ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ደደቢት

ትላንት ሰባት ጨዋታዎች የተደረጉበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዛሬ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ደደቢትን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠናቀቃል። ይህንን ጨዋታ በዛሬው ዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

ትላንት በሊጉ በተደረጉ ጨዋታዎች የተመዘገቡት ውጤቶች ደደቢትን ተከታዮቹ በቅርብ ርቀት እንዲከተሉት ወላይታ ድቻንም በአንድ ደረጃ እንዲንሸራተት አድረገዋል። በመሆኑም የዛሬው ጨዋታ ለሁለቱ ቡድኖች የሚኖረው ዋጋ ከፍ ማለቱን ከዚህ መገንዘብ ይቻላል። ደደቢት አሁንም የሊጉ መሪ ይሁን እንጂ በውድድሩ አጋማሽ የነበረው ፍጥነት ቀንሷል። ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ መሆኑ ለዚህ ማስረጃ ነው። ከኮንፌዴሬሽኑ ታላቅ ድል በኃላ የሊጉን መሪ የሚያስተናግደው ወላይታ ድቻ በአንፃሩ በሊጉ የተሻለ አቋም ላይ ይገኛል። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሶስቱን ማሸነፍ የቻለው የሶዶው ክለብ በሜዳው ካለው ጥሩ ሪከርድ እና በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ያገኘውን ድል ተከትሎ በቡድኑ ውስጥ ከሚኖረው ጠንካራ የማሸነፍ ስነልቦና አንፃር ለደደቢት ከባድ ፈተና ሆኖ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።               

ወላይታ ድቻ በተከላካይ መስመር ላይ አስፈርሞት የነበረው ቻዳዊ የመሀል ተከላካይ ማሳማ አሴልሞን እና ሌላውን ተከላካይ አረጋሀኝ ለማን ያሰናበተ ሲሆን በዚሁ ቦታ ላይ ወንደሰን ቦጋለን ከአዳማ ከተማ ሲያስመጣ ዮናታን ከበደ እና ታድዮስ ወልዴን ከአርባምንጭ እንዲሁም ፀጋዬ ባልቻን ከሲዳማ ቡና ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። በውድድሩ አጋማሽ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀን በሀላፊነት ከሾመ በኃላ እየተሻሻለ የመጣው ቡድን በአመዛኙ ተመሳሳይ ተጨዋቾችን የተጠቀመ ቢሆንም ከለቀቁበት ተጨዋች በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጨዋቾቹን ቦታ ለመሸፈን ዝውውሮቹን የፈፀመ ይመስላል። አመቱ ሲጀምር አንድ ተጨዋች ብቻ አስፈርሞ ውድድሩን የጀመረው ተጋጣሚው ደደቢት ግን በአሁኑ የዝውውር መስኮት ምንም ተጨማሪ ተጨዋች አላስፈረመም። ክለቡ ከነበረው ስብስብ መሀል ሰብረው በመውጣት በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ሲሰለፉ በምናያቸው ወጣት ተጨዋቾች ላይ እመነቱ በመጣል ቀሪውን የውድድር ዘመን ለመጨረስም አስቧል።

Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ

የዛሬው ጨዋታ በዋነኝነት ሁለቱም ቡድኖች ሙሉ ሀሳባቸውን በማጥቃት ላይ አድርገው ከመጀመሪያው ጀምሮ ግቦችን ለማስቆጠር የሚተጉበት እንደሚሆን ይጠበቃል። ወላይታ ድቻ በ4-1-4-1 አሰላለፍ ከኃይማኖት ወርቁ ፊት ያሉትን አራቱን አማካዮች ይበልጥ ወደ ብቸኛው አጥቂ ጃኮ አራፋት ቀርበው እንዲጫወቱ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ከነዚህ ተጨዋቾች መሀል ላይ የሚገኙት በዛብህ መለዮ እና አብዱልሰመድ አሊ ደግሞ የደደቢትን ቅብብሎች ከመጀመሪያው የማበላሸት ሀላፊነት ሊኖራቸው ይችላል። ቀሪዎቹ የመስመር አማካዮች ደግሞ ከበስተኃላቸው ከሚኖሩት የመስመር ተከላካዮች ጋር በመሆን ከደደቢት የቦታው የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያ ተጠባቂ ይሆናል። አማካይ ክፍሉ ላይ አቤል እንዳለን የማይዘው ደደቢት ቦታው በፋሲካ አስፋው እንዲሸፈን ከማድረግ ባለፈ የመስመር አጥቂዎቹ ሽመክት ጉግሳ እና አቤል ያለው ወደ ኃላ ተስበው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ መሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫን በማግኘት በተለመደው ፈጣን ጥቃቱ ወደ ድቻ የግብ ክልል ለመግባት ጥረት የሚያደርግ ይሆናል። የሜዳው ጥራት አናሳነት በቅብብሎቹ ላይ ከሚፈጥረው ፈተና ባለፈ ደደቢት ጥሩ የአማካይ ክፍል ሽፋን የሚሰጠውን የድቻን የኃላ መስመር በጌታነህ ከበደ ብቸኛ የፊት አጥቂነት አልፎ ለመግባት የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው።

የወላይታ ድቻዎቹ እርቂሁን ተስፋዬ እና ፀጋዬ ብርሀኑ አሁንም ከረጅም ጊዜ ጉዳታቸው ባለማገገማቸው ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል።  እዮብ አለማየሁ ከወላይታ ድቻ አቤል እንዳለ ከደደቢት ለ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ተጨዋቾች ሲሆኑ ጌታነህ ከበደ ደግሞ በጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ ከተመለከተው የቀይ ካርድ በኃላ ሶስት ጨዋታዎችን ተቀቶ አንዱን በይቅርታ በመታለፉ ለዛሬው ጨዋታ እንደሚደርስ ተሰመቷል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– እስካሁን በሊጉ 9 ጊዜ ተገናኝተው ደደቢት 5 በማሸነፍ ቀዳሚነቱን ሲይዝ ወላይታ ድቻ 3ቱን አሸንፏል፡፡ አንድ ጊዜ (ዘንድሮ) ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በወላይታ ድቻ ሜዳ የተደረጉትን ጨዋታዎች ስንመለከት ደግሞ በ4 ጨዋታዎች ድቻ ሶስቱን ሲያሸንፍ ደደቢት አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል።

– በሁለቱ የእርስ በእርስ ግንኙነት 28 ጎሎች ተቆጥረዋል፡፡ ከነዚህ መካከል 13 የተገኙት በወላይታ ድቻ ሜዳ (ሶዶ እና ቦዲቲ) ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲሆን በአጠቃላይ ደደቢት 17 ወላይታ ድቻ  ደግሞ 11 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። 

– ወላይታ ድቻ ሶዶ ላይ ባደረጋቸው የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች በሁሉም በማሸነፍ ሰባት ግቦችን ሲያስቆጠር መረቡ የተደፈረው አንድ ጊዜ ብቻ ነበር።

ዳኛ

ይህንን ጨዋታ በዋና ዳኝነት የሚመራው ፌዴራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ነው፡፡ ዘንድሮ 5 ጨዋታ የዳኘው እያሱ ሁለቱ ቡድኖች በአንደኛው ዙር አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ያደረጉትንም ጨዋታ መርቶ ምንም ካርድ ሳይመዝ ጨዋታውን አጠናቋል፡፡ በአጠቃላይ እያሱ ዘንድሮ 13 ቢጫ ካርዶችን አሰይቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *