ወልዲያ በፌዴሬሽኑ ውሳኔ ላይ ተቃውሞውን አሰምቷል

ከወድድር አመቱ ጅማሮ አንስቶ ባልተረጋጋ ሁኔታ እየተወዳደረ የሚገኘው ወልዲያ ስፖርት ክለብ ከሰሞኑ በተደጋጋሚ ከአንድ ወር በላይ ጊዜ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቢደረግላቸውም ፍቃደኛ አልሆኑም በማለት በመተዳደርያ ደንቡ መሰረት በሦስቱ ተጨዋቾቹ ላይ የሁለት አመት ቅጣት ማስተላለፉ እና ቅጣቱ ተገቢ አይደለም በሚል ተጫዋቾቹ ቅሬታቸውን ለፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ማቅረባቸው ይታወቃል።

ክለቡ አለብኝ በሚላቸው ክፍተቶች ላይ የዝውውር መስኮቱ መከፈቱን ተከትሎ ሦስት ተጨዋቾች ወደ ክለቡ ያመጣ ሲሆን ቅጣት ያስተላለፈባቸው ተጫዋቾችን ጨምሮ መያዝ የሚፈቀድለትን የተጫዋች ብዛት በስብስቡ ይዟል። ሆኖም  ቅጣት ያስተላለፈባቸው ተጫዋቾች ለቡድኑ ግልጋሎት የማይሰጡ በመሆናቸው በምትካቸው አዳዲስ ተጫዋቾች ለማስፈረም ወደ ፌዴሬሽን በሚያመሩበት ወቅት የተጫዋቾቹ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ውል መፈፀም እንደማይችሉ ተገልጾላቸዋል። ይህ የፌዴሬሽኑ ምላሽም ተገቢ አይደለም በማለት ቅሬታቸውን ማሰማታቸውን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገረመው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

” የዲሲፕሊን ኮሚቴ የመጨረሻ ውሳኔ ምንም ይሁን ምን እየጠበቅን ነው። ክለቡ ውድድር ውስጥ ሆኖ  ከፍተኛ የሆነ የተጫዋቾች ቁጥር ማነስ እንዳለበት እየታወቀ ተጨዋች እንዳናስፈርም መደረጉ አግባብነት የለውም። ፌዴሬሽኑ በውሳኔው የሚፀና ከሆነም ቡድኑ በቀጣይ በሚኖሩት ተከታታይ ወሳኝ ጨዋታዎች ለሚገጥመው የውጤት መጥፋት ኃላፊነቱን እንዲወስድ ስንል ደብዳቤ አስገብተናል” ብለዋል ።

በሦስቱ ተጨዋቾች (ፍፁም ገብረማርያም፣ ታደለ ምህረቴ እና ያሬድ ብርሀኑ) እና በክለቡ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የዲሲፕሊን ኮሚቴው ዛሬ ማምሻውን የመጨረሻ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *