸውን የመረዳት ጊዜ እያገኙ መምጣታቸውም ለቡና ተጨማሪ ጥንካሬ በሁለተኛው አጋማሽ ሊፈጥርለት እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
በዛሬ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት ኢትዮጵያ ቡና በተለመደው መልኩ ተቀራርበው በሚጫወቱ አማካዮቹ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የሲዳማን የአማካይ እና ተከላካይ መስመር አስከፍቶ ለመግባት ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል። በዚህ ሂደት ውስጥ በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ በቦታው ለተጋጣሚያቸው ክፍተትን ሰጥተው ፈጣን መልሶ ማጥቃትን ሲተገብሩ የሚታዩት ሲዳማዎች በዛሬው ጨዋታ ግን ከዚህ በተለይ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በማጥቃት ሂደት ላይ ለመሳተፍ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ለተጋጣሚ ክፍተት የሚሰጡት የቡና የመስመር ተከላካዮችም ጎናቸው ከሚገኙ የመሀል ተከላካዮች ጋር የሚኖራቸውን ርቀት መመጠን ካልቻሉ በሲዳማ ቡና የመስመር አጥቂዎች በእጅጉ ሊፈተኑ የሚችሉበት ጨዋታ እንደሆነ ይጠበቃል። ሲዳማዎች አንድ የአማካይ መስመር ተጨዋቻቸውን በተጨማሪነት ወደ መስመር በማውጣት እና ቀሪዎቹን አጥቂዎች በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ በቁጥር ተበራክተው እንዲገቡ በማድረግ የሚፈጥሩት ጫና በዚህም ጨዋታ የሚደገም ከሆነ ሁኔውታ ኢትዮጵያ ቡና በተከላካይ መስመሩ ላይ የሚፈጠረውን ጫና የሚቋቋምበት እና አማካይ ክፍል ላይ የሚያገኘውን የቁጥር ብልጫ የሚጠቀምበትን መንገድ ተጠባቂ ያደርገዋል።
የሲዳማ ቡናው የፊት አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ በአምስት ቢጫ ካርድ ከዚህ ጨዋታ ውጪ ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሚካኤል ሀሲሳ ፣ ዮናታን ፍሰሀ እና ሙጃይድ መሀመድ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በመካተታቸው ለዛሬው ጨዋታ አይደርሱም። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አክሊሉ አያናው እና አለማየው ሙለታ አሁንም ከጉዳት ያልተመለሱ ተጫዋቾች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ከአዳዲሶቹ ፈራሚዎች መሀከል ዩጋንዳዊው አጥቂ ቦባን ዚሩንቱሳ የወረቀት ጉዳዮችን ባለመጨረሱ ወደ ሲዳማ ያልተጓዘ ሲሆን ሴኔጋላዊው ባቲስቴ ፋዬ ሴኔ ግን ለጨዋታው እንደሚደርስ ተሰምቷል።
እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– በመጀመርያዎቹ 5 ተከታታይ የሜዳዎቹ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ሲዳማ ቡና ካለፉት 4 የሜዳው ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 12 ነጥብ አስሩን በመሰብሰብ ወደ ቀድሞ ጥንካሬው እየተመለሰ ይገኛል፡፡ ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ ከአዲስ አበባ ውጪ ዘንድሮ ማግኘት ከሚገባው 15 ነጥብ ያሳካው አራቱን ብቻ ነው፡፡
– ሁለቱ ቡድኖች ሲዳማ ቡና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት 2002 ወዲህ 17 ጊዜያት ያህል ተገናኝተዋል፡፡ ሲዳማ ቡና 7 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላነቱን ሲወስድ ኢትዮጵያ ቡና 5 ጊዜ አሸንፏል፡፡ በ5 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ቡድኖቹ በግንኙነታቸው እኩል 21 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።
– በሲዳማ ሜዳ በተደረጉ 8 ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና 5 ኢትዮጵያ ቡና አንድ ጊዜ ሲያሸንፉ 2 በጨዋታዎችን ደግሞ አቻ ተለያተዋል፡፡ በሁለቱ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ከመረብ ካረፉ 42 ግቦች መካከል በሲዳማ ቡና ሜዳ የተቆጠሩት 16 ብቻ ናቸው፡፡
– በ2008 ይርጋለም ላይ 0-0 የተጠናቀቀው ጨዋታ በሁለቱ የእርስ በዕርስ ግንኙነት ታሪክ ብቸኛው ያለ ግብ የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው፡፡
ዳኛ
ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይመራዋል፡፡ ዘንድሮ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ የተቀበለው ቴዎድሮስ በመጀመርያው የውድድር ዘመን አጋማሽ 6 ጨዋታዎችን የመራ ሲሆን 25 ቢጫ እና 2 ቀይ ካርዶችን መዟል፡፡
Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ
ድሬደዋ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የድሬደዋው ጨዋታ በሰንጠረዡ የተለያየ ደረጃ ላይ ቢገኙም ጥሩ ያልሆነ የውድድር አመት እያሳለፉ የሚገኙ ክለቦች የሚገናኙበት ነው። እንደ አምናው ሁሉ አስከፊ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ድሬደዋ ከረጅም ጊዜ በኃላ በ15ኛው ሳምንት ወልዋሎ ዓ.ዩን ማሸነፍ ቢችልም በተስተካካይ ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተሸንፏል። የቅዱስ ጊዮርጊስም የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ምንም ድል ያልተመዘገባቸው ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ በሽንፈት የተጠናቀቁ ነበሩ። በመሆኑም ቡድኖቹ የውድድር ዘመናቸውን ለማስተካከል ሁለተኛውን ዙር የሚጀምሩበትን ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ወሳኝ ይሆንላቸዋል።
በመጀመሪያው ዙር አጋማሽ የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገው ድሬደዋ ከተማ አሁን ደግሞ በተጨዋቾች ዝውውሩ ሰንደይ ሙቱኩ እና ዘካሪያስ ፍቅሬን ለቆ በምትካቸው በረከት ይስሀቅን ፣ ዮሴፍ ድንገቶ እና ሚካኤል አኩፎን አምጥቷል። አሰልጣኝ ስምዖን አባይ እየገነቡት ባለው የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ባለው ቡድን ውስጥ አዳዲሶቹ ፈራሚዎች የሚኖራቸው ስኬታማነት በመጪዎቹ ጨዋታዎች የሚታይ ቢሆንም ቡድኑ የተጋጣሚን የኃላ መስመር አሁን ካለው በተሻለ የሚያስጨንቅ እና ክፍተቶችን የሚፈጥር የአማካይ ክፍል መገንባት እንደሚጠበቅበት ግን ከወዲሁ መናገር ይቻላል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የታየው የውድድር አጋማሹ ለውጥ የአማራ ማሌ ቡድኑን መቀላቀል ነው። የአሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ ስብስብ በተደጋጋሚ ሲቸገርበት የሚታየውን የፊት አጥቂ ቦታ ለማጠናከር ማሊያዊውን አጥቂ ወደ ቡድኑ ማምጣቱ አንደኛው የመፍትሄው አካል ሆኖ ተወስዷል። ሆኖም ቡድኑ እንደተጋጣሚው ድሬደዋ ሁሉ በቁጥራቸው የበረከቱ እና ጥራታቸውን የጠበቁ የመጨረሻ ዕድሎችን የሚፈጥር የአማካይ ክፍል እና የጠንካራ የመስመር አጥቂዎቹ እንቅስቃሴ መመለስ ይጠበቅበታል።
ሁለቱም ቡድንኖች ለማጥቃት ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚጀምሩት የሚጠበቀው ጨዋታ ላይ በመሀል ሜዳ የሚኖረው ፍልሚያ ተጠባቂ ይሆናል። ኢማኑኤል ላርያ የማይጠቀመው ድሬደዋ ከመከላከል ይልቅ የማጥቃት ኃላፊነታቸው ጎልቶ ከሚታየው አማካዮቹ ዘላለም ኢሳይያስ ፣ ዮሴፍ ደሙዬ እና ሱራፌል ዳንኤል የተሻለ የመከላከል ተሳትፎን ይጠብቃል። ቡድኑ የላርያ አለመኖር በሚፈጥረው ክፍተትም የምንተኖንት አዳነ እና አብዱልከሪም ኒክማን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚያስችል መልኩ ሳውሬል ኦርሊሽን ከአንዴ ሌላ አማካይ ጋር እንደምያጣምር ይጠበቃል። የመስመር ተከላካዮቻቸውን እምብዛም በማጥቃት ላይ ሲያሳትፉ የማይታዩት ቅዱስ ጊዬርጊሶች ደግሞ መሀል ላይ በቁጥር በርክቶ የሚጠብቃቸውን የድሬደዋ የአማካይ ክፍል ለማለፍ እና ኳሶችን ለአማራ ማሌ ለማድረስ በመስመር አጥቂዎቻቸው በተጋጣሚ የግብ ክልል ዙሪያ ክፍተትን የመፍጠር አላማ ያለው እንቅስቃሴ ላይ ተመርኩዘው እንደሚያጠቁ ይጠበቃል።
በድሬዳዋ ለተማ ቡድን ውስጥ ቁልፍ ሚና ያለው ኢማኑኤል ላርያ በጉዳት የማይሰለፍ ሲሆን አዲስ ፈራሚዎቹ በረከት ይስሀቅ እና ዮሴፍ ድንገቶ ለጨዋታው እንደሚደርሱ ተሰምቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሰላሀዲን ሰይድ እና ሮበርት ኡዱንካራ ጉዳት ላይ ሲሆኑ ናትናኤል ዘለቀም ከረጅም ጊዜ ጉዳቱ አላገገመም።
እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ 13 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 9 በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ድሬዳዋ ከተማ 3 አሸንፏል፡፡ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ፈረሰኞቹ 25 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ብርቱካናማዎቹ 12 ጎሎችን አግብተዋል፡፡
– ድሬደዋ ላይ 6 ጨዋታዎች ተደርገው እኩል 3 ጊዜ ድልን ተቋድሰዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ሜዳ ድል ካስመዘገበባቸው ሶስት ጨዋታዎች መካከል በ2002 የውድድር አመት 4-0 ያሸነፈበት እንዲሁም አምና 5-3 የረታበት ድሎች በትልቅነታቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
– በዚህ አመት ሁለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ ስታድየም ባደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ ይህም በሁለቱ የእርስ በእርስ ግንኙነት ታሪክ ብቸኛው በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው፡፡
ዳኛ
ይህን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይመራዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ የዳኘው በላይ ዘንድሮ በፕሪምየር ሊጉ 7 ጨዋታዎችን የመራ ሲሆን 27 የማስጠንቀቂያ እና 1 ቀይ ካርዶችን መዟል፡፡
የክፍል 1 ፅሁፍን በዚህ ማያየዣ ተጠቅመው ያገኛሉ | LINK