ሪፖርት | መከላከያ የአመቱን ከፍተኛ ድል አስመዝግቧል

ሁለቱን የመዲናዋን ክለቦች ባገናኘው የዛሬ የአዲስ አበባ ስታድየም ሁለተኛ ጨዋታ መከላከያ በውድድር አመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በጨዋታ ከአንድ ጎል በላይ በማስቆጠር ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3-1 ማሸነፍ ችሏል።

ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያውን ዙር ከወልዲያ ጋር ባደረጓቸው ተስተካካይ ጨዋታዎች ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በርካታ ለውጥ አድርገዋል። በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ስር ሁለተኛውን ዙር የጀመረው መከላከያ አማካይ ክፍል ላይ በብዛት የሚጠቀመውን የበኃይሉ ግርማ እና ቴዎድሮስ ታፈሰን ጥምረት በአማኑኤል ተሾመ እና ዳዊት እስጢፋኖስ የተካ ሲሆን ፊት መስመር ላይም ወልዲያ ላይ በጉዳት ያልነበረው ምንይሉ ወንድሙን እና የተሻ ግዛውን በማራኪ ወርቁ እና አቅሌሲያስ ግርማ ቀይሯል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል የታዩት ለውጦች በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ከጉዳት የተመለሰው ዐወት ገ/ሚካኤል ጫላ ድሪባን ተክቶ በመግባቱ የሚጀምሩ ሲሆን አማካይ ክፍል ላይ አዲስ ነጋሽ ፣ አልሀሰን ካሉሻ እና ምንያህል ይመር የነበራቸው ቦታ በኄኖክ ካሳሁን ፣ በኃይሉ ተሻገር እና ጥላሁን ወልዴ ሰጥተዋል። ፊት ላይም በኃይሌ እሸቱ ምትክ ከዲዲዬ ለብሪ ጋር የመጣመር ዕድል ያገኘው ዳግም ወደ ክለቡ የተመለሰው አንጋፋው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ ነበር።

በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች መከላከያዎች በሳሙኤል ሳሊሶ እና የተሻ ግዛው የኢትዮ ኤሌክትሪክን የተከላካይ መስመር ሰብረው በመግባት ያደረጓቸው ሙከራዎች እና አጋጣሚዎቹ የተፈጠሩበት መንገድ ቡድኑ በጨዋታው ላሳየው የተለየ ተነሳሽነት ማሳያ የሚሆኑ ነበሩ። ቡድኑ የአሰልጣኝ ለውጡ የፈጠረው በሚመስል መልኩ በዳዊት እስጢፋኖስ እየተመራ በከፍተኛ ሁኔታ ኳስን በመቆጣጠር እና ጥሩ የሚባሉ ዕድሎችን በመፍጠር ከተጋጣሚው ተሽሎ ታይቷል። ሆኖም ጦሩ ሊተገብረው ባሰበው የ 4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፍ አተጋገበር ላይ ያለቅጥ ወደመሀል የሚጠጋጋው የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቹ ቦታ አያያዝ በተደጋጋሚ ኳሶች እንዲቆራረጥበት ምክንያት ሆኖ ነበር። ከመሀል ሜዳው ይልቅም ቡድኑ የተሻለ አስፈሪ ይሆን የነበረው እንቅስቃሴዎቹ ወደ መስመር በሚወጡበት አጋጣሚ ነበር።

የመከላከያ የበላይነት 28ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከሳጥን ውስጥ ካደረገው እና ኢላማውን ካልጠበቀው ሙከራ በኃላ ቀንሶ ታይቷል። ኤሌክትሪኮች የተወሰደባቸውን ብልጫ በመቀነስ ወደ ዲዲዬ ለብሪ በሚልኳቸው ኳሶች መነሻነት ወደ መከላከያ የግብ ክልል መድረስ የጀመሩትም ከዚህ በኃላ ነበር። 25ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲዬ ለብሪ ከተከላካዮች ቀምቶ ለታፈሰ ያሳለፈውን ኳስ በድጋሜ ተከላካዮች አወጡት እንጂ እጅግ አደገኛ ነበር። በሀኃይሉ ተሻገር ከርቀት የሞከረው እና ዐወት ገ/ሚካኤል ደግሞ ከማዕዘን ምት የተመለሰን ኳስ ወደ ጎል በቀጥታ ልኮ ኳስ አቤል ማሞን ካለፈ በኃላ ምንተስኖት ከበደ ከመስመር ላይ ያወጣበት አጋጣሚ ኤሌክትሪኮች በእጅጉ ለጎል የቀረቡበት ነበር። ሆኖም ቡድኑ በማጥቃት መንፈስ ውስጥ ሆኖ የተከላካይ ክፍሉን ወደ መሀል ባስጠጋበት ቅፅበት ከዳዊት እስጢፋኖስ የተነሳ ኳስ በሳሙኤል ታዬ አማካይነት ለምንይሉ ወንድሙ ደርሶት ምንይሉም አፈትልኮ በመውጣት ድንቅ የሆነውን የአጨራረስ ብቃቱን ባሳየ መልኩ በሱሊማና አቡ መረብ ላይ ማስቆጠር ችሏል። ይህችም ጎል መከላከያን ቀዳሚ አድርጋ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ኤሌክትሪኮች ግብ ሳይቆጠርባቸው በፊት ሲያደርጉት እንደነበረው በፍጥነት ወደ አደጋ ክልል መድረሳቸውን ቀጥለዋል።  46ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ተስፋዬ በአስደናቂ ፍጥነት ዐወል አብደላን አልፎ ወደ ግብ የላካት ኳስ በአቤል ማሞ እና በግቡ አግዳሚ ጥረት ግብ ከመሄን የዳነች ነበረች። ታፈሰ ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ከወንድሙ ተክሉ ታፈሰ የደረሰውን ሌላ ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ግን አልተቸገረም ነበር። ነገር ግን 58ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳው አለፍ ብሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ሽመልስ ተገኝ በረጅሙ በቀጥታ ወደ ጎል ሲመታ ጥሩ አቋቋም ላይ ባልነበረው ግብ ጠባቂ ሱሊማና አቡ ግልፅ ስህተት ምክንያት መከላከያ ዳግም ጨዋታውን መምራት ችሏል።

መከላከያዎች በሽመልስ ጎል መሪ ከሆኑ በኃላ አቤል ከበደን እና ቴውድሮስ ታፈሰን በማስገባት የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹን ቁጥር በማብዛት ወደ 4-2-3-1 አሰላለፍ መጥቷል። በዚህም ቡድኑ የመጨረሻዎቹን ሰላሳ ደቂቃዎች ጨዋታውን በጀመረበት መንገድ እንዲጨርስ ሲያደርገው ከመጀመሪያው የተሻለ ነፃነት ያገኘው ዳዊት እስጢፋኖስም ይበልጥ በጨዋታው ላይ ልዩነት መፍጠር ችሏል። ተጨዋቹ 86ኛው ደቂቃ ላይ ማራኪ ወርቁ ሶስተኛውን ጎል ሲያስቆጥር የመጨረሻውን ኳስ ያቀበለበት መንገድ ለዚህ ማሳያ ነበር። መከላከያዎች ከጎሏ በተጨማሪ በሳሙኤል ሳሊሶ እና ማራኪ ወርቁ አማካይነት ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። በአንፃሩ እየወረዱ የመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጫላ ድሪባ እና ኃይሌ እሸቱን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት ሀይላቸውን ለማጠናከር ቢሞክሩም ከጨዋታው ምንምን ነጥብ ሳያገኙ ቀርተዋል። መከላከያ ድሉን ተከትሎ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ኢትዮ ኤሌክትሪክ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ – መከላከያ

ታች ከመሆናችን አንፃር ጨዋታው ለሁለታችንም ወሳኝ ነበር። ለኛ እንደ ስድስት ነጥብ ነው የሚቆጠረው። ከሽንፈት መውጣት ትልቅ የስነ ልቦና ጥንካሬን ያመጣል። ድሉ ለተጨዋቾቼ ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው። የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ቡድኑን ስረከበው የአጨራረስ ድክመት እናዳለበት ነበር ሪፖርት የተደረገልኝ። እሱን ለመቅረፍ እየሰራን ነው።

ም/አሰልጣኝ ኤርሚያስ ተፈሪ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ሆኖም ሰሞኑን ከተዘጋጀንበት መንገድ አንፃር ከጨዋታው የጠበቅነውም ያሰብነውም ውጤት የተገላብጦሽ ነው የሆነብን። ራሳችን የሰራናቸው ስህተቶችም ዋጋ አስከፍለውን ተሸንፈን ወጥተናል። በቀጣይ በድክመቶቻችን ላይ ሰርተን ተሻሽለን ለመቅረብ እንሞክራለን። ሽንፈቱ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን እና ተጨዋቼቹን ያሳዘነ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *