የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ ካራ ብራዛቪል አነጋጋሪ ድርጊት…

በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኮንጎ ሪፐብሊኩ ካራ ብራዛቪል ጋር ወደ ምድብ ለመግባት ይጫወታል፡፡ ካራ አሁን ላለበት የማጣሪያ ዙር ለመድረስ የጋናውን አሻንቲ ኮቶኮ እና የቱኒዚያውን ቤንጎርዳን ረቷል፡፡

ካራ ኩማሲ ላይ ከአሻንቲ ኮቶኮ ጋር ያደረገው ጨዋታ ግን አስገራሚ እና ፈገግ የሚሰኙ ኩነቶች የተስተናገዱበት ነበር፡፡ ጋናዊው የእግርኳስ ጋዜጠኛ ሳዲቅ አደምስ (ኦባማ) በአፍሪካ ሳከር የቴሌቭዢን ፕሮግራም ላይ ቀርቦ በጨዋታው የተከሰተውን እንዲህ አብራርቷል፡፡ “ካራዎች ከጨዋታው 24 ሰዓታት አስቀድመው ወደ ባባ ያራ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምድ ለመስራት መጡ። ሆኖም በኩማሲው ስታዲየም ልምምዳቸው ከማከናወን ይልቅ በሁለቱም የጎል ብረቶች ላይ ሄደው ሽንታቸውን ሸኑ፡፡ ይህ ድርጊት ለስታዲየም ጠባቂዎች ሪፖርት ስለተደረገ የካራ ተጫዋቾች እና ሃላፊዎች ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ኮቶኮ ያቀረበላቸውን ሆቴል በመተው ራሳቸው ወደመረጡት ሆቴል አምርተዋል፡፡”

ይህ ድርጊት የጋና የስፖርት ሚዲያዎችን ያስገረመ ነበር፡፡ ካራዎች ልምምድ ለመስራት ትጥቅ ይዘው አለመምጣታቸውን እና በግብ ክልሎቹ አከባቢ የፈፀሙት ተግባርም የምሽቱ መነጋገሪያ ነበር፡፡ ሳዲቅ በጨዋታው ወቅት ስለነበረው ጉዳይ ማስረዳቱን ይቀጥላል፡፡ “በጨዋታው ቀን የተፈጠረው ድራማ ነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ አሻንቲ ኮቶኮ ፍፁም ቅጣት ምት አገኘ፡፡ ፍፁም ቅጣት ምት አልነበረም ሆኖም የካራ ተጫዋቾች አልተቃወሙም፡፡ ኮቶኮ ጥሩ መቺ ነበረው ሳዲቅ የሚባል ሆኖም ወደ ውጪ መትቶ ሳተ፡፡ በአስገራሚ ሁኔታ ኮቶኮ ሁለተኛ ፍፁም ቅጣት ምት በሁለተኛው አጋማሽ አገኘ፡፡ ከዚህ ፍፁም ቅጣት ምት በፊትም ቢሆን የግቡን አግዳሚ ብዙ ግዜ ከመለተማቸው ባለፈ ያለቀላቸውን እድሎች አምክነዋል፡፡ ሳዲቅ ይህንን አልመታም ነበር ፤ የቡድኑ አምበል ኳስን ተረክቦ ቢመታም የካራው በረኛ መለሰበት፡፡ የኮቶኮ ደጋፊዎች ምን እየተፈጠረ እንዳለ መረዳት አልተቻላቸውም፡፡ ከሁለተኛው ፍፁም ቅጣት ምት አምስት ደቂቃ በኃላ ኮቶኮ ሶስተኛ የፍፁም ቅጣት ምት አገኘ፡፡ የካራ ተጫዋቾች አሁንም አልተቃወሙም፡፡ አሁንም በረኛው መለሰው፡፡ ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ካራ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ግብ ጠባቂያቸው መቶ ሳተ፡፡”

ይህ በጨዋታው ላይ መፈጠሩ የሚታመን አይመስልም፡፡ ኮቶኮ አራተኛ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቶ በማስቆጠር ጨዋታውን 1-0 አሸንፏል፡፡ አስቡት አምስት ፍፁም ቅጣት ምት የተሰጠበት ጨዋታ 1-0 ብቻ ሲጠናቀቅ፡፡ በአፍሪካ እግርኳስ የበአድ አምልኮን የሚከተሉ ቡድኖች እንዳሉ ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ የካራ ተጫዋቾች ከጨዋታው አስቀድሞ ያደረጉት ድርጊት እና በጨዋታው ወቅት አራት የፍፁም ቅጣት ምቶች መሳታቸው የሶከር አፍሪካ አዘጋጆችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡ ካራ ብራዛቪሎች በያዝነው ወር መጨረሻ አዲስ አበባ ሲመጡ ይህንኑ ድርጊት ይደግሙ ይሆን” ወይስ ሌላ ተለየ ነገር ይዘው ይመጡ ይሆን?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *