” ኳሱን ልወረውር ስል ከጓንቴ ጋር ተጣበቀ… ” ዘውዱ መስፍን

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ጎንደር ላይ መካሄድ ሲገባው ከፀጥታ ስጋት ጋር ተያይዞ ትላንት በአዲስ አበባ ስታድየም በ08:00 ላይ የተደረገው የፋሲል ከተማ እና ወልዋሎ ጨዋታ ዘውዱ መስፍን በራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል በአጼዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው ጅማሮ 1ኛው ደቂቃ ላይ ተከስቶ ያለፈው ክስተት ጨዋታውን በተከታተሉ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ መነጋገርያ የነበረ ነው። የፋሲል ከተማ አጥቂዎች የፈጠሩትን የግብ አጋጣሚ በአግባቡ የተቆጣጠረው የወልዋሎው ግብ ጠባቂ ዘውዱ መስፍን ኳሱን በእጁ ወርውሮ በግራ መስመር ለሚገኘው አለምነህ ግርማ በፍጥነት አደርሳለው ሲል ኳሱ አቅጣጫውን ስቶ በራሱ መረብ ላይ በማረፍ ጎል ሆኖ ተመዝግቧል። ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ የተቆጠረውን የጎል አጋጣሚ መነሻ በማድረግ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ቆይታ ያደረገው ዘውዱ መስፍን ስለተፈጠረው ሁኔታ እንዲህ ይናገራል ።

” በተጨዋችነት ዘመኔ እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም ፤ ይህ የመጀመርያዬ ነው። ምን እንደተፈጠረ ራሱ አላውቅም። ለተጫዋቹ ወርውሬ ልሰጠው ስል ኳሱ ከእጅ ጓንቴ ጋር ተጣበቀ። ከዛ ስወረውር ከእጄ ተላቆ ጎል ሆነ ። በጣም ነው የደነገጥኩት እና የተረበሽኩት። ከእኔም የማይጠበቅ ስህተት ነው ። በእኔ ስህተት ምክንያት ወልዋሎ ነጥብ በመጣሉ በጣም አዝኛለው። ቡድኑን እና ደጋፊዎቹን በጣም ይቅርታ እጠይቃለው። እንዲህ አይነት ክስተቶች በቀጣይ ጠንክሬ እንድሰራ እና ጥንቃቄ እንዳደርግ ነው የሚያደርገኝ ፤ በጨዋታዎች ሁሉ ትኩረት እንዳደርግም አስተምሮኛል። አንዳንዴ የኳስ ሂደት እንደዚህ ነው። ሳትጠብቀው ያልታሰበ ስህተት ይፈጠርና ተሸንፈህ ትወጣለህ ። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *